የአገሬ ልጆች ጥበባችን የት ጋር እንደመከነ ነጻነታችን የት ጋር እንደተገፈፈ እንወቅ – ደ ሰርፀ ደስታ

DC 6778

ሰከን ብለን ማሰብ ከቻልን እጅግ አእምሮን የሚቧጥጥ የሚያነገበግብ ጉዳይ ነው፡፡ ስሜታችንን አፈን አድርገን እስኪ ትንሽ ወደራሳችን ተመልሰን እናስብ፡፡  እኛ ሌላው ዓለም በጥሩ ነገሮቻችን ያውቀናል ብለን አስበን ይሆናል፡፡ እርግጥም ይመስለናልም፡፡ እውነታው ግን የሚውቀን ካለ አብዛኛው አለም እኛን የሚያውቀን በረሀብ፣ በስደተኝነት እና በመሳሰሉት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ መፈለቂያ፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ እምነት የሰባዓዊ ነጻነት አገር እንደሆነች ጥናት እናጠናለን ከሚሉት ጥቂት ሳይንቲስቶች በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ የተዋረደ ሕዝብ የተዋረደ ነው በጎ ታሪኩ ሳይሆን ውርደቱ ነው የሚነገርለት፡፡ ለመወቃቀስም ለግንዛቤም ይረዳ ዘንድ በአእምሮየ የመጡ ነገሮችን በነጥብ በነጥብ ለማነሳት ፈለግሁ፡፡

ለሕዝብ ሁሉ በተለይም ለጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተስፋ የሆነው ኢትዮጵያዊነት

በታሪክም ርቀትም ሆነ ልዩ በሆነ ሰበዓዊ ፍልስፍና የጥንታዊያን ኢትዮጵያውያን የሚያኮራና ዛሬ ላለው ዓለም ጥበብ ሳይቀር ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ የምናውቅ ስንቶቻችን እንደሆን አላውቅም፡፡ በእርግጥ በዛ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረው ሕዝብ ዛሬ ያለነው አባቶች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ምድሪቱ ግን እነዛ ጠቢባን እንደኖሩባት ሥራዎቻቸው ሕያዋን ሆነው ይመሰክራሉ፡፡ እዚህ ላይ የጥንቱ ስልጣኔ ተካፋዮች እንጂ እኛ ብቻ የስልጣኔው ባለቤቶች ነን እያልኩ አይደለም፡፡ የሜሶፖታሚያ፣ የግሪክ፣ የሮማውያን እንዲሁም ብዙም እኛ በታሪክ የማናውቀው የአረቦችና የሩቅ ምስራቅ አገራት በተለይም የቻይና ጥንታዊ ስልጣኔ ከታላላቆቹ ተርታ ነው፡፡ ስለሆነም እኛ ብቻ የጥንቱ ሥልጣኔ መሠረት እንደሆንን ማሰብ ራሱ ስሜተኝነት እንጂ ማንነታችንን አያገዝፍም፡፡ ትክክለኛው እኛም ከጥንታውያኑ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጆች አንዱ ነበርን፡፡ እዚህ ጋር እኛ ስል ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ግብጽን ጨምሮ አጠቃላይ አካባቢውን በሚወክል መናገር እወዳለሁ፡፡ ምክነያቱም የዚህ አካባቢ ሥልጣኔ ከሌሎች አለማት በተለየ የጥቁር ሕዝብና የአፍሪካ ስለሆነ ነው፡፡ ልብ በሉ የጥንታውያኑ ምስር (ግብጽ)፣ አቢሲኒያ (ኢትዮጵያ)፣ እንዲሁም ኑቢያ (ሱዳን) ስልጣኔዎች የአንድ ሕዝብ ሥልጣኔ እንደሆኑ ታሪክ ይናገራል፡፡ ግብጽ ከእስልምና መስፋፋት ጋር በአረቦች ስለተወሰደች ጥንታውያኑ ጥቁሮቹ (ጠያይሞቹ) የፈሮኖቹ ዘሮች ወይ አልቀዋል ወይ ወደ እኛ ሸሽተው ከእኛ እንደ አንዱ ሆነዋል፡፡ ስልጣኔው ግን የጥቁር አፍርካዊ ሕዝብ ነው፡፡

የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ብዙ ተብሏል፡፡ የእነ ሉሲ ታሪክ ብዙም እኔን አይማርከኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ አካባቢው የጥንታውያን ፈላሰፎች መኖሪያ መሆኑ በዛው ነገር ተመዝግበው እስከዛሬም በሚነበቡ መዛግብት ምስክርነት ማግኘቱ የማንን ምድር ዛሬ እኛ የሲዖል ተምሳሌት እንዳደረግናት ሳስብ አዝናለሁ፣እቆጫለሁ፣ አፍራለሁም፡፡ ዲዮከራተሰ የተባለ ግሪካዊ ጸሐፊ ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደዘገበው ኢትዮጵያውያንን የመጀመሪያዎቹ የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪዎች ያደርጋቸውል፡፡ በእምነትም የመጀመሪያዎቹ በእግዚአብሔር የሚያምን ሕዝብ ይለዋል፡፡ የመልካቸውን መጠየምና የአእምሮ ብስለታቸውንም ሲተነትን ምን አልባት በፀሐይ መንገድ ላይ ስለሚኖሩ ከሌላው አለም ቀድመው የበሰሉ ይለዋል፡፡ የሌለው ዓለም የቆዳ ንጣት በጸሐይ ካለመብሰል እንደሆነ ጸሐፊው በትክክል ተረድቶታል፡፡ ለብዙዎች የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚባሉት እስራኤሎች እንደሆኑ ይታሰባል፡፡ እውነታው ግን የእስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብነት የሚጀምረው ከአብርሃም ነው፡፡ ከዚያ በፊት በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሌሎች ሕዝቦች ለመኖራቸው ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፡፡ የክርስቶስ ምሳሌ የነበረው መልከጸዴቅ አንዱ ነው፡፡ የዚህ ሰው ታሪክ በተለይ ጳውሎስ ወደ እብራውያን 7 ላይ እንደገለጸው እጅግ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ይህ ሰው ከጥነታውያኑ ኢትዮጵያውያን (ምድያማውያን) አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያዊው የሙሴ  አማት የምድያም ካሕን እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

አሁንም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ክርስቶስ ሲወለድ በኢየሩሳሌም ሄደው የሰገዱት የፈላሰፎቹና የከዋክብት ተመራማሪዎቹ የሰበዓ ሰገል አባት በለዓም ምድያማዊ እንደሆነ እናነባለን፡፡ ልብ በሉ ነገሩን ከኢትዮጵያ ጋር ለማጠጋጋት በሚል አይደለም፡፡ እውነት ስለሆነ እንድናውቀው እንጂ፡፡ ለዛሬው ትውልድ በነዚህ ሰዎች ታላላቅ መዛግብት እንደቀሩለት እናያለን፡፡ እኛ ከእኛ እየወሰዱ መልሰው እሱኑ የሚነግሩንን እንጂ የራሳችን መሆኑን ማወቅ የተሳነን መሆናችን የሳዝነኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት አለምን እያነጋገረ ያለው መጽሐፈ ሄኖክ የእኛው አገር በግዕዝ ተጽፎ የተገኘው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በ18 ክፈለ ዘመን በጀምስ ብሩስ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ የተወሰደው፡፡ ከዚያ በኋላ እነሱ ብዙ ሚስጥሮችን ነው ከዚሕ መጽሐፍ እያወጡ ያሉት፡፡ እኛ አገር ለዘመናት ይህ መጽሐፍ ተከድኖ ነበር ወይም ለማይረቡ ሰውች ጥቅም ይውል ነበር፡፡ እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶች ምናችንም አይደለም፡፡ ሄኖክ ራሱ እስራኤላው እንዳልሆነ ስናስተውል ታሪኩ እኛው ምድር እንደሚሆን እንገምታለን፡፡ ልብ በሉ ሄኖክ የሰማይን ሚስጥር ሁሉ ያየ ነው እሱም የዓለም ሕዝብ ሁሉ አባት የሆነው የኖሕ አያት ነው፡፡

