መከራችን መፍትሄ ሳያገኝና ሃዘናችንም ሳይበርድልን ሌላ ከባድ መርዶ ከወደ ሊቢያ ተሰማ

ከአብርሃም ተፈሪ (ሚኒሶታ)

ወዳጆች በቅድሚያ በያላችሁበት የከበረ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ!
ከዚህ ቀጥሎ የምታነቧት አጭር ጽሁፍ በስራ ገበታየ ላይ ሳለሁ በሃሳብ ወዲህ ወዲያ ስባዝን የሞነጫጨርኳት ሰሞንኛ ማስታወሻ ነች።
Abreham D
ሰሞኑን በኛ ኢትዮጵያኖች ላይ የደረሰብንን የሃዘን ማእበል እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በደረሰብን ሃዘን ምክንያት ሁላችንም ልባችን ተሰብሯል ውስጣችንም በቁጭት ተቃጥሎ አሯል። የመን ውስጥ በጦርነት መሃል እየተሰቃዩና እየተገደሉ ስላሉ ወገኖቻችን አዝነን ምን ብናደርግ ይሻላል እያልን እየተወያየን ባለንበት ሁኔታ ሌላ አሰቃቂና ጥላቻን መሰረት ያደረገ ኢ-ሰብዐዊ ድርጊት ከደቡብ አፍሪቃ ተሰማ። በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ከሃገራቸው ኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት ተሰደው በሰው ሃገር ደከመኝ ሳይሉ ቀን ከሌት ሰርተው በላባቸው የሚኖሩ መሆናቸውን ቀናው የሃገሬው ህዝብ የመሰከረበት የአደባባይ እውነት ነው። ይህንን የኢትዮጵያውያኑን ጥንካሬና ችሎታ ተመልክተው የዙሉ ጎሳ የሆኑት የደቡብ አፍሪቃ ዜጎች ለስራ ሊነሳሱ ሲገባ፤ በተቃራኒው ፍጹም ጥላቻን መሰረት ባደረገ ስሜት ካገራችን ይውጡልን በማለት ሲፎክሩ ተሰምተዋል። ይህም አልበቃ ብሏቸው ኢ-ሰብዐዊ ድርጊታቸውን በወገኖቻችን አንገት ላይ ጎማ በማስገባት በጠራራ ፀሃይ እመንገድ ላይ ቤንዚን አርከፍከፍክፎ በመግደል አሳይተዋል። በዚህም ኢ-ሰብዐዊ በሆነ አሰቃቂ ድርጊት ስድስት የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከነዚህም ሶስቱ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን መሆናቸውን የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበውታል። (እዚህጋ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪቃ ላደረገችው የነፃነት ትግል ከፍተኛ አስትዋፆ ማድረጓን ልብ ይሏል።)

(Photo File)
ይህ መከራችን መፍትሄ ሳያገኝና ሃዘናችንም ሳይበርድልን እንደድንገት የድንገት ሌላ ከባድ መርዶ ከወድ ሊብያ ተሰማ። እልም ባለው የሊብያ በርሃና የሜድትራኒያን ባህር ዳርቻ አይሲስ የተባለው ሰይጣናዊ ቡድን ፴ የሚሆኑ የመስቀሉ ተከታይ ኢትዮጵያውያኖችን አንገታቸውን በካራ ቀልቻለሁ በጥይትም ደብድቤ ገድያቸዋለሁ ሲል አወጀ። ይህንንም ስለማድረጉ ማሳያ የሚሆነዉን ወደ ፪፱ ደቂቃ የሚሆን በምስል የተደገፈ ቪድዮ ለቀቀ። ይህንንም ተከትሎ ትላልቆቹ የመገናኛ አውታሮች ወሬውን ተቀባብለው ዘገቡት። እኝም ኢትዮጵያውያን ይህን ዜና እንደሰማን ሃዘናችን እጥፍ ድርብ ሆነ። በሀገር ውስጥም ከሃገር ውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዳግም ልባቸው በከፍተኛ ሃዘን ተሰበረ። ንፁህ ወገኖቻችን እንደ በግ እየተጎተቱ ወደ እርድ ቦታቸው ሲወሰዱ ማየት እጅግ በጣም ያማል። በ፪፩ኛው ክ/ዘመን ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብ ጭካኔ በኢትዮጵያኖች ላይ ሲደርስ ሰው ሆኖ መፈጠርን ያስመርራል። ይህ ከሆነ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከያለበት ቁጣውን፣ ሃዘኑንና ቁጭቱን ማስተጋባት ጀመረ። ይህ ነው በማይባል ሃዘን ሁላችንም እንደተመታን ግልፅ ሆነ። በተለያዩ ሚድያዎችና ማህበራዊ ድህረ ገፆች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአድማስ ጥግ እስከ ጥግ እንባውን ረጨ፣ ማቅ ለበሰ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ጎበዙ መንግስታችን ከተደበቀበት የአራት ኪሎ ጫካ ግቢ ውስጥ ፍፁም ሃላፊነትና ሰብዐዊነት ስሜት በጎደለዉ መንገድ “ስለምን እንደምታወሩ አላውቅም፣ የሰዎቹንም ማንነት በተመለከተ ግብፅ ካይሮ የሚገኘውን ኤንባስዬን አነጋግሬ ኢትዮጵያዊ ስለምሆንና ስላለመሆናቸው ያገኘሁት ማረጋገጫ የለም” በማለት መሪር ሃዘናችን ላይ ተሳለቀብን። ከዛም በመቀጠል ሃዘናቸውን ለመግለፅ በወጡት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ እንደተለመደው የፌደራል ፖሊሶችን በማሰማራት ድብደባና እስራትን አካሄደ። ከዚህም ለመረዳት የሚቻልው የሕወሀት ባለስልጣኖች እንዲሁ በድፍረት እንመራለን እናስተዳድራለን ብለው ወንበር ላይ ተቀመጡ እንጂ የአመራር ጥበብና ችሎታ የሌላቸው፣ ለወቅታዊ ክስተቶች አፋጣኝ የሆነ መፍትሄ መስጠት የማይችሉ፣ በግድ ካልመራንህ እያሉ ከሚያስገድዱት ህዝብ ወደ ኋላ ስልሳና ሰባ ዓመት ርቀው የሚገኙና ከምንም በላይ ሰብዐዊና ሞራላዊ ስሜት የሌላቸው ፍጡሮች መሆናቸውን ነው። በነዚሁ ቡድኖች ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቷ በግልፅ የሚታወቅ ቢሆንም የችግሮቹ ጥልቀትና ስፋት ማለትም ( የሰብዐዊ መብት ጥሰቱ፣ የሙስናው፣ የዘር ክፍፍሉ፣ ሰዎችን ያል አግባብ ማሰሩና መወንጀሉ፣ የብሄራዊ ማንነት መዋረዱና ወዘተረፈ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ጉዳዩን እጅግ በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል።

