ህዝቡን ስሙት…. መግለጫ ይቁም…. ውጥረቱን አርግቡት”

Tenesu

አንደኛ፡
በቀላልና በማያሻማ መንገድ “ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል” ማለት አይቻልንምን…? በደንብ ይቻላል፡፡ ነገሮች እንዲህ ከመወጣጠራቸው በፊት መንግሥት ይህንኑ ቃል ቢናገር ህዝቡ “በጄ” ይለው ነበር፡፡ መንግሥትም ዘወትር የሚወቀስበትን “ህዝብን ያለማዳመጥ ችግር” ለመቅረፍ ጥርጊያ ጎዳናውን ያመቻችለት ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን ለማድረግ አልተፈቀደም፡፡ በዚህ ፋንታ ልዩ ልዩ ባለስልጣኖች ወደ ሚዲያ እየቀረቡ “ማስተር ፕላኑ ህዝብ ሳይመክርበትና ሳይነጋገርበት ወደ ትግበራ ደረጃ አይገባም” ማለትን ነው የመረጡት፡፡ ይህንን ማለቱ ለምን አስፈለገ?..… ይህ እኮ በሌላ ቋንቋ “ማስተር ፕላኑ ይተገበራል” የማለትን ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም “ህዝብ ይነጋገርበታል” ማለት በኛ ሀገር በተለመደው ቋንቋ መሰረት “በማስተር ፕላኑ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች ይካሄዳሉ” እንደማለት ነው እንጂ “በረቂቁ ላይ ህዝቡ ድምጹን ሰጥቶ ውድቅ ለማድረግ ይችላል” ማለት አይደለም፡፡ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት የለመድነው አሰራር ያስተማረን ይህንኑ ነው፡፡

ስለዚህ አሁንም ኳሱ ያለው በመንግሥት እጅ ውስጥ ነው፡፡ ውጥረቱን ለማርገብ ሲባል መንግሥት “ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል” ማለት ይገባዋል፡፡
—–
ሁለተኛ
የመግለጫው ጋጋታ ይገርማል፡፡ ተቃውሞውን እያባባሰ የሚገኘው ዋነኛው “እርሾ” ልዩ ልዩ ባለስልጣናትና ተቋማት የሚሰጡት መግለጫ ነው፡፡ እነዚህ መግለጫዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በአስፈሪ ቃላት የተሞሉ ናቸው፡፡ እስቲ ተመልከቱት!! መንግሥት በየደረጃው በሚሰጣቸው መግለጫዎች ውስጥ “የማያዳግም እርምጃ፤ አስፈላጊውን እርምጃ ” የመሳሰሉ ቃላትን መሰንቀሩ ተቃውሞውን ያዳክመዋል ወይንስ ያባብሰዋል…? በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ለተቃውሞ መውጣቱን እያየንና እየሰማን “ጥቂት ነውጠኞች፣. … አንዳንድ ጸረ-ልማት ሃይሎች፤ ጊዜ ያለፈባቸው የከሰሩ ፖለቲከኞች” እያሉ ማናናቅስ ተቃውሞውን ያስቀረዋል?…. በአብዛኛው ገበሬዎች የታቀፉበትን የተቃውሞ ንቅናቄ በሽብርተኝነት መፈረጁስ ለመንግሥትና ለሀገር ይጠቅማል….?