ሌሎች የጥንታውያን ኢትዮጵያውያን አስደናቂ መዛግብቶች ብዙ ናቸው፡፡ ለዛም ነው ዛሬ የሌሎች  አገራት ተመራማሪውች በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጉራንጉሩን ሁሉ የሚያስሱት፡፡ እኛ ፈዘናል፡፡ ከዛም በላይ የእኛ አይደለም ብለንም የጣልንወ ብዙዎች ነን፡፡ በጀረመን አገር ሀምቡርግ ዩኒቨረሲቲ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኢንስቲትዩት የግዕዝ ቋንቋ የመሰጠቱ ሚስጢር ለግዐዝ ከማሰብ ሳይሆን በእንዚያ ዘመናት በዚህ ቋንቋ ተመዝግበው የቀሩ ሚስጢራትን ለማግኘት ነው፡፡ የኢንስትቲዩቱንም ስም ልብ ብላችሁ አስተውሉት፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ነች ግን ሊሉ የፈለጉት ትኩረታችን ኢትዮጵያ ነች ነው፡፡ ዛሬ በጥንታዊት አክሱምና ሌሎች የሰሜኑ አገራችን ከፍተኛ የአርኪዮሎጂ ጥናትና የመዛግብት ምርምር የሚያደርጉት ጀርመኖች ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብቶች ተርጓሚዎች እነሱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ምርምር ኢትዮጵያውያን የሉበትም፡፡ የግዕዝ ቋንቋና ፊደላት ከቋንቋ በላይ ብዙ ሚስጢራትን ስለያዙ ዓለም ይፈልጋቸዋል፡፡ ለአፍሪካም በሉት የሌላው ጥቁር ሕዝብ ከጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን የተበረከተ ኩራት ነው፡፡ እኛ ግን ዛሬ ራሳችንን ከግዕዝ ፊደላት አመከንን ከራሳችን ሀበት ራሳችንን አገለልን፡፡

 

የኢትዮጵያ የጨለማ ዘመናትና የሌላው አለም ሥልጣኔ

የዛግዌ ሥርዎ ምንግስት እየተባለ ከሚጠራው የላሊበላ ዘመን ሥልጣኔ በኋላ እስክ የታላቁ መሪ ምኒሊክ አሳዳጊ ታላቁ ባለራዕይ ቴዎድሮስ ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ የቁልቁሊት አዘቀት ጉዞ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ይህ ዘመን በአገሪቱ ዱርዬዎች የሰፈኑበት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ቀስ እያለም ሀይማኖት ሳይቀር የጠፋበት ሥርዓትና ሕግ የሌለው ብዙ መዛግብትም የተበረዙበትና እንዲሁም ለሌሎች እጅ የተሰጡበት አኗኗር እንደነበር ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ዘመን የውድመት ዘመን እንደሆነ እናያለን፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ በኋለኛው ዘመን እሱም በፖረቺቻሎች እገዛ በጎንደር ተገንብተው ከምናያቸው ሕንጻዎች በቀር አንድም ንጉስ በሉት መሳፍንተ ለምልክት የሰራው ሥራ እንደሌለ እናያለን፡፡ መሳፍንት ተብዬዎቹ ከተራው ሕዝብ ባልተሻለ መኖሪያዎች እንደሚኖሩም እንገምታለን፡፡ ይህ ዘመን በሌሎችም አገራት እንዲሁ የመሳፍንት አገዛዝ እንደነበር እናያለን፡፡ ሆኖም በሌሎቹ አገራት ከእና በተቃራኒው በመሳፍንቱ መካከል ፉክክር ስለነበር ታላላቅ ሥራዎች ትተው እንዳለፉ ዛሬ ቆመው ባሉት ቤተመንግስቶቻቸውና ከተሞቻቸው እናያለን፡፡ በአውሮፓ በየኮረብታዎቹ የሚገኙ ካስሎችና ሌሎች ውብ ስነሕንጻዎች ከነ ልዩ መናፈሻቸው  የዚያ ዘመን መሳፍንት በረከቶች ናቸው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ግን በጥቁር ሕዝብ እጅ በአሉ አገራት አንድም ቦታ የእኛው ወገን በሆኑት ሱዳኖች በቀር እነዚህን ምልክቶች አናይም፡፡ የእኛው አገር  ከላይ የጠቀስኩትን ጎንደር ውስጥ ካሉ ሕንጻዎች በቀር መሳፍንቶቿ አልሰሩም፡፡ በግብጽና በሌሎች ሰሜን አፍሪካ አገራት በአረቦቹና በአውሮፓውያኑ የተሰሩ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ አሁንም የጥቁሩ ሕዝብ ተሰፋና ራዕይ እዚች አገር ውስጥ አልነጠፈም፡፡

 

