ከማኅበረ ቅዱሳን ላይ እጃችሁን አንሱ – መልካም ሞላ

ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ ‹ማኅበረ ቅዱሳንን እዘጋለሁ› የሚለው ፉከራቸው በተሰማ በቀናት ውስጥ ይህን የሚገልጽ ደብዳቤ ከጽህፈት ቤታቸው ወጥቷል፡፡ ባለ ብዙ ገጽ ማብራሪያ ያለው ደብዳቤው የሚያትተው ስለማኅበረ ቅዱሳን ‹‹ ኃጥያት›› ቢሆንም እዉነታውን ለሚረዳ ግን ደብዳቤው በፓትሪያሪኩ ስም ይውጣ እንጂ የማን ፍላጎት አንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንዴት? ብሎ ለሚጠይቅ ደግሞ ደብዳቤው መጨረሻ ክፍል ላይ በግልባጭ እንዲደርሳቸው ተብለው የተጠቀሱት የመንግስት መስሪያ ቤት ዝርዝር ማየት በቂ ነው፡፡

ጋዜጠኛ መልካምሰላም ሞላ

ለጠቅላይ ሚነስትሩ፣ ለፌደራል ሚኒስቴር፣ ለአ.አ ፖሊስ ኮሚሽን፣ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባ . . .ይልና መጨረሻ ላይ ትግራይ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር፣ ለትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለትግ/መስ/ ፍትህ ቢሮ ይላል፡፡ በቅዱስ ሰኖዶስ ለሚተዳደር ቤተ-ክርስቲያን ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ ድረስ በግልባጭ የሚያሰጠው ለምን ይሆን? ማኅበረ ቅዱሳን ለእኔ በገባኝ እና ባወኩት እጅግ በጣም ባነሰ እውቀት ባጭሩ እንዲህ ፃፍኩት፡፡ እኔ ማኅበረ ቅዱሳንን ያወኩት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ ያኔ እኔ እና እኔን መሰል ጓደኞቼ ስለ ኃይማኖታችን የምናውቀው ነገር ቢኖር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናችንን እንጂ ኃይማኖታችን ውስጥ ስላለው የከበረ ማእድን ጉዳይ እዉቀት አልነበረንም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ገና ሀ ብለን ትምህርት ለመጀመር ግቢውን ስንረግጥ ጀምሮ በፍጹም ክርስቲያናዊ ፍቅር እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ተቀብለው አስተናግደውን ነበር፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግቢው ውስጥ በቆየንባቸው 3 ተከታታይ አመታት ትምህርት ቀርፆ ስለኃይማኖታችን በሚገባ እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ መሰረታዊ ትምህርት በመስጠት እግዚአብሔርን እያወቅነው እንድናመልከው ኃይማኖታችንን በማመን መታመን አጽንቶልናል፡፡ በወጣትነት ዘመናችን የዓለም ባህር ሳያሰጥመን በፊት መርከብ ሁኖ ወጀቡን አሳልፎናል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ነፍሳችንን አድኖታል፡፡ በመንፈሳዊም ይሁን በማህበራዊ ህይወታችን ፍቅርን መረዳዳትን እና መተሳሰብን . ወንድማዊ እና እህታዊ ግንኙነትን በዛ ከባድ በነበረው ዩኒቨርሲቲ ፤ በስጋ ብቻ ሳይሆን በነፍሳችን ተመርቀን እንድንወጣ አድርጎናል፡፡ ማኅበሩ በተመቻቸ ሁኔታ አልነበረም ያስተማረን፣ ቤት እስክናገኝ አንዲት ጠባብ ክፍል ግንድ አጋድመን ፣ መሬት ላይ ዘርግተን እየተቀመጥን፣ ቀን በትምህርት ሌሊት አዳር መርሃ ግብር እየተሰጠን ፣ እሁደ እሁድ በቤተክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ (ያኔ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ን ደሴ አላለቀም ነበር) ድንጋይና ግንድ ላይ ቁጭ ብለን ደስ እያለን እንድንማር ያደረገን እግዚአብሔርን እንድናውቅ ነፍሳችን ያተረፈልን ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ማኅበሩ ህንፃ ለመግንባት ከማሰቡ በፊት መጀመሪያ የእኛን (በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችን) ልብ ውስጥ ፍቅረ እግዚአብሔርን ስሎ ህንጻውን ገንብቶ ነበር፡፡ ማኅበሩ አሁን እንዲህ ባማረ ህንፃ ከመቀመጡ በፊት አቧራ አራግፎ መሬት ላይ ቁጭ ብሎ ሰው ሲሰራ ነበር፡፡

