ጊዜዉ መተባበርን እና መናበብን የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን – ነፃነት በለጠ

tumblr_inline_n407i5d6ch1qersu1

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መነሻነት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደርች መፈናቀላቸዉን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሁለተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አማካኝነት የተነሳዉ ተቃዉሞ መጠኑ እየጨመረ እና ተቃዉሞዉ እየተጠናከረ በመካሄድ ላይ ነዉ፡፡ ይህንን ተቃዉሞ ለማዳፈን የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ያሉት የሃይል እርምጃ ጭካኔ የተሞላበትና ለድብደባ፣ ለግርፋት፣ ለስቃይ እና ለግድያ የዳረገ ነዉ፡፡

ህወሃት (ወያኔ) ገና ከምስረታዉ ጀምሮ የጨነገፈ እና የዲሞክራሲ ባሕርይ ያልነበረዉ ድርጅት ለሥልጣን ሲበቃ ከዚህ ባሕርይዉ ሳይላቀቅ ላለፉት 24 ዓመታት በዜጎች ላይ ግፍና በደል እየፈፀመ ይገኛል፡፡ በዚህ ሰሞን እየተቀጣጠለ ያለዉን የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃዉሞ የኃይል ርምጃ በመዉሰድ ለመከላከል ቢሞክርም እንዲያዉም የተቃዉሞዉ አድማስ እየሰፋ እና እያደገ ሊሄድ ችሏል፡፡ የወያኔ መንግስት እያደረሰ ያለዉ በደል በሁሉም ክልሎች ባሉ ኢትዮጲያዉያን ላይ እየደረሰ ያለ እንጂ የተወሰኑ አካባቢዎችን ብቻ የሚሸፍን አይደለም፡፡ የግፍ አገዛዙ ያስከተለዉ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ቀዉስ ከዳር እሰከዳር ያዳረሰ ጉዳይ ነዉ፡፡

ይህ በጎሳ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዐት ያስከተለዉ መዘዝ እርስ በርሳችን እንዳንግባበ፣ በጎሳችንን ማንነት ዉስጥ ብቻ ተደብቀን ሀገራዊ ስሜት እንዳይኖረን በመደረግ ላይ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ፡፡ ስለሆነም አሁን በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ እየተካሄደ ያለዉን ተቃዉሞ ሰርዐቱ ለነደፈዉ የጎሳ ፖሊቲካ የተመቻችን በመሆናችን በኦሮሚያ እና በጎንደር እየተካሄደ ያለዉን ተቃዉሞ የኛም ተቃዉሞ ነዉ በማለት ድጋፍ ስንሰጥ ብዙም አይታይም፡፡ ለወያኔ መሰሪ ስራ ተመቻችተናል ማለት ነዉ፡፡ በወያኔ ካምፕ የሚፈለገዉ ይህ እርስ በርስ አለመናነበብ፣ አለመተባበር መሆኑ እየተረጨ ላለዉ በጎሳ እና በሃይማኖት የመከፋፈል እስትራቴጅ ራሳችን አዘጋጅተን የወያኔን የስልጣን እና የግፍ አገዛዝ ዕድሜ እያራዘምን ነዉ ማለት ነዉ፡፡