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታና ለሌሎች ተሰፋ የጣሉ ታሪካዊ ክስተቶች

የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት ባለራዕዩ ቴዎድሮስ አሰቡት ሞከሩት፣ ተከታያቸው ዮሐንስ ተከተሉት በመጨረሻም ቴውድሮስ ያሳደጓቸው ታላቁ ምኒሊክ እውን አደረጉት፡፡ ሂደቱ ሥርዓት የሌላቸውን እነዚያን መሳፍንተ አሸንፎ አገር መገንባቱ እጅግ ፈታኝ እንደነበር እንገምታለን፡፡ ይህ ለምኒሊክ የስኬት መጀመሪያው ነበር፡፡ ሌላው የምንሊክ ታላቅ ስኬት የአደዋ ድል ነበር፡፡ በተለይም የአደዋው ድል አንድ ጥቁር ሕዝብ በነጭ የቅኝ ግዛት ወራሪ ላይ የበላይነትን የተቀናጀበት ስለነበር ለጥቁር ሕዝብ ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም በቅጭ ግዛት የተያዙ አገራት ቅኝ ገዥዎችን ማሸነፍ እንደሚቻል አዋጅ የተነገረበት ነበር፡፡ ለብዙዎችም ሀገራት የነጻነት ታጋዮች መነሳትና ቅኝ ግዛት ማክተም ይህ የታሪክ ክስተት ምክነያት ሆኗል፡፡  ከእነዚህ ታላላቅ ሴኬቶች ጋር የሚኒሊክ ራዕይ አገር ወደኋላ የቀረችበትን እድገት በቁጭት መመለስ ነበር፡፡ በዚህም በለራዕዩ ምኒሊክ አንድ ሰው በዕድሜው ይሰራዋል ተብለው ፈጽሞ የማይታሰቡ ሴክቶችን ትተው አልፈዋል፡፡ በዚህ የታሪክ ስኬት ውስጥ ግን የሚኒሊክ ቀኝ እጅ የነበረው ዛሬ አብዛኛው የራሱን አኩሪ ታሪክ ክዶ በዘረኝነት ልክፍት ነጻነቱን አጥቶ ያለው የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ነበር፡፡ ለዚህ የምኒሊክን ጅግኖች የጦር አበጋዞችና ከፍተኛ ሹማምነት መየት ይቻላል፡፡ ሰሞኑን የደጃዝማች ገረሱ ዱኪን የጦር ውሎ የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክ አይቼ ለዚህ ትውልድ ምን ሊነገረው እንደሚችል አስቤ አዘንሁ፡፡  ለዚህ ለቁቤ ትውልድ ይሄ አልገባሕም ብሎታል፡፡ እስከሚገባውም እንደባዘነ ይኖራል፡፡ የታላላቅ አባቶቹን ደምና ታሪክ አርክሷልና፡፡ አባቶቹ የሰሯትን አገር ንቆ ጠላቶቹ ባኖሩለት የቅዠት አለም ይኖራልና፡፡ ይህ ታሪክ ግን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የነጻነት ፈላጊዎች በተለይም ደግሞ የጥቁር ሕዝብ ኩራት ጭምር ነው፡፡

ምኒሊክ በልጅ ልጃቸው  ራዕያቸው እንደሚቀጥል አምነው ልጅ ኢያሱን በምትካቸው ቢመርጡም ነገሮች ሳይሳኩ ከኢየሱ ተነጥቆ ለዘውዲቱ ከዛም አገሪቱን ለረጅም ዘመን ለመሯት ኃ/ስላሴ ንግሲናው ተሰጠ፡፡  ኃ/ስላሴ ብዙ  የአስተዳደር ግድፈቶችና ለዛሬውም ውዥንብር አሉታዊ ሚና ቢኖራቸውም በአለም አቀፍ ግንኙነትና ለነጻነት ሕዝብ ታጋዮች የነበራቸው አስተዋጽዖ ታላቅ እነደሆነና ዛሬም ድረስ አገሪቱ በበጎ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምትነሳባቸው ንጉስ በመሆናቸው እንደ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የሚያኮሩ ናቸው፡፡ ዛሬ መቀመጫውን አዲሰ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ሕብረትም የእኝሁ ኢትዮጵያዊ ንጉስ በረከት ነው፡፡ የአፍሪካን ሕብረት አዳራሽ በአንድ አጋጣሚ አይቼ ከአዘንኩባቸው ጉዳዩች አንዱ ግን ማንዴላን ጨምሮ ሁሉም ለአፍሪካውያን ነጻነት ያበረከቱ መሪዎች መታሰቢያ አዳራሽ ተሰይሞላቸው ዋናው ተዋናይ ኃ/ስላሴ ግን ሥማቸው አንድም ቦታ ማየት አልቻልኩም፡፡  እኔ በግሌ የማንዴላ አድናቂ አይደለሁም፡፡ ማንዴላ 27 በእሰር ስለሕዝብ መቆየታቸው ትልቁ ውጊያቸው ነው፡፡ ከዚህ ጀርባ ግን 27 ሳይገድሏቸው በማሰር ያከረሟቸውን አሰሪዎቻቸውንም አስተዋጽዖ አንዘንጋ፡፡ በፕሬዘዳንትነት ስልጣናቸውም ቢሆን ነጮቹ ሆን ብለው ባይሰጧቸው አይዛካም ነበር፡፡ ሥልጣንም ይዘው ብዙ የቀየሩት ነገር አለነበረም፡፡ ከእሳቸው ይልቅ ነጮቹን በመዋጋት ሙጋቤ ደፋር ነበሩ፡፡ ለዛም ነው ዛሬም ድረስ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮቹ የባርነት ስሜት የሚያነጸባርቁት፡፡ ለደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ጠላቶች ጥቁሮች እንጂ ነጮች አሁንም እንደ ልዩ ፍጥረት ነው የሚያዩት፡፡

