የእነሀብታሙ አያሌው 19 ፍትሕ-አልቦ ወራት!

Habitamu

በበፍቃዱ ኃይሉ (Zone9)

በሚያነጋግርና ምናልባትም ደግሞ በዓለም ላይ ተከስቶ በማያውቅ ሁኔታ ኢሕአዴግ ‹‹ምርጫ 2007ን መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ›› ብሎ ከማወጁ በፊት ለዚህ ውጤት የሚያበቃ ዘመቻ ቢጤ አድርጎ ነበር። የማይዘነጋው የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲዎችን መሰንጠቅ ጨምሮ (‹ገዢው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ በኩል እጁን አስገብቶ ስንጥቁን አባብሶታል› የሚለው የብዙኃን እምነት ነው፤) የጋዜጠኞች፣ ጦማርያን እና ፖለቲከኞች መታሰር እንዲሁም የመጽሔቶችና ጋዜጣ መዘጋት ብሎም ጋዜጠኞችን በማዋከብ በገፍ እንዲሰደዱ ማድረግ ዋና-ዋናዎቹ የዘመቻው አካል ናቸው። በዚህ ዘመቻ ወቅት ከሦስት ጠንካራ ከሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ደምቀው ይታዩ የነበሩ ፖለቲከኞችም ተለቅመው ሐምሌ 1፣ 2006 ታስረዋል። እነዚህም የአንድነት ፓርቲዎቹ ሀብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲው የሺዋስ አሰፋ እና የአረና ፓርቲው ኣብርሃ ደስታ ናቸው።

እነዚህ አራት ፖለቲከኞች ከሌሎች ስድስት የፖለቲካ አራማጆች ጋር በአንድ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው የጥቅምት ወር ማገባደጃ 2007 ላይ ነበር። በክስ ሒደቱ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፉ ሲሆን ኣብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሺ ለክርክር የሚመላለሱበትን 19ኛ ወንጀል ችሎት ደፍራችኋል በሚል ኣብርሃ 16 ወራት፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ እያንዳንዳቸው 14 ወራት ተፈርዶባቸው፣ አንፃራዊ ምቾት ካለው የቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ወደቃሊቲ (የፍርደኞች ክልል) ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ተደርጓል። በቃሊቲ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ‹‹የፖለቲካ እስረኞች›› እየተለዩ መገለል ይፈፀምባቸዋል። ከመገለሎቹ ውስጥ በቤተሰብ የመጠየቂያ ሰዐታቸው በቀን ውስጥ ከጥቂት ደቂቃዎች ያልበለጠ ሲሆን እሱም በሥም የተመዘገቡ የቤተሰብ አባላት ብቻ እንዲሆኑ ተገድቦባቸዋል። በተጨማሪም፣ ሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይቀላቀሉ ብዙ እቀባዎች ይጣሉባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ነሐሴ 14፣ 2006 ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ መዝገቡ በሚጠራበት የእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ ስር ካሉ 10 ተከሳሾች መካከል አራቱ ፖለቲከኞች እና መምህር አብርሃም ሰለሞን በነጻ እንዲሰናበቱ የ19ኛ ወንጀል ችሎት በይኗል። በወቅቱ፣ ከሀብታሙ አያሌውና አብርሃም ሰለሞን በቀር ሦስቱ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ የችሎት መድፈር ፍርድ ላይ ስለነበሩ ለመፈታት ጥቂት ቀናት ይቀሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ፣ ወዲያውኑ ነጻ የመውጣት መብት የነበራቸውም ሀብታሙ አያሌውና አብርሃም ሰለሞንም አልተፈቱም። ምክንያቱም ደግሞ ዐ/ሕግ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ ይግባኝ በማለቱ እና ነጻ መውጣት የነበረባቸውም ይግባኙን ሳይፈቱ እንዲከታተሉ እግድ በማውጣቱ ነበር።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ ስድስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ብዙ ድራማ የሚመስሉ ነገሮችን አይተናል።