የኦሮሚያ ተማሪዎችና በጎንደር ያለዉን ተቃዉሞ የእኛም ተቃዉሞ መሆን ስለአለበት በምንችለዉ መንገድ አጋርነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ ይህ የአዲስ አበባ ማስፋፈያ ማስተር ፕላን ያስነሳዉ ተቃዉሞ ሰብብ እንጂ ዋናዉ ምክንያታችን ለላፉት 24 ዓመታት በዲሞክራሲ ጭምብል የወያኔ መንግሰት እየፈፀመ ያለዉ ማለቂያ የሌለዉ ጭቆና ድምር ዉጤት ነዉ፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ተማሪዎች እና የጎንደር ህዝብ የመረረ ተቃዉሞ የሁላችንም ተቃዉሞ ስለሆነ ከጎናቸዉ በመሆን ትግላቸዉን ልናጠናክር ይገባል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን የበዛ ጥፋት፤ እንግልት እና መበታተን ሊያስከትልብን ይችላል፡፡ ለመጥቀስ ያህል ለወያኔ ከፋፈልለህ ግዛዉ ፖሊሲ የተመቻቸን እንሆናለን፣ ቀጥሎም በህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፣ በተጨማሪም በጋራ የኢትዮጲያን ብሄራዊ አንድነት ለማስጠበቅ በሚደረገዉ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ጋሬጣ እንሆናለን ፡፡ አልፎም ለኢትዮጲያ የዉጭ ጠላቶች በቀላሉ እንጋለጣለን፡፡ ስለዚህ ወቅቱ መተባበርን፣ እርስ በርስ መደጋገፍን የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን፡፡ የወያኔ አገዛዝ ዕድሜዉ እያጠረ መሆኑን የተለያዩ ምልከቶች ተጠናክረዉ እየታዩ ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጲያዊ ለሐገራችን መፃኢ ዕድል መቃናት፣ የተሻለች እና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን ለመመስረት የበኩሉን አስተዋፅዎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን የህዝብ ትብብር ዕዉን እንዲሆን የሚከተሉት ማህበራዊ ኃይሎች ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለተቃዋሚ ኃይሎች

የተቃሚዉ ክፍል በራሱ ዉስጣዊ እና ዉጫዊ ምክንያቶች በመነጩ ችግሮች ተተብትቦም ቢሆን  የራሱን ድርሻ ለመወጣት በመንገዳገድ ላይ ይገኛል፡፡ ወያኔ በመሰሪ ተግባሩ የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት ትርምስ በመፍጠር ለሁለት እንዲከፈሉ በማድረግ ጠንካራ ናቸዉ የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተዳክመዉ እና መኖራቸዉ የሚረሳበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ብቻ ድምፃቸዉ የሚሰማዉ አንዳንድ አደርባይ ተቀዋሚዎች ለዚህ የፖሊቲካ ሴራ ድርሻቸዉን በመወጣት አስከአሁን ዘልቀዋል፡፡ አሁንም በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ  እየተካሄደ ያለዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ አስከአሁን ባለኝ መረጃ የሰማያዊ ፓርቲ ካወጣዉ የተቃዉሞ መግለጫ በስተቀር ሌሎቹ ድምፃቸዉ እየተሰማ አይደለም፡፡ ጊዜዉ ተቀናጅተን የተጀመረዉን ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አድማሱ እየሰፋ እንዲሄድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ሰፊ ሚና ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወያኔን ለማንበርከክ ለወያኔ ምቹ የሆነዉን እርስ በርስ መናቆር እና መናናቅ ጥለን በጋራ መንፈሰ ስንፋለም ነዉ ጨለማዉ ተገፎ የተሻለች ኢትዮጲያን እዉን ማድረግ የሚቻለዉ፡፡ ልዩነትን አቻችሎ በመተባበር የእግር እሳት የሆነብንን አምባገናነዊ መንግሰት በጋራ ከስሩ ስንመነግለዉ ነዉ ኢትዮጲያ ወደተሻለ የታሪክ ምዕራፍ የምትሸጋገረዉ፡፡ ስለዚህ የተቀዋሚዉ ጎራ ህዝብን በማሰባሰብ ወደ ተጠናከረ ትግል ማሸጋገር ይጠበቅበታል፡፡

ለመከላከያ፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለልዩ ኃይል እና ለፖሊስ አባላት

በኦሮሚያ እና በጎንደር የተቀጣጠለዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በአለቆቻችሁ ታዛችሁ የምትፈፅሙት ግድያ፣ ድብደባ፣ ግርፋት እና ማሰቃየት በገዛ ወገናችሁ ላይ መሆኑን ዘንግታችሁታል ማለት አይቻልም፡፡ የሌሎች ሃገር የፀጥታ ኃይሎች የጉዞ መንገድ በመከልከል፣ ዉሃ በመርጨት፣ ዙሪያ ከቦ እንዲቀመጡ ማድረግ፣ ከፋ ከተባለ አስለቃሽ ጢስ በመጠቀም ተቃዉሞን ለማብረድ ይሞከራሉ፡፡ ነግ ግን ከአብራኩ ወጥታችሁ የገዛ ወንድሞቻችሁን እና እህቶቻችሁን በአጠቃላይ ወገናችሁን ርህራሄ በጎደለዉ መንገድ የምትፈፅሙት ተግባር ታሪክ ይቅር የማይለዉ ነዉ፡፡