ደርግ  ስልት አልባ የሆነ የአጥፋው ፍልስፍና ልክፍት የተጠናወተው ዛሬም ድረስ አገሪቷን እየመሩ ያሉት የ60ዎቹ ትውልድ መንግስት ስለሆነ ብዙ ጥፋት ተመዝግበውበታል፡፡ ደርግ ግን ለዚሕች ሀገር ብሔራዊ ስሜትን በመፈጠር የነበረው አስተዋጸዖ ከፍተኛ ነበር፡፡

 

የዛሬዎቹ ባለስልጣኖቻችንስ

የዛው የ60ዎቹ ትውልድ አካል የሆነው ኢሕአዴግ ከደርግ በተቃራኒው የአገርን ብሔራዊ ስሜትን የሚያመክን የዘረኝነት መርዝን ይዞ መጣ፡፡ ዛሬ 25 ዓመት የሞላውን በዘረኝነት ልክፍት የታነጸ ትውልድን አበረከተ፡፡ አደጋው ከሁሉ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ኢሕአዴግ የመጀመሪየዎቹ 7 ምናምን አመታት ዋናው ሥራው ሕዝብን ከሕዝብ በመለያየት ብሔራዊ ስሜትን ማምከን ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ኤርትራውያን በአገሪቱ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ  ዜጋ ነበሩ፡፡ እውንም ከመጀመሪያው ሕዋሕትና ሻብያ እንደተባለው ትግራይንና ኤርትራን በኢትዮጵያ ሀብት በማሳደግ ትግራይን ወደ ኤርትራ መቀላቀል ሀሳብ እንደነበራቸው ይመስል ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድንገት መከሰት የሰው ሳይሆን የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር  ለኢትዮጵያውያን ያደረገው እፎይታ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የታፈነው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ገንፍሎ ታየ፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለኢሕአዴግ ትልቅ ምልክት ሆኖት ብሔራዊ ስሜትን የሚገነባ ሥራ መሥራትን ባሳሰበው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ግን ይህን ስሜት በጥሩ አላየውም፡፡ የብሔራዊ ማንነትን የሚያሳጡ ነገሮችን ማደረጉን ቀጠለ፡፡ በ1993 በአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ በተማሪዎች በተቀሰቀሰው አመጽ ምክነያት የአዲስ አበባ ሕዝብ በመንግስት ላይ አመጸ፡፡ ፖሊስም ሆነ ሌላ ሀይል ሊያቆመው ባለመቻሉ አጋዚ ጦር መጣ፡፡  የዛሬን አያድርገውና የዚያን ጊዜ አመጽ የዘር አልነበረም፡፡ ተማሪዎቹ የአመጹትም ሁሉም አንድ ሆነው ነበር፡፡ ምክነያቱም ፖሊሶች የተወሰኑ ተማሪዎችን ደበደቡ ነበር፡፡ ያኔ የዩኒቨርሲቲ ጓደኛቸው እንጂ የዘር ማንነቱ አይጠየቀም ነበር፡፡ ዛሬ ይሄ አይታሰብም፡፡ መጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆን ሳይሆን የሆነ ብሔር መሆንን ያሰፈልጋል፡፡ ኦሮሞው ሲደበደብ አማራ ወይም ትግሬ ተብዬው ድንጋይ ለደብዳቢዎች ያቀብል ከሆነ እንጂ፡፡ እንዲሁ በተቃራኒው፡፡ ይህን ትውልድ እዝህ ድረጃ ላይ ለማደረስ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ በዘረኝነት ተለክፎ አድጓል፡፡ ዛሬ ኢሕአዴግ በአንድነት የሕዝብና የራሱንም ጥያቄ አንስቶ የሚቃወመው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሌለ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡  ከ1993 ዓመጽ በኋላ ኢሕአዴግ አመጽ ሲነሳ የሚያፍንበትን ኃይል ማዘጋጀት እንዳለበት አመነ፡፡ በመሆኑም ፌደረራል የተባለ ምክነያት የማይጠይቅ ለመድባደብና ለመግደል ብቻ ትዕዛዝ የሚጠብቅ ኃይል አዘጋጀ፡፡ ከዚያም 1997 ምርጫ ሌላ ፈተና ሆኖበት መጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የተማመነውም ፌደራል እንደማያዋጣ ተረዳ፡፡ በተለይ ሟቹ ጠ/ሚኒሰቴር ይህን በደንብ ስለተረዱት ይመስላል ከ1997 ዓ.ም በኋላ ብዙ ሕዝባዊነትንና ብሔራዊ አንድነትን የሚገልጹ እንቅስቃሴዎችን አደረጉ፡፡ ኢሕአዴግ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ሌላ አደገኛ ስልት ይዞ መጣ፡፡ በሌብነት(ሙስና) በገንዘብ የተገዛ አእምሮን ማፍራት፡፡ በዋናዎቹ ባለስልጣኖች ዘንድ ከ1997 በፊትም ሙስናው ቢኖርም ከ1997 በኋላ ግን ሙስና ዋና የፖለቲካ ስልጣንን ማቆያ ስልት ሆኖ በመንግስት መዋቅር ሁሉ ተንሰራፋ ወደ ግሉም ዘርፍ በስፋት ገባ፡፡ አሁን በድብቅ የሚደረግ ሳይሆን የለየለት ገሀዳዊና በሕግ የማይዳኝ የአገሪቱ አደጋ ሆነ፡፡ ሁሉም ሆድ እንጂ አእምሮ የሚባል ነገር አጣ፡፡ ሌላው ከ1997 በኋላ ኢሕዴግ ራሱን በስልጣን ለማቆየት እንደ መከላከያ ስልት የወሰደው የ1ለ5 ስልት ነው፡፡ ሕዝብ እርስ በእርስ አመኔታ እንዳይኖረውና እንዳይተባበር፡፡ ልብ በሉ በዘረኝነት የተደረገው መከፋፈል ሳያንስ ይህ አዲሱ ስልት አንድ ጣሪያ ስር የሚያድሩ ቤተሰብን ሳይቀር መከፋፈል ነው፡