ኃይማኖቴን ምን እንደሆነ ያወኩት በማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ የሁሉም ህግ ማሰሪያ ስለሆነው ፍቅር በተግባር ያስተማረኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እኔ እና እኔን መሰል ብዙ እልፍ አእላፍ ነፍሳቶች በማኅበረ ቅዱሳን ተምረዋል፣ ብዙዎች ወደ ትክክለኛው መንገድ መጥተዋል፣ ብዙዎች ከጥፋት ጎዳና ተመልሰዋል፡፡ የዋና ማዕከል 5 ኪሎ ህንፃ መሰረቱ ድንጋይ ሳይሆን የማኅበሩ ፍሬዎች ልብ ነው፡፡ በአካቢያችን የነበሩ ራቅ ያሉ ጧፍ እና እጣን እንዲሁም ንዋየ ቅድሳት አጥተው ሊዘጉ የነበሩ ቤተ ክርስቲያኖችን ለቁርሳችን ያሰብነውን ዳቦ በመሸጥ እንዲከፈቱ ሲያደርጉ አይተናል፡፡ በማኅበሩ ቤተ-ክርስቲያን ከፍ ብላ ስትታይ አይተናል፡፡ የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስን ቤ/ን ስርዓትን ጠንቅቀን እንድናውቅ ስላደረጉን የተሃድሶ ዜና አያስደነግጠንም፡፡ ዘፈን መሳይ መዝሙሮች አያሳስቱንም፡፡ ዛሬ አማኝ ሁነው ህዝቡን ሲያስጨበጭቡ የነበሩት ነገ ሌላ ዓላማ ይዘው ብቅ ሲሉ አይደንቀንም፡፡ የመናፍቃን ጩኸት አዲስ አይሆንም፤ እንጠነቀቃለን እንጂ በማዕበሉ አንነጠቅም፡፡ እግዚአብሔርን እንጂ ሰው ሰለማንከተል ታዋቂ አጥማቂ ፣ታዋቂ ሰባኪ ፣ታዋቂ . . . የሚሉት ዘመን አመጣሽ ግርግሮች አያናውጡንም፡፡

እግዚአብሔር ድንቅን ይሰራል እናምናለን፤ በሃሰተኞች ግን አንታለልም፡፡ ምክንያቱም ስለኃይማኖታችን ከማስረጃ ጋር ጠንቅን እንድናውቅ አስተምረውናል፡፡ ይሄ በጥቂት አመታት በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ዓመት ያየሁት ስራ ነው፡፡ ብጹዕ ፓትሪያሪኩ ማኅበሩ ለምን እንደሚያሰጋቸው አልገባኝም፡፡ ምናልባትም ከቤተ ክህነት በተሻለ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ ይሆናል፡፡ሌላው በሙስና የተጨማለቁት የውስጥ ሰዎች እንዳይጋለጡም ይሰጋሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ በአክራሪነት ፈርጀውት ነበር፡፡ ራዕያቸውን እያስቀጠሉ ያሉት ዛሬም እየለፉ ናቸው፤ለማፍረስ፡፡ ዛሬም በአንድም በሌላም መንገድ ማኅበሩን ለማዳከም ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከሁለት አመት በፊት ስለማህበራት በተመለከተ አዋጅ ሊፀድቅ ተብሎ( ስራ ላይ ይዋል አይዋል አላውቅም) በተጠራው ስብሰባ ላይ እሰራበት የነበረውን መጽሄት ወክየ ተገኝቼ ነበር፡፡ ባጭሩ አዲስ ይወጣል የተባለው ደንብ ማንኛውም ማህበር ምንም አይነት የልማት ስራ መስራት አይችልም የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ አዋጁ በቀጥታ ለማህበረ ቅዱሳን መምቻ ተብሎ እንደወጣ ግልጽ ነበር፡፡ እኛ በማናውቃቸው የማህበሩ አመራሮች እና ሰራተኞች የሚያውቋቸው እጅግ ብዙ ፈተናዎች እየደረሰበትም የእግዚአብሔር ፍቃድ ስለሆነ እና ስለወደደው እስካሁን በጽናት ቆሟል፡፡

ዛሬም የወጣው ደብዳቤ ለማኅበሩ አዲስ ፈተና አይደለም፡ የሚገርመው ግን መናፍቃን እና ተሃድሶዎች በውስጥ እና በውጭ ሊያፈርሱ ሲተጉ መንግስት አይኑን ተክሎ ሊያጠፋው እየጠበቀ የቤተክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ በተቃራኒ ጎን መቆሙ ብቻ ነው፡፡ እዉነት ነው ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን መንግስትን ቤተ ክህነትን ያስደነግጣል፤ ምክንያቱም ስሙን ይዞ የተኛውን ቤተ ክህነት ስራ ተቀብሎ ማኅበሩ እየሰራ ነው፡፡ ሰነፍ እረኛ የእሱን ከብቶች ጅብ ስለበላቸው ሳይሆን ነቅቶ የጠበቀው ባልጀራው ከብቶች ስለበዙ ይናደዳል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ተማሪዎችና ገዳማት ራሳቸው እንዲችሉ የሚያስችል እቅድ ነድፎ ይንቀሳቀሳል እንጂ ሌላ ድብቅ አላማው የለውም፡፡ ቃለ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መምህር አሰልጥኖ በማስማር እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች አስጠምቋል፡ ክርስትናን አስፋፍቷል፡፡ ቤተክህነቱ ወይም ሲኖዶሱ የረሳቸውን ገዳማት የተዘጉ ቤተክርስቲያኖች ፣ የአብነት ተማሪዎች እየረዳ በሁለት እግራቸው አቁሟቸዋል እንጂ ‹ለድብቅ › አላማ አልተጠቀመባቸው፡፡ በመሰረቱ ይህች ቃል ከየት እንደመጣች ትታወቃለች፡፡ ቴሌቭዥናችን አስሬ እየመጣ አክራሪ እያለ ሲያደነቁረን ከርሟል፡፡

ማኅበሩ ባለ ሁለት ዲጅት የሂሳብ ሲስተም የሚጠቀም እንጂ እንደ አብዛኞች ቤተክርስቲያኖች ለሙስና የሚያጋልጥ አሰራር የለውም፡፡ እቅዱም በአመቱ መጀመሪያ (በቤተክህነት?) አጸድቆ ይጀምራል ኦዲት ተደርጎ ይታያል፡፡ ገዳማትን ሲረዳ፣ ጤናቸው እንዲጠበቅ ተወካዮችን እየሰበሰበ ትምህርት ሲሰጥ ፣ በየገጠሩ እየዞረ ሲያስተምር እንጂ በሚሊዮን ዶላር መኪና ሲገዛ ፤የቤት እቃ ‹ሰርፕራይዝ › እያለ ሲያሟላ አላየንም ፤አልሰማንም፡፡ ለመሆኑ ሲኖዶሱ ዋልድባ ሲታረስ መግለጫ አውጥቶ ነበር? ቆብ አጥልቀው በሃሰት እያስተማሩ እያጠመቁ ብዙ መቶ ሺዎች ክርስቲያኖች ግራ ግቷቸው ሲባዝኑ ያለው ነገር ነበር? ያሬዳዊ ዜማን የለቀቀ እና ዝላይ የበዛበት መዝሙር እና ለዛ ቢስ ስብከት እየተመረተ ምእመናኑ ሲዋትት ምን ብለው መግለጫ አውጥተው ነበር? ምን ብለው እርምጃ ወሰዱ? ወጣቱን የታደገው ማነው? እነ ብጹዕ አቡነ ተክለኃይማኖት እና አቡነ ቴዎፍሎስ ወንበር ላይ ተቀምጦ የመጣን ደብዳቤው ፈርሞ ማውጣት በእዉነት አይከብድም? እርግጥ ነው ህንጻው ይፈርስ ይሆናል፡፡ ግን ልባችን የበቀለውን ፍሬ እንዴት ማጥፋት ይቻልዎታል? በነገራችን ላይ በቅዱስ ሲኖዶስም ይሁን በቤተክህነት ውስጥ እጅግ ለማኅበሩ የሚቆረቆሩ እና የሚጠብቁት፣ የሚጸልዩ ብፁዓን አባቶች አሉ፡፡ ያስቸገሩት ከላይ እየታዘዙ የሚያስፈጽሙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የጽሁፍ መደምደሚያ ግን አንድ እና አንድ ነው፡፡ መንግስት ከማህበሩ ላይ እጁን ያንሳ፡፡

እደግመዋለሁ ደብዳቤው በፓትሪያሪኩ ተፈርሞ ይውጣ እንጂ ከኋላ እጅ ጠምዝዘው የሚያጽፉት እነማን እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከማኅበሩ ላይ እጃችሁን አንሱ፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s