በአንዳንድ አካባቢዎች የጥምቀት በአል የተቃውሞ መገለጫ ሆኖ ዋለ

ጥር ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጥምቀትን በአል ለማክበር የወጡ ዜጎች የኢህአዴግ መንግስት በቅርቡ በኦሮምያ ክልል ነዋሪዎች ላይ የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በማውገዝ የተለያዩ ተቃውሞችን አሰምተዋል። በአዲስ አበባ ጥቁር ልብስ ለብሰው ለመውጣት ዝግጅት በማድረግ ላይ የነበሩ ወጣቶች በደህንነቶች ጥቆማ እንዲያቆሙ ሲደረግ፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ወጣቶች የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ የሚያወገዙ እንዲሁም ለትግል የሚያነሳሱ ባህላዊ ዘፈኖች ሲያቀነቅኑ ተደምጠዋል።
ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ የሚገኙ ወጣት አባላቱን ለአንድ ሳምንት ያክል በመሰብሰብ በበአሉ እለት ተቃውሞ የሚያሰሙትን እንዲከታተሉ የሚያስችል ስልጠና ሰጥቶ ነበር።
ሳምንቱን በተቃውሞ ያሳለፈችውና የተቃውሞው ማእከልነቱን ከአምቦ የተረከበች የምትመስለው የምእራብ ሃረርጌዋ መኢሶ ከተማ፣ የጥምቀት በአልን የተቃውሞ ድምጿን ለማሰማት ተጠቅማበታለች። ተመሳሳይ ተቃውሞ በቡራዩ ከተማም ተካሂዷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 9 ታዋቂ የትግራይ ተወላጆች ” ተደጋጋሚ ጭፍጨፋዎች እንዲቆሙ አስጨፍጫፊዎች መወገድ አለባቸው” በሚል መግለጫ አውጥተዋል።
የትግራይ ተወላጆቹ ለኢሳት በላኩት መግለጫ ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ላንድ አራተኛ ምእተ ዓመት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተደጋጋሚ የጅምላና የተናጠል ፋሽስታዊ ጭፍጨፋዎች እያካሄደ፣እያሰረ፣ እየደበደበ፣ የህዝባችንን ሰብኣዊ መብትና ነፃነት ረግጦ፤ በቋንቋ እየከፋፈለ፣ በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ፣ የህዝብ ሃብት እየዘረፈና በሙስና ተዘፍቆ ህዝባችንን አፍኖ በመግዛት ላይ ” መገኘቱን አውስተዋል።
” ህወሓት በሰራዊት፣ በደህንነት፣ በውጭ ጉዳይ፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የበላይነት ስልጣን፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በኢኮኖሚና በቻይና የኢትዮጵያ የአምባሳደርነት ቦታ ሳይቀር ያለ ማቋረጥ መቆጣጠሩ፣ ህወሓትን ባለ ርስት እንዲመስል አድርጎታል፡፡ ” የሚሉት ተወላጆቹ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚፈፀሙ ግፎች የህወሓት ባለስልጣኖች እንደ ስልጣናቸው ከፍተኛ ተጠያቂነት” ያለባቸው ቢሆንም፣ የሌሎቹ የኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ባለስልጣኖችም ከመጠየቅ ሊድኑ አይችሉም ሲሉ ገልጸዋል።

