ባዶ የምትመስል ሙሉ ሀገር

satenaw

ብሥራት ደረሰ (ከአዲስ አበባ) የሚገርም ነው፡፡ በኢሣት እየቀረበ ያለ አንድ ዝግጅት መከታተል ጀምሬ ነበር፡፡ እሱም ምንትስ ቪዥን የሚባል የኢትዮ-ኤርትራ ሰላማዊ ግንኙነት ላይ እየሠራ እንደሆነ የተነገረለት ድርጅት ያደረገውን ስብሰባ በሚመለከት ዶክተር ጌታቸው በጋሻው ድርጅቱን ወክለው ገለጣ የሚሰጡበት ነበር፡፡ በጉጉት ማዳመጤን መቀጠል ብፈልግም በርዕሴ የተቀመጠው ሃሳብ ድንገት በአእምሮየ ብልጭ አለና ለራሴም ባስደነቀኝ ሁኔታ ቱር ብዬ በመነሣት ወደ መጻፊያና ማንበቢያ ክፍሌ አመራሁ፡፡ ውስጤ ባንዳች ተስፋ መሞላቱ ይሰማኛል፤ ኢትዮጵያችን በአሁኑ ወቅት ባዶ ብትመስልም ሙሉ መሆኗን ማመን ለሚፈልግ ከማንም ባልተናነሰ የሙሉ ሙሉ እንደሆነች መጠቆም ወደድኩ፡፡ መልካም ንባብ፡፡ ካሳለፍነው የመከራ ዘመን አንጻር ይህ እምነቴ ውኃ የማያነሣና በባዶ ተስፋ የመሸንገል ያህል ቢቆጠርብኝ ብዙም አልከፋም – “ሚዜ ጫንቃ ላይ ካልወጣሁ መዳሬን አላምንም አለች ሙሽሪት” እያልንስ በምንተርት ሕዝብ መካከል በክፉዎች ተደጋጋሚ የተንኮል ሤራ ምክንያት የጠወለገን ተስፋ እንዲያንሠራራ ለማድረግ መሞከር የፈጣሪን እገዛ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ይሁንና ከሀገሮች ውድቀትና ትንሣኤ አኳያ ከተመለከትነው ርዕሴና እኔ ትክክል የማንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ማንም ይረዳዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ እናም ኢትዮጵያ ቀን ጥሏት ምንም ዓይነት የሞራልና የበጎ ሥነ ምግባር ተፈጥሮ በሌላቸው አረመኔዎች እጅ ብትወድቅም የብዙ ሀገሮች ዕጣ ከዚህ እኛ ላይ ከደረሰው ክፉ ዕጣ ባልተናነሰ እንደሚመሰቃቀልና በጊዜ ሂደት ግን ተመልሶ እንደሚስተካከል ሁሉ የኛም መጥፎ ዕጣ ቀኑን ጠብቆ እንደሚገፈፍና ታሪካዊ ሥፍራችንን እንደምንይዝ ጥርጥር የሌለው እውነት መሆኑን ላሳስብ እፈልጋለሁ፡፡ በውስጣዊም ይሁን በውጫዊ ምክንያቶች የተነሣ እስራኤል የምትባል ሀገር እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ እንደሀገር አልተበጀችም ነበር፡፡ ዜጎቿ በመላው ዓለም እንደጨው ዘር ተበታትነው ለሰው ሀገር ሲለፉና ሲደክሙ ኖረው ሲያበቁ የግዞት ሕይወታቸው ባከተመባት በዚያች ለነሱ የተቀደሰች ዓመት ውስጥ የዛሬ 67 ዓመታት ገደማ የራሳቸውን መንግሥት ዐወጁ፡፡ በመንግሥትነት ዕውቅና ከማግኘታቸውና አንድ መቶ ዓመት እንኳን ሳይሞሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የመንግሥትነት ኅልውና ካላቸው ሀገራት በበለጠ በሣይንስና ቴክኖሎጂ ወደፊት መጥቀው በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ዓለምን በመቆጣጠር ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደዚህ ደረጃ የደረሱት ግን በርግጥም የእነዚህ ስልሳና ሰባ ዓመታት የመንግሥትነት ዕድሜ የሰጣቸው ፀጋና በረከት ሳይሆን ዜጎቿ በየተሰደዱባቸው ሀገራት ዕውቀትና ልምድ ሲቀስሙ በመቆየታቸውና ከአንዳንድ መረጃዎች እንደምንገነዘበውም የአእምሯቸው የተለዬ ብሩኅነት ለሥልጣኔና ዕድገት ቅርበት እንዲኖራቸው በማስቻሉ እንደሆነ ውኃ ውኃ በሚያሰኝ በረሃ ላይ ሠፍረው ሲያበቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳዩት ያሉት ሁለንተናዊ ምጥቀት ግልጽ ማስረጃ ነው፡፡ በዚያም ላይ ሀገራቸውን