ከመካከላችሁ ከጥቂቶቹ ተጠቃሚ ክፍሎች በስተቀር እናንተ የበይ ተመልካች እንጂ ድህነቱ እና በኑሮ መንገላታቱ በእናንተም እየደረሰ ያለ ነዉ፡፡ ስለሆነም የወያኔን ዕድሜ ከማራዘም እና ወገናችሁን ለስቃይ ከመዳረግ በመቆጠብ የወገን አጋርነታችሁን በተለያየ መልኩ መግለፅ ይጠበቅባችኃል፡፡ አፈሙዙን ወደ ስርዐቱ ላይ በማዞር የወያኔን ዕድሜ በማሳጠሩ ትግል የበኩላችሁን ደርሻ መወጣት ይጠበቅባችኃል፡፡

ለኃይማኖት መሪዎች

በሰላማዊ መንገድ ለተቃዉሞ የወጡ ወጣቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያልተመጣጠነ የኃይል ርምጃ ሲወሰድ እና የሰዉ ልጅ ነፍስ ሲጠፋ እናንተ ዝምታን መምረጣችሁ ምን ይባላል? ተገቢስ ነዉ? ለእዉነት በመቆም፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ሲፈፀም በግንባር ቀደምትነት ቤዛ መሆን የሚጠበቀዉ ከእናንተ ከኃይማኖት መሪዎች ነበር፡፡ በብዙ መንገድ ከስርዐቱ ጋር ላለመላተም አይታችሁ እንዳላያችሁ አልፎም ለስርዐቱ አገልጋይ በመሆን መስለፍን የመረጡ የኃይማኖት መሪዎች በመካከላችሁ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በኦሮሚያ በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ ያለዉን እንቅስቃሴ ለመግታት የመንግሰት የፀጥታ ኃይሎች በምላሹ እየወሰዱት ያለዉ የሃይል ርምጃ በማዉገዝ መንግሰት ከዚህ አሳፋሪ ተግባሩ እንዲታቀብ ማሳሰብ እና ማስጠንቀቅ ይጠበቅባችሁ ነበር፡፡ ግን ምንም የተፈጠረ ስለማይመስለን ለወገኖቻችን ያለን ተቆርቋሪነት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ ነዉ፡፡ አሁንም ጊዜዉ ስላልረፈደ ሁሉም እምነቶች መከፋፈልን የሚሰበኩ ባለመሆኑ ተከታዮቻችሁን በዘር እና በኃይማኖት መከፋፈልን ትተዉ እንዲተባበሩ የራሳችሁን ድርሻ ልትወጡ ግድ ይላል፡፡

ለዲያስፖራ ኮሚኒቲ

በሀገራችን ዉስጥ ያለዉ የዘር ፖሊቲካ ያመጣዉ ጣጣ ለእናንተም ተርፎ በእናንተ ካምፕ ዉስጥ ያለዉን መቆራቆስ ከተለያዩ መረጃዎች እንከታተላለን፡፡ በልማት የተሻለ ደረጃ ባሉ ሀገሮች እየኖራችሁ እና የሰለጠነዉ ዓለም በመተባበር እየሰሩ ያሉትን ነገር እያሰተዋላችሁ የምትገኙ ዲያስፖራዎች የሀገራችንን ሰዎች እንዲተባበር እና ልዩነትን እንዳያራግብ ታስተምራላቸሁ ሲባል ወደ መንደር ደረጃ ወርዳችሁ እርስ በርስ ስትናቆሩ መስማት ለእኛ በሀገር ቤት ላለን ምን ያህል እንደሚያመን ልትገነዘቡት ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም መሬት ላይ ያለዉ ዕዉነታ ግን ለወያኔ መሰሪ ፖለቲካ ተመቻችታችሁ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር ችግሮቻችሁን ከመፍታት ይልቅ ጎራ ለይታችሁ በመናቆራችሁ በሀገር ቤት ላለዉ የፀረ-ወያኔ ትግል መሳሪያ በመሆን እያገለገላችሁ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ ወያኔን ማንበረክክ የሚቻለዉ ስንተባበር ነዉ፡፡ ሰለዚህ በኦሮሚያ እና በጎንደር የተጀመረዉን ትግል ባላችሁበት ቦታ የትግል አጋርነታችሁን መግለፅ ይጠበቅባችኃል፡፡ ላላችሁበት መንግስት እየተፈፀመ ያለዉን ግድያ፣ ድብደባ እና ማሰቃየት እንዲሁም በደርቅ ሳቢያ የተከሰተዉን የከፋ የረሃብ አደጋ ለአለም ህብረተሰብ ልታሳወቁ ይገባል፡፡ ለመንግስታት መሪዎች በአገራችን ያለዉን መከራና ግፍ በማስገነዘብ በኩል ድርሻችሁ የላቀ ነዉ፡፡

በመጨረሻም እናንተ ለእኛ አርአያ በመሆን ያለባችሁን የፖለቲካ ልዩነት በመነጋገር፣ ልዩነቶቻችሁ የማይታረቁ ከሆነ በሚያግባባችሁ በጋራ በመስራት እዉነተኛ እና ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን ለመመስረት የሚደረገዉን እልህ አስጨራሽ ትግል በማገዝ የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል፡፡ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት መለያየት ጠላትነትን አያሳይም፡፡ ከዘር ብሔረተኝነት ወጥተን የህዝቦች እኩልነት እና ነፃነት የተከበረባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን በመመስረት ወደ ገበያ ብሔረተኝነት እንድንሸጋገር የእናንተ ሚና ሊናቅ አይችልም፡፡ እናንተም ለኢትዮጲያ ባለድርሻ ናቸሁና፡፡

ማጠቃለያ

ወያኔ / ኢህአዴግ የሚመራዉ ሰርዐት ኢትዮጲያን ያዋረደ፣ የዘር ፖሊቲካን የፖሊቲካ ሰርዐቱ ዋና ምስሶ በማድረግ ልብ ለልብ እንዳንገኛ ተግቶ እየሰራ ያለ እና ኢኮኖሚዉ በ11 ፐርሰንት አደገ በማለት በዘረፋ ለተሰማሩት ጥቂት የህብረሰተብ ክፍሎች ያመቻቸ እና ህዝቡን ግን ወደከፋ ድህነት የከተተ አስነዋሪ ስርዐት ነዉ፡፡ ይህ ግፈኛ ስርዐት በተቃዉሞ የሚመጣን ማንንም ክፍል በጉልበት ለማዳከምና ለማንበርከክ የሚሞከር አሁንም በጫካ ህግ እየተመራ ያለ መንግሰት ነዉ፡፡ ከዚሁ ጎን በሎሌነት ያሰለፋቸዉ ሆድ አደር ባለስልጣናት የዚሁ የክፋት ስራ ተባባሪ በመሆን ጌቶቻቸዉን ለማስደሰት አደርጉ የተባሉትን በመፈፀም እና ጥቅማቸዉ እንዲቀጥል በማድረግ ስርዐቱ ዕድሜዉ እንዲራዝም የሚቻላቸዉን ያህል እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኦሮሚያ  ባለስልጣናት በክልሉ ወጣቶች ላይ ወያኔን ለማስደሰት እየወሰዳችሁት ያለዉ ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ጊዜ ይወስዳል እንጂ የኢትዮጲያ ህዝብ እንደሚፋረዳቸሁ መጠራጠር የለባችሁም፡፡ ሆኖም ህዝብ ተባብሮ ከተነሳ የሚገታዉ አንዳችም ኃይል እንደሌለ በዓለም የተፈፀሙ የህዝባዊ መነሳሳቶች እና አብዮቶች ታሪክ ያስተምሩናል፡፡

የኢትዮጲያ ህዝብ ሆይ!! በኦሮሚያ፣ በጎንደር እና በሌሎችም አካባቢ እየተቀጣጠለ ያለዉን ህዝባዊ ተቃዉሞ በመደገፍ ሁላችንም ያለብንን የዜግነት ኃላፊነት ልንወጣ ጊዜዉ ይጠይቀናል፡፡

በህብረት እንነሳ !!!

ድል ለኢትዮጲያ ህዝብ !!!

ኢትዮጲያ በነፃነት፣ በሠላም እና በህብረት ለዘላለም ትኑር !!!

እግዚአብሔር ኢትዮጲያን ይጠብቅ !!!

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s