በዝቋላ ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ * የእሳት ቃጠሎው የጀመረው ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው በገዳሙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ነው

zequulla

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የገዳሙ መነኰሳት እየተናገሩ ነው፡፡

ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው የጀመረው ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው በገዳሙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ነው፡፡

ይህ አቅጣጫ፣ የገዳሙ ሞፈር ቤት የሚገኝበት መውጫ መንገድ ሲኾን በአኹኑ ሰዓት በበርካታ ቦታዎች ጭስ እንደሚታይ በመነኰሳቱ ተገልጧል፡፡

የቃጠሎው መንሥኤ በውል ባይታወቅም እሳቱ በአካባቢው ባለው ከባድ የነፋስ ኃይል ወደ ገዳሙ መውጫና በገዳሙ ዙሪያ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል፡፡

የአቅራቢያው ነዋሪ ኅብረተሰብ በጥሩንባ በተላለፈው የድረሱልን ጥሪ የተሰባሰበ ሲኾን ወደ ወረዳው ጽ/ቤትም ተደውሎ የአስተዳደሩ አባሎችና የፖሊስ ኃይል በስፍራው መድረሳቸው ተገልጧል፡፡ ‹‹ቃጠሎውን በቅጠልና በአፈር ለመከላከልና መዛመቱን ለመቀነስ የነፋሱን ጋብ ማለት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፤›› አንድ የገዳሙ መነኰስ፡፡

በጥንታዊውና ታሪካዊው ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ ሲደርስ የአኹኑ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እንደ አርዘ ሊባኖስና የሐበሻ ጥድ ያሉት አገር በቀል ዛፎች በስፋት ወድመዋል፡፡ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ደግሞ ተኣምራዊና ግራ አጋቢ ጠባይዕ የታየበት ነበር፡፡ በምሥራቃዊ አቅጣጫ በሚገኘው የመንግሥት ደን ውስጥ ተከሥቶ በአንድ ገጽ ኃይሉ ሲቀንስ በሌላ አቅጣጫ እየተዛመተ ገዳሙን ጨርሶ ለማጥፋት በተቃረበበት ኹኔታ ከአዲስ አበባ፣ ከቢሾፍቱና ከአዳማ በተመሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና አካላት መተባበር እንዲኹም በመከላከያና በፖሊስ ኃይሎች እገዛ መገታቱ የሚታወስ ነው፡፡
gedam
በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በገዳሙ የጠበል – ሐይቅ የኢሬቻን በዓል ለማክበርና በደብረ ዝቋላ የአባ ገዳ ሐውልት ለመትከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታቀዱንና በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ መገለጹን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር በጻፈችው ደብዳቤ ተቃውሞዋን በማሰማት ላይ እንዳለች ይታወቃል፡፡ጥንታዊውና ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በገዳሙ ደጅ ጠኚውን፣ አፈር ጠባቂውንና የአብነት ትምህርት መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ሳይጨምር እስከ 350 መነኰሳትና መነኰሳዪያት እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a comment