ከምንም በላይ የሚወዱና በአንድነታቸው የማይደራደሩ፣ ጥቂትነታቸው የሚፈጥርባቸውን በሌሎች ያለመዋጥ የኅልውና ሥጋት ለመቋቋም ቀን ከሌት የሚተጉና በተጠራጣሪነታቸው የሚታወቁ፣ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ካልተቆጣጠሩ አለብን ብለው ከሚያስቡት የጠላት መንጋ አኳያ በቀላሉ እንጠፋለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውና የመሳሰሉት ምክንያቶች ለጥንካሬያቸው መነሻ እንደሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ከ“ምቀኛ”ው በበለጠ አደገኛና ዐረመኔ መሆኑ እንዳይከተል እንጂ “ምቀኛ አታሳጣኝ” ብሎ መጸለዩ አግባብ ሣይሆን አይቀርም፡፡ ክፉ ጎረበት ዕቃ ያስገዛል፡፡… መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያንን “እናንተስ ለኔ እንደኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”እንዳላቸው በጥቅስ ቁጥር በተደገፈ ማስረጃ የሚናገሩ አሉ፡፡ በዚህ አባባል የምንረዳው ቢያንስ እኛና እስራኤላውያን በፈጣሪ ዘንድ ቀዳሚውን ግርማ ሞገስ አግኝተን የምንታወስ መሆናችንንና በመከራችን ጊዜ ጥሎ የማይጥለን አምላክ ያለን መሆናችንን ነው፡፡ ከሺዎች ዓመታት የግዞትና የስደት ዘመን በኋላ በለሲቱ አቆጥቁጣና ለምልማ ሕዝቧን ከየዓለሙ ዳርቻ ስትሰበስብና ከእንዳልነበረችነት ወደ አሽቆጥቋጭነት መለወጧን በዘመናችን ባይናችን በብሌኑ እያየን የታሪክ ምሥክር ለመሆን በቅተናል፡፡ ወድቆ መነሣትን በእስራኤላውን፣ ተነስቶ መውደቅን ደግሞ በግሪክ፣ በኦቶማውንና በሮማውያን መንግሥታት እንረዳለን፡፡ የስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት እስራኤል በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን የሚገዙ በሥልጣኔም ባይሆን በፔትሮዶላር የኢኮኖሚ መሠረት ታላላቅ የሆኑ የዐረብ ሀገራት ስሟ ሲጠራ እንዴት እንደሚርበደበዱ አይተናል፤ እያየንም ነው – ተረቱም “ያለው ማማሩ” ነው፡፡ “በጌታዋ የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች” ብንልም ከእውነቱ ብዙም አንርቅም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ መሆን ስላለበት ነው እንጂ በሚሊዮንና በቢሊዮን መካከል ያለው አኀዛዊ ልዩነት ለእግዜሩም ለሰውም ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሁን ያለው አይቀርም፡፡ ጽንስ አለቀኑ አይወለድም፡፡ ቀን ዘመም ሲል አሽከር ጌታ፣ ጌታም አሽከር ይሆናል፡፡ ቀን ሲጎድል ላም በሬን አሸንፋ ገደል ልትከተው እንደምትችል ባናይ እንኳን ቢያንስ እንሰማለን፡፡ ቀንን ደግሞ ቀን ራሱ ያሸንፈዋል፡፡ ቀንን ያለቀን የሚያሸንፈው የለም፡፡ እንደታሪክ በሰው አላጋጭና አሽሟጣጭ የለም፡፡ በዚህ ህገ ወጥ የሚመስል ህጋዊ የተፈጥሮ ሂደት መገረምና እንደማሽላዋ እያረሩ መሣቅ ይቻል ይሆናል እንጂ ሂደቱን መለወጥ ግን ፈጽሞ መለወጥ አይቻልም – ብታርር ብትደብን ምንም አታመጣም፤ ጊዜው ሲደርስ ግን እነዚያኞቹ ቢያርሩ ቢደብኑ ምንም አያመጡም፡- “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” የሚባለው ትክክለኛ አባባል ነው፡፡ (እዚች ላይ ዘሃበሻዎች እባካችሁን ሰሞኑን በውቀቱ ሥዩም የኳላትን “ይደረጋል ሁሉም” የምትለዋን ‹ነጠላ መጣጥፍ› ለአንባቢያን ጋብዙልኝ – ማስወንጨፊያ ምናምን በምትሉት እዚቺው መስመር ላይ ጠቁሙልኝማ)፡፡ አውሮፓና አሜሪካም በዘመኑ ፍዳቸውን አይተዋል፡፡ ቁም ስቅላቸውን በልተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ እነጃፓንና ኮሪያ ከኢትዮጵያ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ተለግሶላቸዋል – ልብ እናድርግ ከኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ተደማጭ ነበረች፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ፕሬዚደንት ንጉሣችንን ለማንም ጥቁር የሀገር መሪ ባላደረገው መልክ የተለዬ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ የቀድሞ ንጉሣችን ናይጄሪያውያንን አስታርቀው አንዲት ሀገር አድርገዋል፤ የቀድሞ ንጉሣችን በጃማይካውያን እስከመመለክ ደርሰዋል – አሁንም ድረስ፡፡ ኢትዮጵያውያን የጠፈርና የሥነ ሕንፃ ተመራማሪዎች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን የሥነ ፈለክና የሥነ ከዋክብት ተመራማሪዎች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን አንቱ የተባሉ ፈላስፎችም ነበሩ፡፡ የአሁኑ ወያኔያዊ ማፈሪያ ታሪካችን ሲፋቅ ጎልቶ የሚታይ ብዙ የሚያኮራ ታሪክ አለን፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ግን ጊዜው ሆነና እንኳንስ የተጣላን ልናስታርቅና በሕዝቦችና በሀገሮች መካከል ሰላም ልናወርድ ይቅርና ራሳችንም ሰላም ርቆን በቆሌቢስ ሽፍቶች ከግንድና ከቋጥኝ ያለ አንዳች ዕረፍት እየተላጋን በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል፡፡ በነዚህ አዋራጅ የባንዳ ልጆች የማይም አገዛዝ ምክንያት ሀገራችንና እኛ ሕዝቡ ክፉኛ በመዋረዳችን ስማችን ጠፍቷል፤ ሚዛናችንም ቀሏል – ለምሥክርነትና ለዋስም የማንበቃ ቀትረ ቀላል ሆነናል፤ መስተደንግፀችን ተገፍፎ ማንም የዐረብ ጀማላ የሚጫወትብን አልባሌ ሆነናል፡፡ እኛ ስንጠራ የኩራታችን ምንጭ የነበረው አኩሪው ታሪካችን ሣይሆን ረሀብተኛነታችን፣ ኋላ ቀርነታችን፣ ለማኝነታችን፣ ተሰዳጅነታችን፣ ዐላዋቂነታችን፣ ምቀኝነታቻን፣ ራስ ወዳድነታችን … ፊታቸው ላይ እየተደቀነባቸው የሚጠሉን የዓለም ዜጎች ተበራክተዋል፡፡ ሀገራችን ውስጥ መብታችንን የሚያከብር መንግሥት ስለሌለን በየምንሄድባቸው ሀገሮችም – የዴሞክራሲ ሥርዓት ሠፍኖበታል በሚባል ሀገር ቢሆንም እንኳን – የቤቱን እያዩ የማያከብሩን ብዙዎች ናቸው፡፡ “ራቁቱን ለተወለደ ኩርማን (እርቦ?) ምን አነሰው” ከሚል ኢትዮጵያዊ ብሂል በመነሣት ይመስላል በሄድንበት ሀገር ሰብኣዊ መብታችን እንዲከበርልን ስንጠይቅ በሀገራችን ውስጥ ያለውን ዘግናኝ ሁኔታ የሚያውቁ ባዕዳን ያን ደጋግመው እያስታወሱን እንደቀበጥን ያህል በሾርኒ በመናገር ያላግጡብናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ውርደት በምግብ ብዛትም ሆነ በሀብት ክምችት የሚፋቅ ባለመሆኑ ዘወትር ኅሊናችንን ለሚጠዘጥዝ ቁስል ዳርጎን ይገኛል፡፡ መቼ ነው ከዚህ ዓይነቱ አዋራጅ ሕይወት የምላቀቀው? መቼስ ነው የምንከፋውና የምንናደደው? መቼ ነው ሀገራችን ናፍቃን ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና “ሆ!” ብለን የምንነሣው? የሀገራችን ጉዳይ ጥቂቶች ብቻ የሚንገበገቡለትና በተናጠል የሚሰውለት ሣይሆን የሁላችንም