አገሪቱን ያለወደብ ማስቀረትን ጨምሮ ከላይ የዘረዘርኳቸው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ጥፋቶች ሲሆኑ፡፡ እንደሌሎቹ ሁሉ ለአገሪቱ የራሱ በጎ የሚባሉ አስተወጽዖዎች አሉ፡፡ በልማት በኩል በተለይ በመንገድ፣ግድብ፣ ፋብሪካ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጅክቶች ኢሕአዴግን የሚያስመሰግኑ ሥራዎች እንደተሰሩ አይካድም፡፡ በተለይም ደግሞ ከ1997 በኋላ ከላይ እንደጠቀስኩት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር በፊት ያልታየ ለየት ያለ ሕዝዊ የሚመስል አመራር ምክነያት ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች ተጀመሩ፡፡ አገሪቱም ኢሕአዴግ እንድሚለውም ባይሆን የእድገት መስመር ላይ ትመስላልች፡፡ አደጋው ግን አሁን ያሉት ባለስልጣኖቻችን ሥራዎችን የሚያከናውኑት ከአገር ፍቅር ስሜት አይመስልም፡፡ ሕዝቡን ይሄን ሰራንልህ ስለዚህ አፍህን ዘግተህ ተገዛ ለማለት እንጂ፡፡ አብዛኞቹ ከግል ጥቅማቸው ጋር የተያያዘ እንጂ ሀገራዊ ቁጭት የለባቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ግን ከዚህም በከፋ እኔ ብቻ በልቼ ልሙት የአውሬነት ጸባይ ይታይባቸውል፡፡ ከ1997 በኋላ ኢሕአዴግን የብሔር ፖለቲካ አላዋጣ ስላለው እንደሆነ ባለውቅም የብሔር ብሔረሰብ ቀን፣ የባንዲራ ቀን ምናምን የሚሉ ብሔራዊ አንዲነትን የሚጠግኑ ስነስርዓቶችን ማየት ችለናል፡፡ ያም ሆኖ እዚህም ላይ ከልብ የሄዱባቸውን የብሔር ፖለቲካ ሊያሰቀሩት አይፈልጉም፡፡ ከፋፍሎ መግዛት ለኢሕአዴግ ዋናው ስልቱ ነው፡፡ የ1ለ5 ስልትም ለዚህ ነው፡፡