ነሐሴ 29፣ 2007 ይግባኙ ያስቀርባል አያስቀርብም በሚለው ጉዳይ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ ዳኜ መላኩ የፈረሙበት (የደብዳቤውን ፎቶ ይመልከቱ) ደብዳቤ ጉዳዩ ለክርክር ‹ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም› በሚለው ላይ ‹ያስቀርባል› የሚል ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ችሎቱ ‹ያስቀርባል የሚለው ላይ ለመወሰን› የሚል ምክንያት እንዳዲስ በመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ቀጠሮውን ሲያጓትተው ቆይቶ ሕዳር 29፣ 2008 (ማለትም በሦስት ወሩ) ‹ያስቀርባል› የሚል ብይን በማሳለፍ በዐ/ሕግ እና በመልስ ሰጪዎች መካከል የቃል ክርክር እንዲካሄድ ወስኗል። እንግዲህ፣ በዳኛ ዳኜ መላኩ ቀድሞ የተወሰነው ውሳኔ (ዳኛው መፈረማቸውን አላመኑም) ድጋሚ በችሎት ፊት ቀርቦ እስኪወሰን በመሐል የባከነው ከሦስት ወራት በላይ ጊዜ እስረኞቹ ያለምንም ካሣ የሚከፍሉት የማይገባ መስዋዕትነት ሆኗል ማለት ነው።

ይህንን ሁኔታ ታዝበው ብቻ ማለፍ ያልሆነላቸው አምስቱ የይግባኝ መልስ ሰጪዎች የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ይቀየሩልን የሚል አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ አቤቱታቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ያላቸው አማራጭ መከራከር ብቻ ነበርና የቃል ክርክሩን አካሄዱ። ጎን ለጎን ግን ሀብታሙ አያሌው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበተኝ በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከመፈታት መታገድ አልነበረብኝም በማለት ክስ መሥርቶ ነበር። ክሱ ውድቅ እየተደረገበት እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ተጓዘ። የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎትም ቢሆን አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልገው ለነበረው የዚህ ክስ መልሱን ሲያንጓትት ቆይቶ ባለፈው ማክሰኞ (ጥር 24፣ 2008) ብይን አሳልፏል።

የሰበር ሰሚ ብይን ‹የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 188/5 በሚደነግገው መሠረት የፍርድ እግድ ማውጣት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በነሀብታሙ ጉዳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው› እንደሆነ ተናግሯል። ሰበር ሰሚ ችሎቱ በብይኑ እንዳስረዳው ‹ይግባኙ ያስቀርባል የሚል ብይን ላይ ችሎቱ እስኪደርስ ድረስ መልስ ሰጪዎች ነጻ ሁነው የመቆየት መብት ነበራቸው›። ይህንን ካለ በኋላ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን ወደስር ፍርድ ቤት መልሶታል።

ይህም ማለት፣ በሕጉ አግባብ፣ እነሀብታሙ (ነሐሴ 29፣ 2008 ‹ያስቀርባል› ተብለው የነበሩት ተቀባይነት ስላጣ) ቢያንስ እስከ ሕዳር 29፣ 2008 ላይ እስኪወሰን ድረስ ያለውን ጊዜ በሙሉ ነጻ ሆነው፣ ከቤታቸው በመመላለስ ይግባኙን መከታተል ይችሉ ነበር። ነገር ግን ቀድሞ በወጣው ‹ሕጋዊ መሠረት በሌለው የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ብይን ሳቢያ› እስረኞቹ ማረሚያ ቤቱ ውስጥ እንዲቆዩ ተገድደዋል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የበየነው ብይን የዘገየ በመሆኑ ለእስረኞቹ ምንም ፋይዳ የለውም፤ ምክንያቱም ብይኑ ነጻ የሚያወጣቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ‹ይግባኙ ያስቀርባል› ብሎ ከመወሰኑ በፊት ብቻ ስለሆነ ነው። (ይህ ማለት ግን ያስቀርባል ስለተባሉ ብቻ በእስር መቆየት ስላለባቸው ሳይሆን፣ የሰበር ሰሚው ብይን ያስቀርባል ከተባለ በኋላ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ እግድ ሊያወጣ የሚችልበት መንገድ አለ ብሎ ክፍተት በመተዉ ነው።) ይሁን እንጂ የሰበር ሰሚ ችሎት ብይን ሕግ ሆኖ የሚፀድቅ በመሆኑ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ጉዳይ ከተከሰተ አጭር መፍትሔ ይሆናል የሚል ተስፋ መሰነቅ ይቻላል።