መንግሥት የሃገሪቱን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት የሚሻ ከሆነ በሚዲያ የሚንፈቀፈቀውን የመግለጫ ጋጋታ መግታትና ችግሩን ከመሰረቱ ማጥናት አለበት፡፡
—–
ሶስተኛ
ይበልጥ የሚገርመው ነገር ደግሞ የአንዳንድ ባለስልጣናት ያልተገባ አነጋገር ነው፡፡ እኔ አፈንዲ በግል ስራዬ ላይ የተሰማራሁ ሰው ነኝ፡ በመንግሥት ስም የያዝኩት ስልጣንና ወንበር የለኝም፡፡ ከመንግሥት ቢሮክራሲ ውጪ በመሆኔ እንዳሻሁት ብናገርና ብጽፍ “የመናገር መብቱን ተጠቀመ” ነው የምባለው፡፡ ከዚህ አልፎ ለክስና ለህዝባዊ ችሎት የምቀርብበት የህግ አንቀጽ የለም (ህዝብን በይፋ እስካልተሳደብኩ ማለቴ ነው)፡፡ የኔ ንግግርና ጽሑፍ ህዝብን አስቆጥቶ ሀገር የማናወጥ አቅምም የለውም፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናት ግን ሲናገሩም ሆነ ሲንቀሳቀሱ የህዝቡን ክብርና ልዕልና ዝቅ ከሚያደርጉ ድርጊቶችና ንግግሮች መቆጠብ አለባቸው፡፡ እነርሱ የሚናገሩት አንድ ቃል ሺዎችን አስቆጥቶ ሀገሪቱን የበለጠ ሊያተራምሳት ይችላል፡፡

ይሁንና ባለስልጣናቶቻችን ሹመት ሲሰጣቸው የንግግርና የእንቅስቃሴ ፕሮቶኮሎችን የሚያስገነዝብ “ኦሬንቴሽን” የሚሰጣቸው አይመስልም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ባለስልጣናት ስብሰባ ሲመሩም ሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የሚናገሩባቸውን ቃላት አይመርጡም፡፡ በትህትና ከመናገር ይልቅ መደንፋትና ማስፈራራት ይቀናቸዋል፡፡ እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዘብ ባለው አነጋገራቸው ይታወቃሉ፡፡ ሌሎቹስ?… በጣም ያሳዝናል!!

የአሁኑ ተቃውሞ በአንድ ጊዜ የመጣ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ተቃውሞው ውስጥ ለውስጥ ሲቀጣጠል የቆየ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አቶ አባይ ፀሐዬ የሚባሉት የቀድሞ ባለስልጣን ሃዋሳ ላይ የኦህዴድ ካድሬዎችን በመሰብሰብ ተናገሩት የተባለው ቃል ነው፡፡ እኚያ ባለስልጣን ለካድሬዎች “ማስተር ፕላኑን የሚቃወሙትን ልክ እናስገባቸዋለን” ማለታቸው ነው የተነገረው፡፡ ኦህዴድ የራሳቸው ድርጅት ስለሆነ “የኛ ካድሬዎችን እንደፈለግነው ነው የምናናግራቸው” ልንባል እንችላለን፡፡

በትናትናው ዕለት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው “ልክ እናስገባቸዋለን” የሚለውን ቃል መደጋገማቸውስ ምን ይባላል…? ይህ አነጋገር ለተቃውሞው መፈንዳት ዐቢይ ሚና መጫወቱን አያውቁትም ማለት ነውን…? ተቃውሞ አድራጊዎቹን “ጋኔል… ጋንግስተር፣ ጠንቋይ…” ወዘተ እያሉ መዝለፍስ ጥቅሙ ምንድነው…? የታላቋ ሶሻሊስት ሊቢያ ዐረብ ጀመሃሪያ አብዮታዊ መሪ የነበሩት ወንድም ሙአመር አል-ቀዛፊ (ጋዳፊ) በመጨረሻው ሰዓት የተነሳባቸውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንደማብረድ በሚዲያ ቀርበው ተቃዋሚዎቻቸውን “የሐሺሽ ተጠቃሚዎች፣ የአል-ቃኢዳ ምንደኞች፣ አሸባሪዎች” እያሉ ዘለፏቸውና በእሳት ላይ ቤንዚን ጨመሩ፡፡ ሊቢያንም ወደ ባሰ ብጥብጥና ሁከት ከተቷት፡፡ እኛ በጭንቅ ዘመናት የበለጠ የምንዋደድና የምንፋቀር ህዝቦች በመሆናችን ያንን የመሰለ ብጥብጥና ሁከት በሀገራችን ይከሰታል ብዬ አላስብም፡፡ ባለስልጣኖቻችን በሚወረውሯቸው ቃላት ላይ ጥንቃቄ ካላደረጉ ግን ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት አነጋገራቸውን ያላረሙ ባለስልጣናትን ወደ ህዝብ ሚዲያ ባያቀርብ ይሻለዋል፡፡
—–
አጭር የመፍትሔ ሓሳብ