ሕዝብ በዛሬዎቹ መሪዎቻችን ያለው አመለካከትስ

ተማርኩ የሚለውና ብልጣብልጡ አብዛኛው ሕዝብ እንደ እኔ ሁለት ጽንፍ ላይ ቆሟል፡፡ በጽንፈኛ ተቃዋሚነትና በጽንፈኛ ደጋፊነት፡፡ እነዚህ ሁለቱም ያለምክነያት የሚደግፉ ያለምክነያት የሚቃወሙ ናቸው፡፡ ሁለቱም ውጤታማ አይመስሉኝም፡፡ እርስ በእርስ ያው የዘር ልክፍት የዚህን የሕዝብ አካል ጎድቶታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሲደግፍና ሲነቅፍ እንኳን በአንድነት አይደለም ሁሉም በየፊናው ነው፡፡ አብዛኛው ከትግራይ የወጣውና ሌላ ቦታ እየኖረ ያለው የተማረውም ሆነ ያለተማረው የዚህ መንግስት ጭፍን ደጋፊ ነው፡፡ ለእንደንዚህ አይነቶቹ ደጋፊዎች መግደልም፣ ማሰርም፣ ሁሉንም ግፍ መፈጸም ትክክል ነው፡፡ ሌላው ኦሮሞ እና አማራ ነኝ የሚለው ከዚህ መንግስተ ጥቅም ያለተጋራ ብልጣብልጡ ሕዝብ በተቃራኒው ጭፍን ተቃዋሚ ነው፡፡ ሁለቱም በዘረኝነት የተለከፉ ስለሆኑ ግን አንድ ሆነው አይቃወሙም፡፡ ሌሎች ሌላ የተቃውሞ ስልት ነው፡፡ ሌሎች አነስተኛ የዘር ምድቦች ሂደቱን የሚከታተሉ ናቸው፡፡ በአገሬው ዋናው ሕዝብ በኩል ግን ተቃውሞውም ይሁን ድጋፉ ከፖለቲካ ጋር ሳይሆን ከኖሮ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ግን የግድ የፖለቲካ ስጋት ስሜት እንዲያደርበት ሆን ተብሎ በሥርዓቱ ጫና ይደረግበታል፡፡ የ1ለ5 ስልት አንዱ አላማ ይሄ ነው፡፡

የአገሬ ልጆች መፍትሔው ምንድነው;

ከላይ አሁን ያለውን መንግስት ባለስልጣኖች ሐጥያት አብዝቼ ያቀረብኩት ለመክሰስ አይደለም እየሆነ ስላለው ነገር እንድንረዳና  ምን መሆን እንዳለበት መፍትሔ የሚሆነን ነገር እንደናስብ እንጂ፡፡ ሁላችንም ዕድሉ ገጥሞን ሥልጣን ላይ ብንወጣ ምን እንደምናደርግ እናስብ፡፡ አሁን ከአሉት ባለሥልጣኖች የተሻለ ነገር እንሰራለን የሚል የጀብደኝነት ስሜት ሳይሆን የላፍንባቸውን የራሳችንን ሕወት መርምረን ማንነታችንን እንወቅ፡፡ አንድ ነገር እኔን የከብደኛል ዛሬ እራሱ በዘረኝነት ልክፍት የመከነ ሰው ኢትዮጵያን ለመምራት እድሉ ቢሰጠው የተሻለ ነገር ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዛሬ ወንድሙን ለገንዘብ ብሎ የሚለውጥ አደገኛ ሰው እንዲሁ፡፡ ዛሬ በየተኛውም አጋጣሚ ለየትኛውም ወገን የማያዝን አእምሮ ያው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉም ውጭ ሆኖ ግን አንዳንድ ምኞቶች የሚፈትኑት ሰውም አደጋ ነው፡፡ አሁን ላይ ሆኖ ባይፈተንም ወደፊት እድሉን ሲያገኝ ላለመፈተኑ ከወዲሁ አሰብ አድርጎ የተወሰኑትንም እኳን ቢሆን ከራሱ ጋር በአምላኩ ፊት መሀላ ማድረግን የግድ ይለዋል፡፡ አገርንና ሕዝብን ለመምራት ከሜዳ መጥቶ ዘው እንደሚባልበት የተከፈተ አዳራሽ አይደለም፡፡   የአብዛኞቹ የዛሬ ባለሥልጣኖቻችንም ችግር ከመጀመሪያውም አስበውት ሳይሆን እየቆየ የተጠናወታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም ቅጥ ያጣ አልጠግብ ያለ የሌብነት (ሙስና) ልክፍት ፈጽሞ ማሰብ እንዳይችሉ የደፈናቸው እየቆየ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአብዛኞች ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችም የግል ጥቅም እንጂ የአገርና ሕዝብ ቁጭት እምብዛም አይታይባቸውም፡፡

