የዩኒቨርስቲው በር ተሰብሯል! ዐምዶቹም ተነቃንቀዋል!

By ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የአ.አ ዩ የቀድሞ የፍልስፍና መምህር)
በዚህ ጽሑፍ የማነሣቸው ርእሰ ጉዳዮች በአራት የተከፈሉ ናቸው፡፡
አንደኛው፡- ስለ ዩኒቨርስቲ አጠር ያለ መሠረታዊ ሐሳብ እና የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፤
ኹለተኛ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት መዳፍ ሥር ስለ መውደቅ፤
ሦስተኛው፡- የፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬን ገጸ ሰብእና (persona) በኹለት ወጎች ሥር ማብራራት ሲኾን፣
አራተኛው፡- የርእሰ ጉዳዮቹ ማጠቃለያ ነው፡፡
፩ (ሀ) ዩኒቨርስቲ እና አካዳሚያዊ ነጻነት ከኹሉ አስቀድሞ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው፣ በዚህ ጽሑፍ የቀረቡት አስተያየቶች እና ምልከታዎች እንደ አንድ በፍልስፍና መስክ የተሰማራ ሰው መጠየቅ ያለባቸውን ነገሮች ለመጠየቅ ያለሙ ናቸው፡፡ ይህም ሐሳቦቹ እና ምልከታዎቹ በአጠቃላይ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከመከጀል ብቻ ሳይኾን ሳንጠይቃቸው ብናልፍ ትክክል አይኾንም ከሚል እምነት በመነሣት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንደኛው ዓላማ የሚያጠነጥነው፣በዩኒቨርስቲ ምንነት ዙሪያ በመኾኑ ስለ ዩኒቨርስቲ ጠቅለል ያለ ዕሳቤ እና በተጨማሪም ዩኒቨርስቲን፣ “ዩኒቨርስቲ” የሚያሰኙትን ርእይ፣ ተልእኮ እና ግብ ማሳየት ነው፡፡ የዩኒቨርስቲ ዋነኛው ርእይ እና ተልእኮ፣ ዕውቀት ማፍለቅ ሲኾን፣ ያፈለቀውንም ለተማሪዎች ማስተላለፍ እና መተግበር ነው፡፡ ይህም ማለት የዩኒቨርስቲ ዋነኛው ተግባር ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ አኹን ላይ የደረሰውን ዕውቀት መጠበቅ እና መከባከብ እንዲኹም በተሟላ መልኩ ለትውልዱ ማሳወቅ እና ማስተላለፍ ነው፤ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልነበረውን ሐሳብ እና ዕውቀት መፍጠርም ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ የአንድ ሀገር ምሁራዊ ህልውና እና የሥልጣኔ ዕድገት መገለጫ በመኾኑ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሌሎች ተቋማት በተሻለ የሕግ እና የነጻነት መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ ካርል ያስፐርስ ስለ ዩኒቨርስቲ ምንነት ሲገልጹ፤ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት ቁሳዊ እና ፋይናንሳዊ ድጎማ የሚተዳደር ቢኾንም ከሌሎች ተቋማት ለየት የሚያደርገው የራሱን ርእይ እና ተልእኮ ቀርጾ የሚተገብር እና የሚንቀሳቀስ አንጻራዊ ነጻነት ያለው በመኾኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን የመንግሥት ደመወዝተኛ ቢኾኑም እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች (civil servants) የመንግሥትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተቀጠሩ አገልጋዮች የማይኾኑት፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርስቲ ዐቢይ ተልእኮ የምንለው፣ ተቋሙ እውነት ላይ ለመድረስ ማንኛውም ጉዳይ የሚጠየቅበት እና የሚመረመርበት ማእከል መኾኑ ነው፡፡ ይህንንም ተልእኮ በአግባቡ ለመወጣት ዩኒቨርስቲ በልዩ ልዩ ተቋማት ሥር ለሚያካሒደው ጥናት እና ምርምር ያልተገደበ ነጻነት እና መብት ይኖር ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ዩኒቨርስቲ ነጻነቱን በማስቀደም ነው፣ የዕውቀት መዲና እና መፍለቂያ ኾኖ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ የመጣው፡፡ የዩኒቨርስቲ ነጻነትን ባነሣን ቁጥር የአካዳሚያዊ ነጻነት ጥያቄ ቁልፍ የኾነ ድርሻ ያለው መሠረታዊ ሐሳብ እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡ (ለ) አካዳሚያዊ ነጻነት አካዳሚያዊ ነጻነት ማለት ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ ሊኖረው የሚገባውን ነጻነት እና መብት የሚደነግግ የሕግ መርሕ ነው፡፡ አኹን በዓለም ላይ በሰፊው ተቀባይነት ያገኙት የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፣ የዛሬ አንድ መቶ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በጉዳዩ ዙሪያ የጥናት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ተሳታፊዎቹ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች አቅርበው፣ ሕጋዊ ከለላ ለማሰጠት በመቻላቸው እነሆ እስከ አኹን ድረስ ወሳኝ የኾኑ የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች እና አዕማድ ኾነዋል፤ ፍሬ ሐሳቦቹም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ 1. የመመራመር እና የማሳተም ነጻነት ማንኛውም መምህር በፈለገው እና በመረጠው ርእስ ምርምር እና ጥናት የማካሔድ ሙሉ መብት አለው፡፡ በተጨማሪም በምርምር ያገኘውን ውጤት ያለምንም ዕንቅፋት እና ገደብ የማሳተም መብት አለው፡፡ 2. መምህር በክፍል ውስጥ ስለሚኖረው ነጻነት ማንኛውም መምህር ለሚያስተምረው ትምህርት ይኾናል የሚለውንና የሚበጀውን የማስተማርያ ጽሑፎችን የማካፈል እንዲኹም ማንኛውንም ትምህርት ነክ የኾኑ ጉዳዮችን በውይይት እና በጥያቄ ያለምንም ጫና ለተማሪዎቹ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ 3. በትምህርት ተቋም ቅጽር ውስጥ የሚኖር መብት/Intramural Right) ማንኛውም መምህር አቅሙና ችሎታው እስከ ፈቀደ ድረስ የአንድን የዩኒቨርስቲ አስተዳደር እና አመራር ሳይፈራ እና ሳይሸማቀቅ የማሔስ እና የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡ 4. ከትምህርት ተቋሙ ቅጽር ውጭ ስላሉ ጉዳዮች የሚኖር መብት(Extramural Right) ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ እያለ የሀገሩን የአስተዳደር፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዳዮችን የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡ እነዚህ ከላይ የተገለጹት መርሖዎች በሕግ ማህቀፍ ሥር መካተታቸው፣ በአካዳሚው ዓለም ውስጥ ለተሰማሩ መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑና እንዲኹም ለወከባና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መከታ ይኾናቸዋል፡፡ ፪. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ለመቆጣጠር የተደረገው ሒደት ኢሕአዴግ ስለ ፖለቲካ ስትራቴጅና አቅጣጫ በ1997 ዓ.ም. ባወጣው ሰነድ ላይ፤ ስለ ሀገሪቱ ምሁራን የሚከተለውን ግምጋሜ አቅርቧል፡፡ ግምጋሜው የታየበትን መነጽር፣ ከዚህ በታች ስለምናቀርበው የዩኒቨርስቲው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል መንደርደሪያ ይኾነናል፡፡ እንደ ኢሕአዴግ አመለካከት፣ምሁሩ ምንጊዜም ወደ ሥልጣን ማማተሩ ስለማይቀር በተቻለ መጠን የሥልጣን መወጣጫ መንገዱ ተዘግቶ መያዝ አለበት፡፡ ይህን ለማሳካት ምሁሩ የንዋይ ፍላጎቱ በተቻለ መጠን እንዲሟላለት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም በሙያው ዙሪያ ባሉ ሳንካዎችና ጥቅማጥቅሞች ተጠምዶ ወደ ሀገራዊ ጥያቄዎች ሳይሻገር በእዚያው ማጥ እየዳከረ እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከዛሬ ስድስት መቶ ዓመት በፊት፣ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ከደረሷቸው መጻሕፍት መካከል ‘መጽሐፈ ምስጢር’ ብለው በሰየሙት ድርሳናቸው ውስጥ፣ ሳይማሩ እናስተምራለን ብለው ስለተነሡ የቤተ መንግሥት ባለሟሎች የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ከአባ ጊዮርጊስ የወሰድነው ጥቅስ ሊቁ ለሌላ ጉዳይ የተናገሩት ቢኾንም ለያዝነው ርእስ የመንፈስ ቅርበት አለው ብለን ስለምናምን በዚሁ አገባብ የጠቀስነው መኾኑን ለአንባብያን እያስታወስን ጥቅሱን ያጎረሱንን መሪጌታ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ “እሉ እሙንቱ [መነኮሳት] እለ ቀዲሙ የዐየሉ ገዳመ አድባረ ወበዐታተ ወድኅረ ይትዋሐውሑ በአዕጻዳተ ነገሥት፡፡ ቀዲሙ ከመ ኢይትመሀሩ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት በንኡሶሙ ወጽኡ ገዳመ ወተግኅሡ እምዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እንተ ይእቲ እመ ኩልነ ዘኢይነጽፍ ሐሊበ አጥባቲሃ፡፡ ወድኅረኒ ኢይፈጽም ገድሎሙ በጽማዌ ውስተ ገዳም ቦኡ ውስተ አብያተ ነገሥት ወበዊኦሙ ከመ ኢያርምሙ መሀሩ ዘኢትምህሩ ወሰበኩ ዘኢያእመሩ፡፡ ይልህቅኑ ሕፃን ዘእንበለ ሐሊበ አጥባተ እሙ ይሌቡኒ መነኮስ ዘኢተምህረ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት ከመ ይኩን መመህረ ለሰማዕያን ፡፡ ለሀወት ገዳም በኃጢአቶሙ ወለሀዋ አድባረ ምኔታት ወኢረኪቦቶሙ፡፡ “ለሀወት ቤተ ክርስቲያን በእንተ ዘነሠቱ አናቅጺሃ ነቢያተ ወነክነኩ አዕማዲሃ ሐዋርያተ፡፡ ወሠርዑ ሎሙ ሕገ ወሥርዓተ ዘኢይወጽአ እምእስትንፋሰ አፉሁ ለእግዚአብሔር ፡፡” ትርጉም፡- “እነዚህ [መነኮሳትም] ቀድሞ በበርሀ በተራሮችና በዋሻዎች የሚዘዋወሩ በኋላ ግን በነገሥታት ዐፀዶች ውስጥ የሚመላለሱ ናቸው፡፡ ቀድሞ በታናሽነታቸው ጊዜ የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት እንዳይማሩ የጡቶቿ ወተት የማይደርቅ የኹላችን እናት ከኾነች ከቤተክርስቲያን ዐፀድ ርቀው ወደ ገዳም ወጡ፡፡ ኋላም ገድላቸውን በገዳም ውስጥ ኾነው በጭምትነት እንዳይፈጽሙ ወደ ነገሥታት ቤት ይገባሉ፤ገብተውም ዝም እንዳይሉ ለራሳቸው ያልተማሩትን ያስተምራሉ፤የማያውቁትንም ይሰብካሉ፣ሕጻን ያለ እናት ጡት ያድጋልን? መነኩሴስ ለሚሰሙ ሰዎች አስተማሪ ይኾን ዘንድ ያልተማረውን የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት ያስተውላልን? “ቤተ ክርስቲያን ስለ ኃጢአታቸው አለቀሰች፡፡ የገዳማት ተራሮችም እነርሱን ባለማግኘታቸው አለቀሱ፤ቤተ ክርስቲያን ነቢያት በሮቿን ስላፈረሱ፣ ምሰሶዎቿ ሐዋርያትንም ስለነቀነቁ አለቀሰች፡፡ ከእግዚአብሔር አንደበት ያልወጣውንም ሕግና ሥርዓት ለራሳቸው ሠሩ፡፡” ከላይ በጥቅስ ከተቀመጠው የአባ ጊዮርጊስ ትዝብት የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡ የአመራረጣችን መሠረት፣ ባለንበት ወቅት አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዴት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት መዳፍ ሥር እንደ ወደቀ የጥቅሱ መንፈስ ማሳያ ኾኖ ስላገኘነው ነው፡፡ አኹን በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት፣ ከገጠር ወደ ከተማ እንደ መጣው ኹሉ፣ የአባ ጊዮርጊስም ‘ምሁራን’ ከበረሓ ወደ ቤተ መንግሥት የመጡ በመኾናቸው ተመሳሳይነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ የቅዱሱን ተግሣጽ በኹለት ምድብ በመክፈል በመጀመሪያ፣ የትዝብታቸውን መነሻ ቀጥለን ደግሞ፤ ድርጊቱ ያስከተለውን አሉታዊ ዉጤት እናያለን፡፡ ሀ. የትዝብታቸው መነሻ፡- የተወሰኑ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት በመፈለግ ወደ ዋሻ፣ አድባራት እና በረሓ ገቡ፡፡ መንፈሳዊ ተጋድሎ አልኾንላቸው ሲል በረሓውንና ዋሻውን ለቀው ወደ ቤተ መንግሥት ጠጋ አሉ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም አዘውትረው መመላለስ ጀመሩ፡፡ ከማዘውተራቸው ብዛት የቤተ መንግሥቱን አመኔታና ይኹንታ ተቀዳጁ፡፡ የሹማምንቱን ቅቡልነት ቢያገኙም በየበረሓው ወጣትነታቸውን በከንቱ አባክነው በዘመኑ ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ይገኝ የነበረውን ትምህርት ሳያገኙ ስለቀሩ፣ የቤተ መንግሥት ባለሟልነታቸውን ተጠቅመው፣ ያልተማረውን ምእመን እናስተምራለን ብለው ተነሡ፡፡ ለ. ድርጊቱ ያስከተለው አሉታዊ ውጤት፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፤ኹኔታው ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በኹለት ዘይቤ (Metaphor) ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም፡- “በሮቿ ተሰበሩ” እና “አዕማዷ ተነቃነቁ” የሚሉት ናቸው፡፡ በሮቿ ተሰበሩ፡- “በሮቿ ተሰበሩ” ከሚለው ዘይቤ ውስጥ በዛ ያሉ ምልከታዎችን መንቀስ ይቻላል፡፡ በር ስንል የሚፈለገው የሚገባበት፣ መግባት የሌለበትን ደግሞ መቆጣጠሪያ ሥርዓት መኾኑን ነው የሚያመለክተው፡፡ በመኾኑም የተናጋና የተሰበረ በር ያለው ተቋም፤ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት፣ ሥርዓት አልባ ጎዳና ኾኗል ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ልዕልና አስጠብቃ መዝለቅ ተስኗታል እንደማለትም ነው፡፡ አዕማዷ ተነቃነቁ፡- የአንድ ቤት ዐምዱ ወይም ምሶሶው ከተነቃነቀ፣ጨርሶ የመፈራረሱ ጉዳይ ተቃርቧል ማለት ነው፡፡ በአባ ጊዮርጊስ ዕይታ፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት በአጠቃላይ አስተምህሮዋ ተናግቷል ማለታቸውን ያሳያል፡፡ በተፈጠረው አግባብ የለሽ አካሔድና ቀውስ የቤተ ክርስቲያኒቷ አበው አዘኑ፤ አለቀሱም፡፡ ወደ ጥንተ ነገራችን ስንመለስ፤የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አቀራረብ፣ አኹን በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ የሚካሔደውን ኹኔታ በሚገባ ለመረዳት እንደ መነጽር ይኾነናል፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ፣ የአባ ጊዮርጊስ ‘መምህራን’ እናስተምራለን ብለው የተነሡት ራሳቸው ሳይማሩ ያልተማሩትን ሰዎች ለማስተማር ነው፡፡ በእኒህ ኹለት ዓመታት ውስጥ፣ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እናሠልጥን ብለው የተነሡት የመንግሥት ሹመኞች ራሳቸው በሚገባ ሳይማሩ፣ አልተማሩም የሚሏቸውን ሳይኾን፣ የተማሩትን ክፍል ለማስተማር መነሣታቸው ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር አባ ጊዮርጊስ የታዘቧቸው መምህራን ከአኹኖቹ እናስተምር ባዮች በእጅጉ የተሻሉ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይኸውም የቀድሞዎቹ፣ ራሳቸው ባይማሩም እናስተምር ያሉት ያልተማሩትን ሲኾን የእኛዎቹ ግን እናስተምር ብለው የተነሡት የተማሩትን በመኾኑ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ኀዘናቸው ምን ያኽል በበረታ ነበር!! አባ ጊዮርጊስን በእጅጉ ያሳዘናቸውና ያስገረማቸው፣ ቤተ መንግሥት በፍጥረቷ የአስተዳደር መንገድ መቀየስ እንጂ የዕውቀት ምንጭ ወይም የምሁርነት ምኩራብ ሳትኾን፣ ዐዋቂዎች ነንና እናስተምር እያሉ የሚነሡባት ማእከል ኾና ስላገኟት ነው፡፡ አኹን ወዳለንበትም ጊዜ ስንመጣ፣ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለው በየዩኒቨርስቲው እናሠልጥን እያሉ የሚመጡት ሰዎች አኳኋን ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’ አስቀድመው ወደ በረሓ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ቤተ መንግሥቱን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ፡፡ ከዚያም ቤተ መንግሥቱም ዩኒቨርስቲውም አይቅርብን ብለው የዩኒቨርስቲውን መምህራን እናስተምራለን ብለው ብቅ አሉ፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ኀዘን የበረታው፣ እኒኽ ‘ምሁራን’ ቤተ ክርስቲያን እንደ በሮቿ የምታያቸውን የነቢያት አስተምህሮ ስለሰበሩና በምሰሶ የተመሰሉትን የሐዋርያትን ዶግማና ቀኖና ስላነቃነቁ ነው፡፡ ብዙዎችን ታዛቢዎች በእጅጉ እያሳሰባቸው ያለው በአስተማሪነትና በአሠልጣኝነት ስም፤ ዩኒቨርስቲው የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የምርምርና የመሳሰሉት ዕሴቶች ገዳም ኾኖ ሳለ፤ ሊቃነ ማእምራኑ (ፕሮፌሰሮቹ) ያስቀመጧቸውን ሚዛኖች (በሮች) በመስበር አዕማዷን ስላነቃነቁት ነው፡፡የቤተ ክህነቱ በር እንደተሰበረው ኹሉ፣ የየኒቨርሲቲውም በር ተሰብሯል ስንል ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹንም ኾነ መምህራኑን መርጦ የመቀበል መብቱ ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ትእዛዝ እንዲሞላ በመደረጉ፣ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት ኾኗል ማለታችን ነው፡፡ የአዕማዷን መነቃነቅ በምናነሣበት ጊዜ በዋናነት የምናቀርበው፣ ዩኒቨርስቲው የነበረው የማስተማር ሥነ ዘዴ ተሽሮ፣ ከፖለቲካ ኃይሉ በመጣ ማዘዣ፣ እነርሱ ይበጃል የሚሉትን አካሔድ ተግባራዊ እንዲያደርግ መገደዱን ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው፣ ከቢፒአር እስከ ቢኤስሲ እና አንድ ለአምስት አደረጃጀትን መምህራኑ ሳይመክሩና ሳይዘክሩበት፣ ዩኒቨርስቲው እንዲከተል መደረጉ ነው፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’፣ የመንግሥትን ኃይልና ቤተ ክርስቲያንን ገና በሚገባ ያልተቆጣጠሩ ሲኾን፣ የአኹኖቹ ምሁሮች ግን ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ ለያዙ ኃይሎች ተጠሪዎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ከንኡሳን (ደቃቂን) ሓላፊዎች እስከ ዐቢይ አለቃው – ፕሬዝዳንቱ፣ ድረስ ለቤተ መንግሥቱ የፖለቲካ ቀኖና ተገዥና ተኣማኒ በኾኑ እሺ ባዮች እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ እውነተኛ ዩኒቨርስቲያዊ ይትበሃል ተሽሮ፣ የበረሓ ጀግኖች እንዳፈተታቸው የሚናኙበት ኾነ፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም፣ ዩኒቨርስቲያዊ ልዕልናው ስለ ተገፈፈ ሳይንሳዊና ሞያዊ አሠራሩ ተሻረ፡፡ በቦታውም ከፖለቲካው ጽሕፈት ቤት በሚመነጭ ኢሕአዴጋዊ ትእዛዝ በሩን አፈረሱት፤ ዐምዱንም አነቃነቁት፡፡ ካርል ያስፐርስ የገለጹት ‘አማናዊው ዩኒቨርስቲ’ እና እውነተኞቹ ምሁሮቿ ስለ እነዚህ ሰዎች አድራጎት አብዝተው ያዝናሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲቋቋም፣ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የበሩን ኹለት አዕማድ ‘በዕውቀት’ እና ‘በሠናይ’ (Virtue) በመመሰል የዘመሩለት፣ ማንም ሰው ሊያየው በሚችለው መልኩ መሠረቱ ተናጋ፤ ውድቀቱም ተቃረበ፡፡
፫. የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ገጽታ፣ ከኹለት ትረካዎች አንጻር ሲፈተሽ ፕሬዝዳንት አድማሱ ለአራት ዓመታት የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር ኾነው በቆዩባቸው ጊዜያት፣ እኔም እንደ አንድ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ አባል ኾኜ በማገለግልበት ወቅት ስለ ሰውዬው ያየኹትንና የታዘብኩትን ጉዳይ በሚከተሉት ወጋዊ ትረካዎች ለማቅረብ እሞክራለኹ፡፡ ይህንንም ለመተግበር ፕሬዝዳንቱ በተለያዩ ወቅቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ካደረጉት ንግግር፤ በየጊዜው የዩኒቨርስቲውን አስተዳደርና ሒደት በሚመለከት ጽፈው ወደተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በላኳቸው ሰነዶች እናም በመጨረሻም ዩኒቨርስቲው ልማታዊ ወይም ተግባራዊ መንገድ ይዞ መጓዝ አለበት ብለው ደጋግመው ካቀረቡት ዕቅድ በመነሣት ነው፡፡ ሀ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የካውንት ሌቭ ቶልስቶይ ጀነራል ከዚህ የሚከተለውን ትረካ የወሰድኩት፣ ከሌቭ ቶልስቶይ “ጦርነት እና ሰላም” ከሚለው ታላቁ ድርሳን ነው፡፡ ለአንባብያን እንዲመች ለማድረግ ሐሳቡ ላይ ትኩረት በመስጠትና በማገናዘብ እንደሚከተለው አቀርባለኹ፡፡ የታሪኩ መቼት፣ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “የናፖልዮኒክ ጦርነት” ተብሎ በሚጠራውና ናፖሊዮን ቦናፓርት ሩስያን ወርሮ ለመያዝ ባካሔደው ጦርነት ወቅት ነው፡፡ የፈረንሳይ ሠራዊት በዚያን ጊዜ በጦርነት ዐውድማ ማንም ተፎካካሪ ኃይል ስላልነበረው፣ የወረራ አቅጣጫውን ወደ ሩስያ ባደረገበት ወቅት ትልቅ መደናገጥንና ፍርሀትን በመላው ሀገሪቱ አሳደረ፡፡ የወራሪውን ሠራዊት ለመቋቋም በአንድ የተወሰነ ግንባር ያሉ የሩስያ ጀነራሎች የመከላከል ዕቅድ ለመንደፍና በአጠቃላይ የጦርነት ስልት ለማዘጋጀት ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከቶልስቶዩ ጀነራል በስተቀር ኹኔታውን በጥሞና በመከታተል የተቻላቸውን የሐሳብ አስተዋፅኦ ለማበርከት ሞክረዋል፡፡ በአንጻሩ ግን ጀነራሉ ስለ ውጊያው ስትራቴጂ የበኩሉን ድርሻ ማቅረብ ከመዘንጋቱም በላይ የጉዳዩ ክብደት ሳያሳስበው እያንቀላፋ ነበር፡፡ የጀነራሎቹ ስብሰባ አልቆ ኹሉም የድርሻቸውን የውጊያ ሚና ከተከፋፈሉ በኋላ ተለያዩ፤ ጀነራሉም የተወሰነ ድርሻውን በሓላፊነት ተረክቦ ወደ አንደኛው ግንባር ተላከ፡፡ በበነጋው ይኼው ጀነራል የዕዙን ወታደሮች ይዞ ከጦር ሜዳው ደረሰ፡፡ በሥሩ ያሉት መኮንኖች ጦሩን ቦታ ቦታ ካስያዙ በኋላ ፍልሚያ ሊጀምር ትንሽ ሲቀረው ጀነራሉ ከቦታው ተሰወረ፡፡ አብረውት የነበሩት የጦር አመራሮች በመገረም የጀነራሉ ምክትል ዕዙን ተረክቦ እንዲመራ በመስማማት በጣም ከከረረ ውጊያ በኋላ ሩስያውያኑ ድል ቀንቷቸው የወራሪውን ኃይል ለመመለስ ቻሉ፡፡ ከጦርነቱም በኋላ ባገኙት ድል በመደሰት፣ ሞቅ ያለ ግብዣ ተደርጎ በትልቅ ድግስ ላይ እንዳሉ ጀነራሉ በነጭ ፈረስ ላይ ኹኖ ከግብዣው አካባቢ ብቅ አለ፡፡ ይህን ያዩ መኮንንኖች ወደርሱ ቀርበው፣ “በጣም የምታስገርም ሰው ነህ፡፡ ከትላንት ወድያ የጦርነቱን ፕላን ስናወጣ፣ አንተ ታንቀላፋ ነበር፤ ትላንት ጧት ደግሞ እንድታዋጋ ተሰጥቶኽ ከነበረው ግንባር ተሰወርክ፡፡ እንደዚህ ዐይነት ድርጊት ወደ ጦር ፍርድ ቤት እንደሚያስወስድኽና ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያሰጥኽ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡” በማለት በቁጣ ተናገሩት፡፡ ጀነራሉ፣ ተናደው በቁጣ ላናገሩት መኮንኖች የሚከተለውን መልስ ሰጣቸው፡፡ “ከኹሉ አስቀድሞ ንዴታችኹ ይገባኛል፡፡ ኾኖም ግን አንድ ለናንተ የተሰወረና እኔ ደኅና አድርጌ የማውቀው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸዉም ከእናንተ ይበልጥ እኔ ራሴንና ማንነቴን ጠንቅቄ ስለማውቅ ነው፡፡ እኔ የጦርነቱ ፕላን ሲወጣ ሙሉ ለሙሉ ተካፋይ ብኾን ኖሮ፣ ዛሬ ድል ከእናንተ ጋር አትኾንም ነበር፡፡ ትላንትናም ቢኾን በጦር ሜዳው ግምባር ዋናው አዋጊ ብኾን ኑሮ ከድል ይልቅ ዕጣችኹ እንዲኽ አያምርም ነበር፡፡ ዐያችኹ፤ ከኔ ይልቅ ምክትሎቼ የተሻሉ አዋጊዎች ናቸው ብዬ ስላመንኩ ሓላፊነቱን ለእነሱ ትቼ ዘወር አልኩ፡፡ በእኔ ዐተያይ ሀገር መውደድ ማለት የራስን አቅም ሳይፈትሹ፣ አደርገዋለኹ በሚል ድፍረት መንቀሳቀስ ሳይኾን የራስን ችሎታና አቅም በሚገባ አጢኖ፣ የተሻለ ሰው ከተገኘ የሥራ ምድቡን ለቆ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ለሀገርና ለወገን ሲባል ከቦታው ዘወር ማለት ነው፡፡” በዚህ ትረካ ያየነው፣ የቶልስቶዩ ጀነራል ችሎታ ባይኖረውም ሀገሩን የሚወድና የሞራል ላቂያ ያለው ሰው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በእሱ አስተያየት፣ ሀገር መውደድ ማለት ከኹሉ አስቀድሞ ችሎታም ባይኖር የያዙትን ሹመት የሙጥኝ ብሎ አልለቅም ከማለት ለተሻለ ሰው ቦታውን መልቀቅ ማለት ነው፡፡ ወደ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ስንመለስ፤ ራሳቸውን ከማወቅ አንጻርም ኾነ ለያዙት ቦታ ከእርሳቸው የተሻለ፣ እዚኹ ግቢ ውስጥ፣ በርከት ያለ ሰው መኖሩን እያወቁ እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ዘወር አለማለታቸውን ስንታዘብ፣ ስለ ራሳቸው የተሳሳተ ግምት እንዳላቸውና ሀገር ወዳድነታቸውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለን እናስባለን፡፡ ምናልባት በዚህ ድምዳሜ ላይ ፕሬዝዳንቱ፣ ሀገሪቱን በበላይነት ከሚያስተዳድሩት ውስጥ ለሥራቸው የማይመጥኑ መኖራቸው እየታወቀ፣ ምነው እኔ ብቻ ተነጥዬ ቦታህን ለሚችል ሰው ልቀቅ መባሌ፤ ብለው ይጠይቁ ይኾናል፡፡ ጥያቄያቸው የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ኾኖም ግን፣ በሀገራችን የቅርብ ታሪክ ውስጥ ለሀገርና ለወገን ሲሉ ቦታቸውን የለቀቁ እንዳሉ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚለው አስደማሚ መጽሐፋቸው ላይ ስለ ቦታ መልቀቅ የሚከተለውን ታሪክ ያጫውቱናል፡፡ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት፣ የአፍሪካን የግብርና ሚኒስትሮች በአጠቃላይ ወደ አሜሪካ መጥተው እንዲወያዩ የስብሰባ ጥሪ አቀረቡ፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ቢኾኑም ከሩዝቬልት ጋር ተገናኝቶ ስለ እርሻ ብቻ ሳይኾን እንግሊዞችን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማውረድ ትብብራቸውን እንዲለግሱ ለመጠየቅ ታስቦ ነበር፡፡ ለዚህ ሥራ ብቁ የሚኾኑት ከአቶ መኮንን ይልቅ አቶ ይልማ ደሬሳ መኾናቸውን አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ከወንድማቸው ከአቶ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ጋር ተመካክረው፣ ሐሳቡን ለጃንሆይ አቅርበው በማስወሰን አቶ ይልማ ደሬሳ ሔደው ከሩዝቬልት ጋር በመነጋገር፣ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡ ለ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች “ሐኪሞች በሌሉበት ምግብ አብሳዮች የጤና አማካሪ ኾነው ብቅ ይላሉ፡፡” (ፕሌቶ) ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” በሚለው መጽሐፉ፣ ከሙያቸው ውጭ ጣልቃ እየገቡ ችግር ስለሚፈጥሩ ሰዎች በሚከተለው ትረካ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ አልፎ አልፎ ትልቅ ግብዣ በሚካሔድበትና ተጋባዡ ቦታ ቦታውን ይዞ በሚታደመበት አዳራሽ ውስጥ ምግብ የሚያበስሉ ወጥ ቤቶች፣ እንግዶቹ ወዳሉበት ሥፍራ በመሔድ፣ ራሳቸውን እንደ ሕክምና ባለሞያ በመቁጠር የጤና አማካሪ ኾነው ይቀርባሉ፡፡ በመኾኑም ከጠረጴዛ ወደ ጠረጴዛ በመዞር “ይቺን ብትበላ ትስማማኻለች፤ ይኼኛውን ምግብ ብዙ አትድፈር፤ በተለይ ደግሞ ይህ ዐይነቱ ምግብ ለደም ብዛትና ለኩላሊት ፈውስ ነው፤” ወዘተ የሚል ምክር ይለግሳሉ፡፡ በእንዲህ ዐይነት ከሙያቸው የራቀ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉ ወደ ግብዣው ቦታ እውነተኞቹ ሐኪሞች ወይም ዶክተሮች ብቅ ሲሉ ወጥ ቤቶቹ ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡ የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች ሐኪም መስለው መቅረባቸው ጥፋተኛ ቢያሰኛቸውም እውነተኞቹ ሐኪሞች ሲመጡ ቦታውን ለቀው ወደ ማዕድ ቤት መመለሳቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ከዚህ ትረካ ስንነሣ የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ለተሻለ ሰው ቦታ መልቀቃቸውን እንገነዘባለን፡፡ ከሙያና ችሎታ ዉጭ ቦታን መያዝ በተመለከተ፣ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቁ የአሜሪካን ፈላስፋ ዊሊያም ጀምስ፣ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፤ “ለእኔ የተሰጠኝን አብዛኛውን የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ ባነበብኩ ጊዜ፣ ይህች ሀገር ስንት ገበሬ እንዳጣች ሳስብ አዝናለሁ፡፡” አሉ፡፡ እኔም የፕሬዝዳንት አድማሱን ኹኔታ ሳስብ፣ሰውዬው አለቦታቸው ሳይገቡ በሙያቸው ተሰማርተው፣ የጀመሩትን የግብርና ምርምር ቢቀጥሉ ኖሮ፣ ሀገሪቱ ከረኀብ ለመውጣትና በምግብ እህል ምርት ራሷን ለመቻል ታደርገዋለች ለሚባለው ተጋድሎ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖራቸው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፬ ማጠቃለያ ጹሑፋችንን የምናጠቃልለው በሚከተሉት ሁለት ጉዳዮች ዙርያ አጠር ያሉ ነጥቦችን በማንሣት ነው፡፡ እነዚህንም ነጥቦች “ዕውቀት” እና “እብሪት” በተሰኙ ሁለት አርእስት ከፍለን እናቀርባለን፡፡ ሀ. ዕውቀት የአንድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራር ለመኾን የሰውዬው ወይም የሴትዬዋ የዕውቀት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያለ መኾን አለበት፡፡ የዛሬ ኃምሳ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በምሁራኑ አካባቢ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሚኾን ሰው ምን ዐይነት መሥፈርት ማሟላት አለበት? አንድንስ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ብቁ የሚያሰኘው ነገር ምንድር ነው? ፕሬዝዳንትን ለመሠየም የሚያስችሉ ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያላቸውን መመዘኛዎች ማስቀመጥ ይቻላል ወይ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሣት፣ ረዘም ላሉ ጊዜያት ከተወያዩ በኋላ አምስት ወይም ስድስት መሥፈርቶችን ለይተው አወጡ፡፡ ከተስማሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ከኹሉም በላይ የተጠናከረ ምሁራዊ ዝንባሌና ርእይ ያለው መኾን እንዳለበት፤በኹለተኛ ደረጃ የአመራርና የአስተዳደር ችሎታ ያለው መኾን እንደሚገባው ካቀረቡ በኋላ ሌላው ነጥባቸው፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ባለትዳርና ቤተሰብ ያለው ቢኾን ይመረጣል የሚል ነው፡፡ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፤ የአሜሪካን ምሁራን ለፕሬዝዳንትነት አስፈላጊ ናቸው ብለው ከዘረዘሯቸው መሥፈርቶች ውስጥ፣ በእኔ አተያይ፣ ባለትዳር ቢኾን ይመረጣል ያሉትን መለኪያ ብቻ የሚያሟሉ ይመስለኛል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጠንካራ ምሁራዊና የአስተዳደር ክህሎት ስለሚጎድላቸው፣ ዩኒቨርስቲው የራሱን ዕቅድ ነድፎ፣ እንደ አንድ አካዳሚያዊ ተቋም ከመተግበር ይልቅ ከመንግሥት ሥራ እየተቆጠረ የሚሰጠው