መንግሥት ከርሱ የሚጠበቀውን ያድርግ፡፡ ጆሮዎቹን ክፍት አድርጎ ህዝቡን ያዳምጥ፡፡ ማስተር ፕላኑ በብዙሃኑ የኦሮሞ ህዝብ የተወገዘ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን በይፋ ይናገር፡፡ የታፈኑ የህዝብ ተቃውሞ ያለባቸውን ርዕሶች በአግባቡ ይፈትሽ!! ዜጎችን በእኩል ዐይን ይመልከት፡፡ ከኢንቨስተሮች የዶላር ጋጋታ በፊት የድሃ ገበሬዎችን ህልውናና እና ማንነት ያስቀድም፡፡ ኢንቨስተር በዶላር ላይ ዶላር የሚቆልልበትን ስርዓት ከመዘርጋት ይልቅ ደሃው ገበሬ በመሬቱ በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ የሚሸጋገርበትን አሰራር ያስፍን፡፡ በከተሞች አካባቢ የሰፈነውን የኖሮ ውድነትና ስራ አጥነት ለማስተንፈስ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ይቅረጽ፡፡ አዲስ አበባ ብቻ የምትለጠጥበትን የከተሞች ልማት ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተማ የልማት አምባ የሚሆንበትን አዲስ የከተሞች ልማት ስትራቴጂ ይቅረጽ፡፡ የፌዴሬራሊዝም ስርዓቱ በህገ-መንግሥቱ ባለው በተቀመጠው መሰረት በትክክል ይተግበር!!

ተቃውሞውን ለመቆጣጠር በሚል በብዙ ከተሞች ውስጥ የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ዳር ድንበር ወደ ማስከበር መደበኛ ስራው ይመለስ፡፡ በምትኩ የፖሊስ ሃይሉ ጸጥታውን የመቆጣጠር ስራውን ይቀጥል፡፡ በተቃውሞው ሳቢያ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ነጻ ኮሚሽን በአስቸኳይ ይቋቋም፡፡ በተቃውሞው ሳቢያ የታሰሩ ወገኖች በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡ ህይወታቸውን ላጡት ተገቢው ካሳ ይከፈል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ዝምታቸውን በመስበር ለችግሩ እልባት የማፈላለግ ሃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡
——
ታሕሳስ 17/2008
አፈንዲ ሙተቂ
—–
እንደ ጭማሪ
“አፈንዲ ፈርቷል” እያላችሁ የምታሙኝ ኮልኮሌዎች እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡ ፍርሃት በኛ ዘንድ የለም፡፡ ለረጅም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከመናገር የተቆጠብነው ነገሮችን በአትኩሮት ለማጥናት ካለን ፍላጎት አኳያ ነው፡፡ ደግሞም ፌስቡክ ላይ የምንታወቀው ወቅታዊ ርዕሶችን በመጻፍ ሳይሆን የቆዩ ጉዳዮችን በማሰናኘት ነው፡፡ እናንተ ግን በሰው ፍላጎትና ምርጫ ላይ በግድ ልወስን ባይ ስለሆናችሁ በሃሜትና በውረፋ ልትጨርሱን ተቃርባችሁ ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከአንድ ሳምንት በፊት አግብቼ ጫጉላ ቤት የከተትኩ መሆኔን እያወቃችሁ ነው እንዲህ የምታሾፉት፡፡

ግድ የለም!! ሁላችሁም እንዳትረሷት!!…. ጊዜው ሲደርስ ልክ እናስገባችኋለን፡፡ ቂቂቂቂቂቂቂ… !!!

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s