ሌላው በቀለኝነትን መካሰስን ሳይሆን ያለፈውን እንዳለፈ ትተን ተበዳዩን በካሳ በዳዩን በይቅርታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የብሔራዊ እርቅ መጥቶ እፎይ የምንለበትን ነገር ማሰብ ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ግን ብሔራዊ እንድነት ያሰፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከሁሉም በላይ ጉልበት ነው፡፡ መጀመሪያ እንትን ነኝ ከዚያ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የተልፈሰፈሰ ብሔራዊ ስሜት ኢትዮጵያን ይቅርና ነኝ ለሚለውም ጎሳ መሪነት ብቃት እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡ ሁላችንም ወደራሳችን እንመለስ፡፡ ምን እየሆንን ነው; የምንፈልገውስ ምንድነው; ብሔራዊ ሥሜት ያለው ዜጋ አይፈራም፡፡ ማንንም የእኔ አይደለም ብሎ አይጠራጠርም፡፡ ይህ ጎልበት በሌለበት ነጻነት የለም፡፡

ጆሮ ከአላቸው ዛሬ ያሉትም ባለሥልጣኖች ወደራሳቸው ተመልሰው ማሰብ ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡ አይደፈሩ የሚመስሉ የሳዳም ሁሴንና የጋዳፊን ነገር ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ውጤቱም ምን ያህል አገርና በሕዝብ ላይ አደጋ እንዳለው ማሰብን ቢችሉ መልካም ነው፡፡ በእኛውም አገር የሆነው በታሪክ ያለፍንባቸው የጥሎ ማለፍ የሥልጣን ቅብብሎሽ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን ማሰብ ብንችል፡፡ በስልጣን ያዝነው የምንለው ሀብት ሁሉ አንድ ቀን እንዳልነበረ ሊሆን እንደሚችል ብናስብ፡፡ ሁላችንም ባለስልጣኖችን ጨምሮ በየግላችን መስገብገባችን ከሥጋ ፍላጎት አልፎ ሰማያዊ ቤት የሚሰራ እንዳልሆነ ማሰብ ጥሩ ነው፡፡  የሕዝባችን ኑሮ፣ ድህነታችን፣ በአለም ሳየቀር አሁንም ረሀብተኞች እንደሆንን፣ አሁንም ስደተኞችን እንደሆን አስበን ይመመን፡፡ ማንም ለእኛ አያዝንም፡፡ በሰው አገር ያልፍልናል ብለን ብንታረደ፣ ብንቃጠል ሌላ ችግር ሁሉ ቢደርስብን ማንም አያዝንም፡፡ እኛው በገዛ ወገናችን ጨክነናል፡፡ እኛ ከበላን 90 ሚሊዮን ሕዝብ እነደጠገበ እናስባለን እናወራለን፡፡ የእኛ ልጆች ሰላም ከገቡ የሌላዋ ደሀ እናት ልጅ ሕወት ምናችንም አልሆን አለ፡፡ እኛን ከደላን ሌላው ምናችንም አልሆን አለ፡፡ ይሕ እርግማን ነው፡፡ እስኪ ወደራሳችን እንመለስ፡፡ የአገራችን ጉዳይ ይቆጨን የሕዝባችን ሥቃይ ይመመን!

ኦቦሉዋን ሰዲ ተካ ዱር ዱበና፣

ወልጂበኒስ ሚቲ ኮቱ ወልጎረፈና፡፡

የአሊ ቢራ ሐቲ ኬ/ቴኛ ተካ ማልቱ አዳ ኑ ባሴ ለሁላችሁም ግብዣዬ ነው

 

አቤቱ ቅዱስ አባት እግዚአብሔር ሆይ አእምሮአችንን ክፈት! አሜን!

 

አመሰግናለሁ!

ደ ሰርፀ ደስታ

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s