የሚሆነው መቼ ነው? “እኔም በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል፤ ስላገሬ ባይተዋር እንደሆንኩ በሰው ሀገር ጠፍቼ አልቀርም” ብለን ወደየኅሊናችን የምንመለሰው መቼ ነው? ልጆቻችን ቆንጆ ሀገር እንዳለቻቸው በኛ መስዋዕትነትና በመስዋዕትነታችንም ውጤት የምናሳያቸው መቼ ነው? እየተዘነጋን እንጂ ከእኛም ብዙ ይጠበቃል፡፡ …. ለማንኛውም ይህ ከፍ ሲል የጠቀስኩት የዘመኑ መጥፎ አሻራ በቅርብ የሚረግፍ ነው፡፡ ታያላችሁ በጣም በቅርብ አዲስ ታሪክ ይፈጠራል፡፡ አንድ ወንዝ ሄዶ ሄዶ የሚገባበት የበረሃ አሻዋም ይሁን ባሕር አለ፡፡ አንድ ዛፍ አድጎ አድጎ ለቤት መሥሪያም ይሁን ለማገዶነት ወይም ለቁሣ ቁስ መሥሪያ የሚቆረጥበት ወቅት አለ፡፡ … ሁሉም ነገር ዕድገቱን ይጨርሳል፡፡ ሲጨርስም ከነበርነት ወዳልነበርነት ይዛወራል፡፡ ወያኔም ይኼውና ወደመጨረሻው “የዕድገት” ጫፍ ደርሶ ጣር ላይ ይገኛል፡፡ (ሌኒንን አንዱ እንዲህ ብሎ ይመክረዋል፡- አንተ ሰው የዛሩን መንግሥት ቀላል አድርገኸዋል! ትልቅና ልትቋቋመው የማትችለውን ግምብ ልትጥል እየታገልክ እንደሆነ አይገባህም?… ብታርፍ ይሻልሃል፡፡ (“ዐርፈህ ልጆችህን አሳድግ” እንደምንባባለው፡፡) ሌኒንም አለው፡- እርግጥ ነው የዛሩ መንግሥት በግምብ ሊመሰል ይችላል – ነገር ግን ግምቡ እጅግ የበሰበሰ ከመሆኑ የተነሣ በቀላል ግፊ ወድቆ እንክትክቱ ይወጣል፡፡ የሆነው ሁሉ ሆነ …) ወያኔም እንደፀጉራም ውሻ በሕይወት ያለ እየመሰለ እንደእውነቱ ግን ሞቷል፡፡ ጽልመታዊ የታሪክ ባንክ ውስጥ ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ ካስቀመጠው ደራጎናዊ የክፋትና ጭካኔ ተቀማጭ ትንሽ ትንሽ እየመነዘረ አሁንም ኃይለኛና ብርቱ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራል እንጂ ብርታቱም ሆነ የኅልውና ዋና ቅመሙ ከመለስ ጋር ወደመቃብር ወርዷል፡፡ ግን ግን ግንቦት 8/81ዓ.ም የሞተው ደርግ ሥር ሰድዶ በነበረው የአስፈሪነት ጥላው ምክንያት በአጥንቱ ሲገዛ ቆይቶ በዚያው ሟርተኛ ወር ግንቦት 20/83ዓ.ም ግብዓተ መሬቱ እንደተፈጸመው ሁሉ ሐምሌ 7/2004 ዓ.ም ከመለስ ዜናዊ ጋር የሞተው ሕወሓትም ሰሚን ሣይቀር በፍርሀት በሚያርበደብድ የጭካኔ ተግባሩ ምክንያት መኖር ሳይገባው ደፋር በማጣቱ ግና ይሄውና በሕይወት ያለ መስሎ በድኑ ብቻ ይኖራል፡፡ እውነቱ ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ ዐረመኔነት የሚጠቅመው ለዚህ ነው – ሣትኖር ያኖርሃል፤ ተቀብረህ እንኳን ሕይወት አለህ – ታስፈራለህና፡፡ … ወደዋናው የተስፋየ ምንጭ ልግባ፡፡ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን በስደት ይኖራሉ፡፡ የትኞቹ በምን ሁኔታ የት እንደሚኖሩ ተጨባጭ መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ የየዘርፉ ምሁራን፣ ሣይንቲስቶች፣ መሃንዲሶች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ አርቲስቶች፣ ፈላስፎች፣… ቀን እስኪያልፍና ወደሀገራቸው እስኪገቡ አንገታቸውን ደፍተው የሰው ሀገር ባርያ ሆነው ይኖራሉ፡፡ በሀገር ውስጥ የሚገኘውን አብዛኛውን የይስሙላ “ምሁር”ና ከፊደል ሠራዊት ጋር የተጣላ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚያውደለድለውን አድርባይ ትተን በውጭ ያለውን ከአንጀቱ የሚማስነውን የተማረ ኃይል ስናስብ ሀገራዊ ተስፋችን ይለመልማል – እነዚህኞቹ ምሁራን እንደሀገር ቤቱ “ምሁራን” እንቀልድ ቢሉ በዚያ ያለው ዓለም አቀፍ ፉክክር የዋዛ አይደለምና ከሙያቸው ጋር ይቆራረጣሉ፤ የእንጀራ ገመዳቸውንም ይበጣጥሳሉ፡፡ በዚህ ቀልድ የለም፡፡ በዚያ ላይ በስም የማናውቃቸው ብዙ ሀብታሞች፣ ብዙ የነገር ብልት ዐዋቂዎች፣ ብዙ አስታራቂ ሽማግሌዎች … በየሀገሩ ተደብቀው ይኖራሉ፡፡ ዕድሜ ለመላኩ ተፈራ፣ ዕድሜ ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ዕድሜ ለመለስ ዜናዊና ለበሰበሰ የጥቁሮች አፓርታይድ ሥርዓቱ፣ ዕድሜ አሁን ሥልጣን ላይ ያለ ለሚመስለን ለዘረኛው የወያኔ ማፊያ ቡድን … በነዚህ የእፉኝት ልጆች ሕዝብን የማሳደድና የማጋዝ ሰይጣናዊ ተልእኮ ምክንያት ብዙ ዜጎቻችን በየሀገሩ ተበትነው ዕውቀትና ልምድ እየቀሰሙ ናቸው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን መሰደድና መጋዛቸውን እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥሬ “እንኳንስ ይህ ሆነ” ማለት ባልችልም ሀገርን የማፍረስና ሕዝብን የመበተን አደጋው የማያመልጡት ዕጣ መሆኑ እስካልቀረ ድረስ ሀገራችንን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኅዋን እንድትዋኝበት፣ ሕዝባችንም ከርሀብ አዙሪት ወጥቶ ከተመጽዋችነት ወደ መጽዋችነት የሚሸጋገርበት ወርቃማ ዘመን እንዲብት ሊያደርጉ የሚችሉ እጅግ በርካታ ዜጎች በየሀገሩ ዕውቀትና ልምድ እየቀሰሙ እንዳሉ ከግምት ባለፈ መረዳት እችላለሁ፡፡ ያ ነው ለኛ ትልቁ ተስፋ፡፡ ወገኖቼ! በፊዚክስ አንድ እውነት አለ፡፡ እሱም አንድን ነገር ተፈጥሮውን ትቀይረው ይሆናል እንጂ አታጠፋውም የሚለው ነው፡፡ ይቅርታ ወንድሞቼና እህቶቼ – አትቀየሙኝና አንዲት ጠያፍ የምትመስል ግን ቁም ነገር ያዘለች ብሂል ልናገር፡፡ አንዲት ሴት በጓደኞቿ መሀል ሳለች ድንገት የመጣባትን የፈሷን ድምፅ ልትቀንስና እንዳይሰማባት ለማድረግ ትሞክራለች አሉ፡፡ እንዲያ ስታደርግ ግና እንዲያውም ካሰበችው በላይ “ሽጉጧ” ይጮኽባታል፡፡ ያኔ “ውይ! መንግጌ አባስኩሽ?” ትልና አካባቢዋ የነበሩ ሰዎችን ይባስ አሳቀቻቸው ይባላል፡፡ የወያኔ ድርጊትም እንደዚሁ ነው፡፡ ሊያጠፋቸው በድርጅታዊ ማኒፌስቶውና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ሣይቀር ከመነሻው መግለጫና ዐዋጅ አውጥቶ ሲንቀሳቀስባቸው የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያዊ ኑባሬዎች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየጠፉ ያሉ ቢመስሉም በውጪ ግን ከምንጊዜውም በበለጠ እየገነኑ መጥተዋል፡፡ እዚህ የምታፍነው ነገር እዚያ መፈንዳቱ አይቀርም፡፡ እዚያ የምታምቀው ነገር ደግሞ እዚህ አፈትልኮ ይወጣል፡፡ ሞኝነት ነው እንጂ አንድን ነገር ማጥፋት ከባድ ነው፤ “እውነት ያርጋል እንጂ አይጠፋም” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ኃይለኛው ሂትለር ሞክሮ ያልተሣካለትን አንድን ዘር የማጥፋት ቅዠት እነዚህ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደንቆሮ የባንዳ ልጆች እውን ያደርጉታል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ መሞከራቸውና በተወሰነ ደረጃ በሀገር ውስጥ ሊሣካላቸው መቻሉን ግን አንክድም፡፡ ያም እግዚአብሔር የፈቀደው ስለሆነ እንጂ እያደረጉት