አንጀት የሚበሉ ጠቅላይ ሚኒስትር!

PM Hailemariam Desalegn. ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝሩት አማኑኤል

ሕዝብ አዋቂ ነው። የፖለቲካ ሶሲዮሎጂስቷ ቴዳ ስኮፖል በሚያሳምን ሁኔታ እንደገለጸችውና በአገራችን በተግባር እንደሚታየው ሕዝብ ዝም ቢልም አፈናን ተቀብሏል ማለት አይደለም። በአፈና ውስጥ ያለ ሕዝብ ዝም ሲል እንድም ብናገርም ለውጥ አላመጣም ማለቱ ነው፤ አንድም ማኩረፉንና መከፋቱን መግለጹ ነው፤ አንድም የተመቻቸ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ አድብቶ መጠበቁ ነው።

ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በፊት የነበረውን ሁኔታና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማኅበራዊ ሥነልቦና ባለማወቅ በሙሉ ልቡ እንደሚያሸንፍ አምኖ የምርጫውን ሂደት ለቀቅ አደረገው። አድብቶ ሲጠብቅ የነበረው ሕዝብ ዕድሉን ሲያገኝ አደባየው። በሚያሳፍር ሁኔታ የኢትዮጵያ ናሙና በሆነችው አዲስ አበባ በነጻ ምርጫ መቶ በመቶ ተዘረረ፤ እርቃኑን ቀረ! በእርግጥ ከምርጫ 97 በኋላ በተካሄዱት ምርጫ ተብየዎች ኢሕአዴግ ዓይኑን በጨው አጥቦ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ሲለን ከርሟል። ሐቁን ግን እኛም ኢሕአዴጋውያንም በሚገባ እናውቀዋለን።

ከምርጫ 97 በኋላም ሕዝቡ ዝም ብሏል፤ አሁንም እንደለመደበት ጊዜ ይጠብቃል እንጂ አፈናን ተቀብሏል ማለት ግን አይደለም። ሥርዓቱን የሚደግፉ የሉም አይባልም። በደንብ አሉ። የብሔረሰብ ፖለቲካ ያናወዛቸውና በብሔረስብ ትስስር የከበሩት ጠንካራ የሥርዓቱ ደጋፊዎች ናቸው። ግን በጣም ጥቂት ናቸው። ብዙሃኑ ሕዝብ አሁንም ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ጋር አይደለም። ጥርጥር የሌለው ነገር ነው።

ለዚህች ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ በተወያዩበት ወቅት ያነሱት ነገር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቢያንስ ጉቦ አትስጡ፤ ሰጪ ከሌለ ተቀባይም የለም” በማለት ስለሙስና ሲናገሩ ተስምቷል። የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በአቶ ኃይለማርያም ንግግር “ታላቅነትና መሠረታዊነት” ላይ የተስማሙ ቢመስሉም ችግሩ የሥርዓት ችግር እንደሆነ በሚገባ ያውቁታል። ግን በአንድ በኩል ስለሥርዓት ችግር ቢናገሩ ምን እንደሚመጣባቸው ስለሚያውቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩን ምንጭ ቢናገሩም የሚሰማቸው እንደሌለ ስለሚረዱ ዝምታን መርጠው ይልቁንም በአቶ ኃይለማርያም ንግግር የተደመሙ መስለው ከስብሰባው ወጥተዋል።

የሙስና ችግር፣ የመሬት ዘረፋና ቅሚያ ችግር፣ የመልካም አስተዳደር ገደል መግባት ወዘተ. የሥርዓት ችግር እንደሆነ፣ አገዛዙ ከዚህ አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀው በራሱ ባለሥልጣናት አጋፋሪነትና መሪነት እንደሆነ አቶ ኃይለማርያምም አሳምረው ይገነዘባሉ። የሚያሳዝነው ለስሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ተባሉ እንጂ ማፊያውን ቡድን ሊቆጣጠሩትና ልጓም ሊያበጁለት የሚችሉበት አቅም ጨርሶ የላቸውም። ይህንም በሚገባ ይገነዘቡታል። ስለዚህም ዋናውን ጉዳይ ትተው በጭፍጫፊው ላይ ያተኩራሉ።

ሕዝብ ሳይቸግረው ጉቦ ይሰጥ ይመስል “ጉቦ ሰጪ ከሌለ ተቀባይ አይኖርም” የሚሉት ተረት ተረት ይናገራሉ። ለዚህ ነው ከወዳጆቼ ጋር ስንወያይ፣ “እኝህ ሰውዬ ሊታዘንላቸው እንጂ ሊታዘንባቸው አይገባም” እያልኩ አስተያየት የምሰጠው። በኔ ግምት ሰውዬው አቅም አልባ ከመሆናቸው የተነሳ ሥልጣን አልፈልግም ብለው መውረድ ሁሉ የሚችሉ አይመስለኝም። አንጀት የሚበሉ ጠቅላይ ሚኒስትር!

ምንጭ፡ የቀለም ቀንድ

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s