ኾኗል፡፡ ስለኾነም ፕሬዝዳንቱ ምንጊዜም የመንግሥትን ፖሊሲና ፕላን ወደ ዩኒቨርስቲ አምጥተው ማስፈጸም ስለሚፈልጉ፣ አኹን ባለበት ኹኔታ የጥናትና ምርምር ማእከል መኾኑ ቀርቶ፣ “ልማታዊ ዩኒቨርስቲ” ተብሎ እስከ መጠራት ደርሷል፡፡ እዚህ ጋ እንደ ማሳያ ለማቅረብ የምፈልገው፣ ከስድስት ወራት በፊት ጋዜጠኞችን ሰብስበው በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሲሰጡ፤ለዩኒቨርስቲው እንደ ርእይና እንደ ግብ አድርገው ካቀረቧቸው አንዱ፣ የበሬ ማድለብን ፕሮጀክት ነው፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚያስገርመው፣ አንድ ዩኒቨርስቲ በዋናነት የአእምሮ ማድለቢያ እንጂ የበሬ ማድለቢያ እንዳልኾነ ብዙ ሰዎች ያውቁታል፡፡ እርሳቸው ግን ይህን መሳታቸው ከግል ድክመት የመነጨ ሳይኾን ወደ እውነተኛ የሙያ ጥሪያቸው ከማዘንበል የተነሳ ነው፡፡ባለፉት አራት ዓመታት ያደረጓቸውን ንግግሮች ያዳመጠ ሰው ሊስተው የማይችለው ነገር ቢኖር፣ ፕሬዝዳንቱ ኹልጊዜም ሪፖርት አቅራቢ ኾነው መገኘታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ዩኒቨርሲቲው እንዴት ካለፉት ዓመታት ዘንድሮ የተማሪውን ቅበላ እንዳሳደገ፤ ምን ያህል ዐዲስ ሕንፃዎች እንደ ተሠሩ፤ ስንት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንደገቡ፤ ስንት ዐዲስ የትምህርት ክፍሎች እንደተከፈቱ… ወዘተርፈ በቁጥር ማቅረብ ነው፡፡ እንደዚህ ዐይነት ዘገባዎች፣ በዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ወይም በየትምህርት ክፍሉ ሊቀርብ ሲችል የፕሬዝዳንቱ ተቀዳሚ ሥራ ኾኖ መገኘቱ በእጅጉ አስገራሚ ነገር ነው፡፡ በመጨረሻም ፕሬዝዳንት ኾነው ባገለገሉባቸው ጥቂት ዓመታት፣ የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ እርሳቸው በሚቀርብበት ጊዜ ቶሎ ብሎ የሚቀናቸው፣ ጉዳዩ በኮሚቴ እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በኮሚቴ ማየቱ ተገቢ ቢኾንም የቀረበውን ጥያቄ ኹሉ ወደ ኮሚቴ ማስተላለፍ፣ በራስ ያለመተማመንና ሓላፊነትን ለመሸሽ የሚደረግ አዝማሚያ መስሎ ይታያል፡፡ ለማሳያ ያኽል፣ በቅርቡ የሪፖርተር ጋዜጠኛ፣ “የክብር ዶክትሬት ለመጠሪያነት ይውላል ወይ?” በሚል ለጠየቃቸው ሲመልሱ፤“በእኔ እምነት ይቻላል፤ ነገር ግን መጠራት ይቻላል ወይስ አይቻልም ለሚለው ጉዳይ የመጨረሻ ዕልባት ለመስጠት እንዲረዳ ኮሚቴ አቋቁመን እንዲወሰን እናደርጋለን፡፡” በማለት መልሰዋል፡፡ ለ. እብሪት እብሪት ብቻውን የሚከሠት ነገር አይደለም፡፡ ዕውቀት በሌለበት ቦታ፣ ንዋይ በበዛበት መንደር እብሪት መፈልፈሏና ማበቧ አይቀርም፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ያልኾነውን ነገር መኾን ሲከጅል፣በእብሪት አዙሪት ውስጥ ይወድቃል፡፡ ጥንታውያኑ የግሪክ ጸሐፍት እብሪትን ሲገልጹት፣ ከአማልክቱ ጋር ለመወዳደር መሻት ነው ይሉታል፡፡ ይህ ውድድር በመጨረሻም ለእብሪተኛው ውድቀት ይኾነዋል፡፡ የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እብሪቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት የታዩ ቢኾንም፤ በእኔ ላይ የደረሰውን እብሪታዊ ድርጊት እንደ ማሳያ ልጥቀስ፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በዩኒቨርስቲው ላስተማርኩበት የጠየቅኹት የሰባቲካል ፈቃድ ስለተነፈገኝ፣ ሥርዓቱንና ዕርከኑን ጠብቄ ቅሬታዬን ለፕሬዝዳንቱ አቀረብኩ፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ላስገባኹት በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች ያሉት አቤቱታ በማግስቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.፣ “በጥልቅ መርምረን እንዳረጋገጥነው፣ የኮሌጁ ውሳኔ የሚለወጥበት ምክንያት የለም” የሚል መልስ በቆራጣ ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡ የእብሪቱ ጫና ባይኖርና እንደ ደንቡ ቢኾን ኖሮ፣ ከትምህርት ክፍሉ ጀምሮ እስከ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ድረስ ያሉትን ሓላፊዎች እንዲኹም የሕግ አማካሪዎቻቸውን ሳያማክሩና በማስረጃነት ያቀረብኳቸውን ሰነዶች ሳይመረምሩ በሰዓታት ውስጥ ባልወሰኑ ነበር፡፡
Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s