በዚህ አጭር ፅሁፌ የችግሮቹን መንስኤዎች ሁሉ ለመዘርዘርና ለመተንተን አልደፍርም ነገር ግን የአብዛኛዎቹ ችግሮች መንስኤ መንግስት ነኝ የሚለው የሕወሃት ቡድን የሚከተለው የተበላሸ ፖለቲካ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ተጠቅሞ ብሄራዊ ኩራትና ማንነቱን ሊያስመልስ ይገባል ስል አጥብቄ እከራከራለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ እግረ መንገዴን አንዳንድ የማምንባቸውን የምፍትሄ ሃሣቦች እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ።

የመፍትሄ ሃሳብ ፩፡ በሃገሩስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የምንገኝ ኢትዮጵያኖች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአንድነት አብረን ልንቆምና ልንተባበር ያስፈልጋል። ካለንበት ዘመን ጋር አብረው የማይሄዱትን፣ ኋላ ቀርነታችንን ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት እሴትና ኩራት የማይጨምሩልንን ጠባብ የሆኑ የዘርና የፖለቲካ አመለካከት ጭምብሎቻችንን አውልቀን ልንጥላቸው ይገባል። አይጠቅሙንም! የትም አያደርሱንም። ይልቁንም በዘር በሃይማኖት ሳንለያይ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በሕብረት ልንቆም ይገባል። ምናልባትም አስቀድመን ይህን አድርገን ቢሆን ኖሮ እንዲህም አይነቱ መሪር ሃዘን ባልመጣብን ነበር።

የመፍትሄ ሃሳብ ፪፡ ሁላችንንም ኢትዮጵያዉያንን ሊያስተሳስር የሚችል ጠንካራ የሆነ አቋም ሊኖረን ይገባል። ችግርና ሰቆቃ ሲደርስብን ብቻ ሳይሆን በአዘቦቱም ግዜ የህዝባችንና የሃገራችን ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል። ለምሳል፡ ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ላይ ሁላችንም ቁርጥ ያለ አቋም ሊኖረን ይገባል። የመብት ጥሰት ትንሽ ትልቅ የለውምና ሁላችንም ለመብታችን መቆምና መታገል አለብን። ይሄ ጉዳይ ትንሽ ነው ብለን ልናልፈው የሚገባ ነገር መኖር የለበትም። በዛ ደረጃ ልዩ ትኩረት መስጠት ስንችል ነው እንዲህ አይነት ከባድ ችግሮችን ማስወገድ የምንችለው።

የመፍትሄ ሃሳብ ፫፡ በሃገራችን የፖለቲካም ይሁን የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የያገባኛልና የባለቤትነት ስሜት ሊሰማን ግድ ይላል። እንደዛ ሲሆን ነው እኛን የሚመጥን ዘመናዊ የሆነ መሪም ሆነ አስተዳድር ልናገኝ የምንችለው። በተራ የፖለቲካ ዲስኩርም ልንታለል አይገባም። ይሕንን ማድረግ ስንችል ነው ብሄራዊ ክብርና ኩራታችንን የምናስመልሰው። አለበለዚያ ሁሌም ከሌሎች በታች ሆነን አንገታችንን ደፍተን እንኖራለን።

በመጨረሻም ብዙዎቻችን የተለያዩ ጠቃሚ የመፍትሄ ሃሳቦች እንደሚኖሩን በመገመት ፅሁፌን በዚሁ አጠናቅቃለሁ።
ከመቼውም በላይ ተነቃቅተን የመፍትሄ ሃሳቦቻችን ላይ ልናተኩር ይገባል እላለሁ!
አመሰግናለሁ!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
አብርሃም ተፈሪ

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s