ህወሓት የደርግ ኣገዛዝን ለማስወገድ ባስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ህይወታቸውን የሰዉበት ድርጅት መሆኑን ያስታወሱት የትግራይ ተወላጆች፣ነገር ግን ህወሓት ሲመሰረት ጀምሮ የተቆጣጠሩት ግለሰቦች ፀረ ኢትዮጵያ ስለሆኑ ሌሎች አባላትን አግልለው የድርጅቱ ዓላማ የትግራይ ሬፐብሊክ መመስረት እንደሆነ በማኒፌስቶ እስከመግለጽ ደርሰው እንደነበር አትተዋል።
“እነዚህ ግለ ሰቦች የመገንጠል ዓላማቸው ለመተው ቢገደዱም በኢትዮጵያ ደረጃ ስልጣን ከያዙ በሁዋላም በሉአላዊነትና በኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ጥያቄዎች ላይ የማይታመኑ መሆናቸውን ደጋግመው አሳይተውናል” የሚሉት ተወላጆች፣ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ህወሓት ብሄራዊ ጥቅምን አሳልፎ የሰጠ አገዛዝ የለም” ሲሉ ኮንነውታል። ህወሓት/ኢህአዴግ ግልፅነት በጎደለው አሰራር የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን የመስጠቱ አደጋ ስላለ የኢትዮጵያ ህዝብ ለያውቀውና ሊቃወመው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የህወሃት ባለስልጣናት በትጥቅ ትግሉ ጊዜ በትግራይ ውስጥ ከጦርነት ውጭ ደርግ ከገደላቸው በቁጥር የሚበዙ ሰላማዊና ራሳቸውን ሊከላከሉ የማይችሉ ዜጎችን ማስረሸናቸውን የሚገልጹት፣ የትግራይ ተወላጆች፣ ነፍሰ ገዳዮቹ ከ40 ዓመት በፊት ጀምረው የንፁሃን ዜጎችን ህይወት በመቅጨት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ግፉና ግድያው በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል። ባለፈው ህዳር በኦሮሞ ተማሪዎች የተጀመረውና የህዝብ ድጋፍ ኣግኝቶ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለመግታትና ለመደፍጠጥ የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች ብዙ የኦሮሞ ተወላጆችን መግደላቸውና በብዙ ሺ የሚቆጠሩትን ማሰራቸው፣ በጎንደር አካባቢ የሚፈፀመው ወንጀልም በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና እንዳስቆጣቸውም ጠቅሰዋል።
“የኦሮሞ ተማሪዎችና አርሶ አደሮች ሰላማዊ ተቃውሞ በማሰተር ፕላኑ ምክንያት ቢቀጣጠልም፣ በ25 ዓመት የህወሓት/ኢህአዴግ ጭቆና ከተጠራቀመ ብሶት ጋር የተያያዘ ” መሆኑን የገለጹት ተወላጆቹ፣
የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች የሚፈጽሟቸው አረመኔያዊ የጅምላ ግድያዎች ከዚህ በፊትም በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ በ1985፣ በ1993፣ በሰኔ በ1997፣ በጥቅምት 1998፣ በጋምቤላ በታህሳስ 1996 መፈጸማቸውን አስታውሰዋል። እነዚህ ጭፍጨፋዎች የሚቆሙት አስጨፍጫፊዎቹ ወንጀለኞች ከስልጣን ሲወገዱ ብቻ መሆኑንም ግልጽ አድርገዋል።

በአቋም መግለጫቸው መጨረሻ “የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች ማንንም ብሄር/ብሄረሰብ የማይወክሉ፣ ለይስሙላ የህዝብን ጥያቄ አንግበው ብዙ ወጣቶችን አስገድለው ለስልጣን የበቁ ተራ አጭበርባሪዎችና ወንበዴዎች መሆናቸውን፣ ለነዚህ ወንጀለኞች አቤቱታ ማቅረብ (ግድያቸውን እንዲያቆሙ፣ ህገ መንግስታቸውን እንዲያከብሩ መጠየቅ ፋይዳ የሌለው መሆኑን፤ ወንጀል ያልፈፀሙ የኢህአዴግ አባላት ወንጀለኞቹን በይፋ በማጋለጥ የህዝብ ወገንነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው፣ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የሚደመሰሰውና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባው በተናጠል ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኣብሮ ሲታገል መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚፈጸመው ወንጀል ተጠያቂዎች በዋናነት የህወሓት መሪዎች ቢሆኑም ፣ ግብረ-አበሮቻቸውም የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴግ መሪዎችም መሆናቸውን፣ የትግራይ ህዝብ የህወሓት ሰለባ እንጂ ለህወሓት ወንጀል ተጠያቂ አለመሆኑን “ጠቅሰዋል።
በዲያስፖራ የሚኖሩ ትግራዎት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር አብረው ለዴሞክራሲና ለአገር አንድነት እንዲታገሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመግለጫው መጨረሻ ላይ ስማቸውን ያሰፈሩት የኢትዮሚዲያ ዋና አዘጋጅ አቶ አብርሃ በላይ፣ የህወሃት መስራችና ሸንጎ የአመራር አባል ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ በላይነሽ ተክሉ፣ ገብረመድህን አርአያ፣ ዶ/ር ግደይ አሰፋ፣ ግርማይ ገዛሃኝ፣ ካህሳይ በርሀ፣ ነጋሲ በየነና ተስፋይ አጽብሃ ናቸው።

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s