በደብረ ብርሃን በሊቀ ጳጳሱ መኖርያ ቤት ቦምብ ፈነዳ፤ “በሊቀ ጳጳሱ እና በአስተዳደራቸው ላይ ጫና የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው”/የሀገረ ስብከቱ ምንጮች/

His Grace Abune Ephrem

  • ፖሊስ አምስት ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያካሔደ ነው
  • ከደረጃቸው ዝቅ የተደረጉት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊ ይገኙበታል
  • አማሳኞች፣ ጠንቋይ አስጠንቋዮችና መናፍቃን ፈተና ኾነዋል

(ሰንደቅ፤ ረቡዕ፤ ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የደብረ ብርሃን መኖርያ ቤታቸው፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ቦምብ መፈንዳቱ ተገለጸ፡፡

በመንበረ ጵጵስናው የሊቀ ጳጳሱ መኖርያ በሚገኘው ዕቃ ቤት አጠገብ የፈነዳው ቦምቡ፣ በብፁዕ አቡነ ኤፍሬምም ኾነ በሌላ ሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም፡፡

ከፍተኛ ድምፅ የተሰማበት የፍንዳታው ስፍራ ጉድጓድ ፈጥሮ የሚታይ ሲኾን የዕቃ ቤቱ መስኮቶች ረግፈዋል፤ በመንበረ ጵጵስናው አጠገብ በሚገኘው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ያለው የሊቀ ጳጳሱ ቢሮ መስተዋቶችም ተሰነጣጥቀዋል፡፡

የከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት፣ አምስት የሀገረ ስብከቱን ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ታኅሣሥ 27 እና ጥር 3 ቀን በቁጥጥር አውሎ ምርመራ እያካሔደ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ሓላፊው ቀሲስ አስቻለው ፍቅረ፣ የሕግ ክፍሉ መምህር አክሊል ዳምጠው፣ ኹለት የጥበቃ ሠራተኞች እና አንድ የሊቀ ጳጳሱ የቅርብ ዘመድ በአስተዳደሩ ፍ/ቤት በተለያዩ ጊዜያት በፖሊስ ቀርበው ከ7 እስከ 10 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡

ፍንዳታው በተከሠተበት ወቅት፣ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የልደትን በዓል ለማክበር በመርሐ ቤቴ እንደ ነበሩ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ “የማስፈራራት ዓላማ ያለው ነው፤” ያሉት ምንጮቹ፥ ከክሥተቱ ኹለት ሳምንት በፊት በሊቀ ጳጳሱ የዝውውር ርምጃ የተወሰደባቸውየአስተዳደር ክፍሉ ሓላፊና ሌሎች የጥቅም ግብረ አበሮቻቸው በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና በአስተዳደራቸው ላይ ጫና ለመፍጠር ያቀዱበት ሳይኾን እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡

በአስተዳደር ጉባኤ ታይቶ በሊቀ ጳጳሱ የጸደቀ ነው በተባለው ውሳኔ÷ በሙስና፣ በባለጉዳዮች እንግልት እና በጠንቋይ አስጠንቋይነት ክፉኛ የሚተቹት የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ሓላፊ ቀሲስ አስቻለው ፍቅረ ከደረጃቸው ዝቅ ተደርገው ወደ ስታቲስቲክስ ክፍል ባለሞያነት መዘዋወራቸው ታውቋል፡፡

በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ አስተምህሮንና ሥርዓትን በሚፃረሩ የኑፋቄ አካሔዶች ገዳማቱን በማተራመስ እና በጠንቋይ አስጠንቋዮች ሳቢያ ከወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከአገልጋዮች እና ከምእመናን በርካታ ምሬቶች እና አቤቱታዎች ለብፁዕነታቸው እና ለጽ/ቤታቸው ሲቀርቡ የቆዩ ሲኾን ከሰላም አኳያም አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው የዞኑ አስተዳደር ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ማሳሰቢያ ሲሰጥ መቆየቱ ተገልጧል፡፡

በጸሎተኛነታቸው እና በአባትነታቸው ተወዳጅ የኾኑት የዕድሜ ባዕለጸጋው ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ ሀገረ ስብከቱን በሊቀ ጳጳስነት ሲመሩ ከ፳ በላይ ማስቆጠራቸውን ያስረዱት ምንጮቹ፣ የተቃጣባቸው አደጋ፣ “በግል ጥቅም ኅሊናቸው ከታወረ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ ከማይሉ አካላት በቀር በሌላ በማንም ሊታሰብ አይችልም፤” በማለት በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ መሠረት፣ የሀገረ ስብከት ዋና ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ለሚገኘው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሾመው ሊቀ ጳጳሱ፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት መሪና ተጠሪ ሲኾን ለአስተዳደሩም የበላይ ሓላፊ ነው፡፡ በአስተዳደር ጉባኤው የታየና የተጠና የሰው ኃይል ቅጥር፣ ዕድገት፣ የሥራ ዝውውር፣ ደመወዝ መጨመርና ሠራተኛ ማሰናበት ሊፈጸምና በሥራ ላይ ሊውል የሚችለው በሊቀ ጳጳሱ ጸድቆ መመሪያ ሲሰጥበት ነው፡፡

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s