ያለው ነገር ሁሉ በነዚህ ጥቂት ወሮበሎች አእምሮ ታስቦ፣ በነሱው ኃይል ወደ ተግባር ተተርጉሞ ሊታይ የሚችል ተዓምር ሆኖ አይደለም፡፡ መሆን ያለበት ነገር እንዲሆን ክፉ ነገር አድራጊዎች ክፉው ድርጊት በሚፈጸምባቸው ላይ እንዲነግሡና የተላኩበትን ድርጊት እንዳሻቸው እንዲፈጽሙ በቂ ጊዜና ሰፊ ዕድል ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፈተና በተፈጥሮው መንታ ተልእኮ ያለው ነው – አንድም የክፉ አድራጊው የክፋት መጠን እስከምን ሊደርስ እንደሚችል የሚለካበት ሲሆን አንድም ደግሞ ክፋቱ የሚፈጸምበት አካል ግፍና በደልን የመቋቋም አቅሙ እስከምን ድረስ እንደሆነ የሚፈተሸበትና በኋላ ደግሞ በቀኝ ኋላ ዙር ጊዜ ሁሉም የየሥራውን የሚያገኝበትና የተፈጥሮና የፈጣሪ ዳኝነት የሚገለጸበት ዑደታዊ እውነት ነው፡፡ በዚህ ቀመር ውስጥ የክፋት ፈጻሚና የክፋት ሥራ ተቀባይ ወገኖች የብዛት ተመጣጥኖ(ሬሽዎ) ከቁብ ሊጣፍ የሚችል አይመስለኝም፡፡ አንደኛው ወገን መነቃቃትንና እንደቀትር እባብ መወራጨትን ሲታደል ሌላኛው ወገን ድበታንና ጥልቅ እንቅልፍን “ይታደላል”፡፡ ይህ አንደርባዊ አፍዝ አደንግዝ ሲገፈፍ ግን የብድራቱ ክፍያ መጠን እጅግ ዘግናኝ ነው የሚሆነው፡፡ መጠንቀቅ ታዲያ ያኔ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው “እዩኝ እዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል” የሚባለው፡፡ ሁሉም ነገር የወር ተራ ጉዳይ ነው፡፡ የሌሊት ፈረቃ ሠራተኛ ቀን ይተኛል፤ የቀንም ሌሊት፡፡ ምን አዲስ ነገር አለ? ሶሎሞንም እኮ ያኔ ዱሮ ጨርሶታል – የመትከያ ጊዜ አለ – የመንቀያ ጊዜ አለ፤ የልደት ጊዜ አለ – የሞት ጊዜ አለ፡፡ ችግራችን ድንቁርናችን ነው፡፡ ችግራችን በኛ ሠፈር የወጣችው ፀሐይ በሌሎች ሠፈሮች ፈጽሞውን ልትወጣ እንደማትችል ማመናችን ነው፡፡ ትልቅ ቂልነት፡፡ ይህን ዛቻ አይሉት “ትንቢት” የምናገረው በዚህ ወይ በዚያ አቅጣጫ አስፈሪ ፀረ-ወያኔ ጦር አይቼ አይደለም – በጭራሽ፡፡ እርግጥ ነው በጦር ለሚያምን ወያኔን የሚመስል በጡንቻ የሚያስብ ፍጡር አባባሌን ከቀልድ አያሳልፈውም፡፡ ይሁንና ጋዳፊ በእንትኑ ሣንጃ እስኪወደወድበትና ነፍሱ ከሥጋው እስክትለይ ድረስ የሊቢያ ፕሬዝደንት የሆነ ያህል ይቆጥር ነበር፡፡ ኒኮላይ ቻውቼስኮ ከነሚስቱ በእቶን ሲጋይ የሮማንያ መሪ እንደሆነ ያህል ይሰማው ነበር፡፡ ሣዳም ሁሴን በካቦ ሲንጠለጠል የኢራቅ መሪ እንደሆነ ሳያምን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ያ ጨካኝና ሥልጣኑን ከኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ አስበልጦ ይመለከት የነበረው መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሁሉ ነገር ከድቶት – የሀገሪቱ ንፋስ እንኳን እርሱ ከሄደ በኋላ በደስታ ሲፈነጥዝ ታዝበናል – ጅራቱን ወትፎ ሀገሪቷንና ሕዝቡንም ለ“ወምበዴው አምበል” አስረክቦ ሲኮበልል የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት እንደሆነ ሳያስብ አይቀርም፡፡… አምባገነኖች የመጨረሻ ዕጣቸውን አስቀድመው ሊረዱና ሊጠነቀቁ አይሞክሩም፡፡ የሚገርመው ነገሩ ደርሶባቸው እያዩትም ማመን አይፈልጉም፡፡ ከዚህ አኳያ ብልጡ የቱኒዚያው የቀድሞ መሪ ቤን አሊ ሳይሻል አይቀርም – አያያዙን አይቶ ቀድሞ ሹልክ አለና ሕይወቱን አተረፈ፤ የሕዝብ ዕልቂት እንዳይከተልም ዘየደ፡፡ አላህ ይባርከው፡፡ የኞቹ ግን እንጃላቸው፡፡ ጌቶቻችን ብዙ ናቸውና ሁኔታው አልሆን ሲላቸው ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ለማምለጥ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ግን ደም መጥፎ ነው፤ ደም ከሰንሰለት የጠነከረ አሣሪ መሆኑን የነለገሠ አስፋውንና መላኩ ተፈራን እየተርመጠመጡ በወያኔ መያዝ ማስታወስ ብቻውን በቂ ነው፡፡ እንደደም ቀያጅ ገመድ የለም፡፡ በነገራችን ላይ የዶክተር መሣይ ከበደን ወላዋይና ብዙም ትርጉም የማይሰጥ አቋም ሀገር ቤት ያለን ኢሣትን የምንመለከት ወገኖች እየተከታተልንና እየተቸነውም ነው፡፡ ከጓደኞች ጋር ስንነጋገር የዶክተሩ በአንድ በኩል ለወያኔ የይቅርታና የምሕረት እጅን ስለመዘርጋት በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔን በምርጫ ሣይሆን በጡጫ የማስወገዱን አስፈላጊነት ከአንደበታቸው ስንሰማ ግራ ተጋብተናል፡፡ ዶክተር መሣይ የሚሉት “ወያኔን መወንጀል የለብንም፤ ሙሉ ይቅርታም ማድረግ አለብን፤ (በዘረፋ ያገኙትን) ሀብት ንብረታቸውንም መንካት አይኖርብንም፤ ሥልጣንም ተጋርተን ሀገሪቱን በጋርዮሽ ማስተዳደር አለብን…” ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ወያኔን በኃይል ካልሆነ በምርጫ አናሸንፈውም ብሎ ከሚያምን አንድ ምሁር “ጠላትን በኃይል አንበርክከን የያዘውን ሥልጣን ከተረከብን በኋላ እንደገና ለሥልጣን ጋብዘን የሠራውንም ወንጀል ሁሉ እንዳልሠራ በመቁጠር ይቅር ብለነው ስናበቃ ከሀገርና ከሕዝብ በዘረፋና በሙስና ያካበተውን ሀብትና ንብረት ሳንነካበት እየተንደላቀቀ ይኑር” ብሎ በሕዝብ ቁስል እንጨት መስደድ ምን ይባላል? ይህ ዓይነቱ የፍትህ ሥርዓትና የፍርድ ሂደትስ የገነት ነው ወይንስ የገሃነም? ሰዎቹ አስቀድመው የሰው ዕልቂትና የሀብትና የንብረት ውድመት እንዳይከሰት በማሰብ በራሳቸው ተነሳሽነት ምሕረትና ይቅርታ ቢጠይቁ ያን ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሕዝብ ከሚመረጥ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ይሆናል – እንዲህ ዓይነት “ቅብጠት” ደግሞ ወያኔን ሲያልፍ አይነካውም፡፡ የጭንቅ ቀን ሲመጣ ሕዝቡን እርስ በርስ አጨራርሰውና እንደአይሲስ ብዙ ነገር አውድመው ይጠፋሉ እንጂ ወያኔዎች በተፈጥሯቸው እነሱ የማይቆጣጠሩትና የማያሸንፉበት ድርድር ውስጥ በጭራሽ እንደማይገቡ እንኳንስ እኛ ጥንት ያኔ ሲጸነሱ በቤታቸው ጣሪያ ላይ የነበረው የሣጥናኤል ልዑክ ጠማማው ኮከብም ያውቃል፡፡ በወያኔና በኢትዮጵያ – በወያኔያውያንና በኢትዮጵያውያን – መካከል ያለው ቁርሾና ቅራኔ በድርድር ሣይሆን በደም ነው የሚፈታው – ይህ “ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ ትጠልቃለች” ዓይነት ዘመን የማይሽረው አጠቃላይ እውነት ነው፡፡ ወያኔ ለኢትዮጵያውያን ጆሮ እንዲሰጥ ከተፈለገ በአዲስ ደምና ሥጋ እንደገና መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ባለኝ ነገር ሁሉ መወራረድ እችላለሁ – አይቻልም እንጂ ቢቻል በነፍሴም ጭምር – ወያኔ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ካለው ጥላቻና ቂም በቀል በመነሣት መናገር የምንችለው ብቸኛ ነገር ቢኖር ቀንደኛ ወያኔዎች ወይም ሀገርና ሕዝብ ወዳድ ኢትዮጵያውያን – ከሁለት አንደኛቸው ከምድረ ገጽ ካልጠፉ በስተቀር በነዚህ ሁለት ተጻራሪ ኃይላት መካከል ያለው ቅራኔ በፍጹም አይፈታም፡፡ እሳትና ቤንዚን ኅብረት የላቸውም፤ ዐይንና ናጫ ፍቅር ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ ዐይጥና ድመት ተጫጭተው ጋብቻ አይመሠርቱም – ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውምና፡፡ የማይሆን ነገር እንዲሆን መጠበቅ ደግሞ የዋህነት ብቻ ሣይሆን ጅልነትም ነው፡፡ ወያኔና ኢትዮጵያ በጊዜ ሂደትና በተሞክሮ ሊስማሙ ቢችሉ ኖሮ ሩብ ምዕተ ዓመት ከበቂ በላይ ነበር – ግን አይሆንም፡፡ ከመነሻው የእነዚህ ሁለት ተፃራሪ ኃይላት ዕርቅም ሆነ ጠብ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ጥላ ሥር ቢሆን ኖሮ መሸናነፋቸው ትርጉም ያለው ሊሆን በቻለ ነበር – የኛ ሁኔታ የተለዬ ነው፤ መፍትሔውም እንደዚሁ የተለዬ ነው፡፡ ወያኔን በኃይል ከሥልጣን አስወግዶ ከወያኔ ጋር እንደገና መደራደር ግና ከመፍትሔው መዝገብ ውስጥ በጭራሽ አይካተትም፡፡ እንዴት ተደርጎ? ለዚህ ለዚህማ ትግል ለምን ያስልጋል? የወያኔ ዋና ዓላማ ማፍረስና ማፍረስ ብቻ ስለሆነ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ዕርቅ የለውም – አይሲስ የሚባለው የመካከለኛው ምሥራቅ ጉግማንጉግ ከማን ጋር ሊታረቅ ይችላል? ስለዚህ ወያኔን በጦር ካወረዱ በኋላ ከወያኔ ጋር ድርድር መቀመጥና በወንጀሉ እንዳይጠየቅ መስበክም ሆነ ጥብቅና መቆም በትንሹ የዋህነት ነው – ዶክተር መሣይና ሌሎች መሣያውን የሚሰሙኝ ከሆነ ማለቴ ነው፤ በ40 ዓመታት ውስጥ ወያኔን ማወቅ አለመቻል ከምንም በላይ የሚያሣዝን ጉዳይ ነው፤ ወያኔን ከሚናገረውና ከሚያደርገው በላይ የተለዬ ተፈጥሮ የሚሰጡ ሰዎች በሞኝነታቸው ያሣዝኑኛል፡፡ ለነገሩ “እሳቸው በመጡና ድንጋይ በበሉ” እንዳለችው ነው፡፡ ነፃነቱ ይምጣና ያኔ የሚደረስበት ይሆናል፡፡ እንዲያው ለማለት ያህል ግን እንዲህ አልን – ገና ብዙ እንልም ይሆናል፡፡ ለማንኛውም በኃላፊነት የማያስጠይቅ መጥፎ ሥራ ሊኖር አይገባም፡፡ አስተማሪነትም የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር በትግርኛ “ዝአኽለን ጥህነን በዓል ማርያም ትብላ” እንደሚባለው ነው – “የሚበቃትን ያህል ከፈጨች በኋላ ‹ውይ! ለካንስ የማርያም በዓል ነው› ትላለች” ለማለት ነው፡፡ አዎ፣ እኔ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ትለመልማለች፡፡ ጊዜው ሲደርስ ጠላቶቿ መፈጠራቸውን ይራገማሉ፡፡ በኃጢኣታችን ምክንያት ባዶ ቀፎውን ቀርቶ በነፃና ሳያስቡት ቤተ መንግሥታችንን የያዙት እነዚህ የታሪክ አራሙቻዎች በቅርብ ይወገዳሉ – ፈጣሪ ቁና መስፋቱን ዘንግቶ አያውቅም፤ አሁንም እየሰፋ ነው፡፡ ጠንቃቸው ግን ያስፈራል፡፡ እንደኔ የዚህ ጠንቅ ጦስ ለትግራይ ክፍለ ሀገር ይተርፋል ብዬ ስለማስብና ስለማምንም ከትግራይ መሬት ብዙ ይጠበቃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በነፃነቱ ትግል የትግራውያን ተሣትፎ የጎላ ቢሆን ደስታዬ ወሰን የለውም፡፡ ወያኔዎችን የሚያስወግደው በአመዛኙ የትግራይ ሕዝብ ቢሆን ለቀሪው ሕዝብ እንደትልቅ ካሣ ሊቆጠር ስለሚችል ብዙ ንቃቃትን ይጠግናል፡፡ በል ያለኝን አልኩ፡፡ ሰው ነኝና አጠፋለሁ – በተለይ ሳላውቅ፡፡ ይቅርታ ግን እጠይቃለሁ፡፡ እናም ባጠፋሁ ይቅርታ፡፡ ቸር ያሰንብተን፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s