እነሀብታሙ አያሌው 19ኙን ወራት በወኅኒ ያሳለፉት በምቾት አይደለም። ሀብታሙ ራሱ የኩላሊት ሕመሙ በየጊዜው ሆስፒታል እያመላለሰው ነው። እሱም የተፈቀደለት ጊዜ ብቻ ነው። ኣብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሺ የጠያቂ ማዕቀብ ተጥሎባቸው፣ መጽሐፍ በማይገባላቸው ሁኔታ፣ ከእስረኞችም ጋር እንዳይቀራረቡ ተደርገው ነው የታሰሩት። ዳንኤል ሺበሺ ጥር 24 ለችሎቱ እንዳስረዳው ጊቢው ውስጥ በተነሳ የቡድን ፀብ፣ እሱ ምንም የማይመለከተው ሆኖ ሳለ፣ ወደልዩ ቅጣት ክፍል በመጋዝ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው።

ከአራቱ ፖለቲከኞች ጋር አብሮ በይግባኝ የተያዘው ወጣቱ አብርሃም ሰለሞን ቤትኤል ት/ቤት ውስጥ መምህር ነበር። ከመታሰሩ ቀደም ብሎ ለሠራው ሶፍትዌር፣ ከታሰረ በኋላ አሸናፊ ተብሎ፣ እናቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሜዳልያ ተቀብለውለታል። ይኸው ለአገሪቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት አስተዋፅዖ ታደርጋለህ ተብሎ የተፈረደበት ወጣት፣ በሸለመው መንግሥት ‹‹በአሸባሪነት›› ተጠርጥሯል።

በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ ቀሪዎቹ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ተከላክለው ነጻ እንዲወጡ በወሰነባቸው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከያ ምስክሮቻቸውን እና ማስረጃዎቻቸውን እያቀረቡ ነው። በዚህ መዝገብ ያሉ እስረኞች ጉዳይ ግን፣ በኢትዮጵያ ያሉ ‹‹ፖለቲካ-ነክ›› እስሮች እና ክሶች አንድ ማሳያ ነው። የብዙ ወራት እስር፤ ያለምንም ፍትሕ።

የሽብር ክሶች የቱንም ያህል ማስረጃ አልባ ቢሆኑ እንኳን ዳኞች የክሱ መልዕክት በተከሳሽ እና መንግሥት መካከል ፀብ መኖሩን ስለሚነግራቸው በነጻ አዕምሮ መበየን ይፈራሉ፤ ስለሆነም ሰበብ አስባብ ፈጥረው ብይኑ መንግሥትን የማያስከፋ እንዲሆን ያደርጋሉ። ዳኞች ነጻ ሆነው ቢሠሩ እንኳን የቀጠሮዎቹ ሰበብ አስባቦች እና መራዘሞች በራሱ ተጠርጣሪውን ‹ነጻ› እስኪባል ድረስ አንድ የእስር ዘመን ጨርሶ እንዲወጣ ያስገድዱታል።

***
ይህ ጽሑፍ ጥር 28/2008 አዲስ ገጽ መጽሔት ላይ የታተመ ነው።

 

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s