በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት-ሁመራ ተወላጆች አስተባባሪ ኮሚቴ ለአምባሳደር ግርማ ብሩ የፃፈው ደብዳቤ

girma biruu

የካቲት 29, 2008 ዓ/ም MARCH 8, 2016
ለተከበሩ አቶ ግርማ ብሩ
በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዋሺንግቶን ዲ.ሲ.

ጉዳዩ፦ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ፤

እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያ አሜሪካውያን የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች፤ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት-ሁመራ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ አፈና፣ ጭቆና፣ ማፈናቀልና ብሎም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በመቃወም ድምጻችንን ለማሰማት ሲሆን ይህንን የተቃውሞ ድምጻችንና የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ በኢምባሲው በኩል ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲያቀርቡልን የቀረበ አቤቱታ ነው።

እኛ የዚሁ አካባቢ ተወላጆች ከ 1970 ዎቹ ጀምሮ ሕወሃት (TPLF) ተከዜን በመሻገር ባደረሰብን ጥቃትና ወረራ ተፈናቅለን እስከአሁን ድረሰ በስደት ዓለም እንገኛለን። የወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት-ሁመራ ሕዘብ ለጎንደር ብሎም ለአማራው ሕዝብ ታሪክና ቅርስ ቀዳሚ ባለቤት ከሆኑት ማኅበረሰቦች አንዱ ነው። ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ታሪካችን ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት- ሁመራ የጎንደር ክ/ሃገር አካል እንጅ የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም።

ከተፈጥሮና ከታሪክ አካልችን ከጎንደር ክ/ሃገር በመለየት ተፈጥሮአዊውን የተከዜን ወንዝ ድንበር በመጣስ የተደረገው አከላለል ሕገ- መንግስቱን የጣሰ ተከባብሮና ተፋቅሮ በኖረው የትግራይና የጎንደር ሕዝብ አንድነት ላይ ያነጣጠረ ኢ-ሰብአዊ የሆነ የተስፋፊነት ወረራ ነው። የወልቃይት ጠገዴ ሕዘብ ቋንቋው አማርኛ ባህሉ አማርኛ የዘር ሀረጉም አማራ ነው። ከትግራይ ሕዝብ ጋር የሚያስተሳስረን ቢኖር ኢትዮጵያዊነታችንና አጎራባች ደንበርተኛ እንደመሆናችን መጠን የትግርኛ ቋንቋ መናገራችን ብቻ ነው።

ከ 1950 – 1970 ዎቹ ዓ/ም የሰቲት-ሁመራ የእርሻ ልማት በዚያን ጊዜ የነበሩ ደጋግ አባቶቻችን ኤርትራውያንና የትግራይ ወገኖቻችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለት የተቋቋመው ማህበር ላይ “የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት-ሁመራ ሁለገብ” በማለት ሁሉም ተጠቃሚ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በጣም የሚያሳዝነው በስደት አለም የምንኖር የክልሉ ተወላጆች በአገራችን ዲሞክራሲ፣ ሰላምና እኩልነት አለ ብለን በተወለድንበት አካባቢ የአያት ቅድመ-አያት ርስታችን ለማልማት የርሻ መሬት እንዲሰጠን ብንጠይቅ የተሰጠን መልስ “ደማችን አፍስሰን አጥንታችን ከስክሰን የያዝነው መሬት ልትጠቀሙበት አትችሉም፤ እንዲያውም ነቅለን የጣልነው እሾህ ተመልሶ ማየት አንሻም” የሚል ነው። “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እንዲሉ ይህን መልስ ያገኙ ከውጭ የሄዱና ሌሎች ወጣት ገበሬዎች በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉልና ሌሎች ክልልሎች ተበታትነው ይገኛሉ።

በዚህ ባልፈው የካቲት ወር የትግራይ ክልል አስተዳደር ፕሬዝዳንትና በየእርከኑ የሚገኙ ባለስልጣኖች የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት ጥያቄን አንግበው ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝለት በማስተባበር በሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለው ዛቻ፣ ማስፈራራት፣ ጠብ-አጫሪነትና ፕሮፓጋንዳ በእጅጉ አሳዝኖናል። ሰላምን አንግቦ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት የሚያደርግን አካል ማስፈራራትና መዛት ኃልፊነት የጎደለው አስተዳደር መሆኑን ከማሳየቱም በላይ የአስተዳደሩ የማን አለብኝነት ትምከህተኝነቱን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። ይህ ዓይነት ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆምና ጉዳዩ ብክብ ጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ እንዲገኝለት እናሳስባለን።
ይህን ግፍና በደል አስመልክቶ የጎንደር ሕዝብ ሆነ የወልቃይት ጠገዴ በተለያዩ ወቅትና ጊዚያት ክ 25 ዓመት በላይ ሕጋዊ በመሆን ከማመልከት አልተቆጠበም፤ ለማስረጃ ያህልም የሚከተሉት ሰነዶችና የአከባቢው ሕዝብ ፊርማ ዝርዝር አያይዘን አቅርበናል።

ስለሆነም በቅርቡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት-ሁመራ ሕዝብ የአማራ ብሄረተኝነት ማንነት ጥያቄ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አቋቁመው ጥያቄውም ለኢትዮጵያ ፌደረሽን መንግስት አቅርበው ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደርጉ ይገኛሉ። እኛም በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የአካባቢው ተወላጆች ጥያቄአቸውን ስለምንጋራ፤ ድምጻቸው ድምጻችን፣ ብሶታቸውም ብሶታችን በመሆኑ እንዲሁም እየከረረ እየሄደ ያለው የትግራይ አስተዳደር ዛቻና ወከባ በጅጉ ስላሳሰበን የተከበረው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጉዳዩን በጥሞና ተመልክቶ ጥያቄአችንን ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲያቀርብልንና አስቸኳይ መልስ እንድናገኝ ጥረት ያደርግልን ዘንድ ከአክብሮት ጋር በትህትና እንጠይቃለን።

ግልባጭ ለሚከተሉት የኢትዮጵያ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ቀርቧል፦ ለሰብዓዊ መብት ጉባኤ
ለሚንስትሮች ም/ቤት
ለኢ.ፌዲ.ሪ ፖሊስ ኮሚሽን
ለፍትህ ሚንስቴር
ለኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ጽ/ቤት
ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ኮሚሽን
ለፌደራል እና አርብቶ አደር ልማት ሚ/ር ለኦ.ህ.ዴ.ድ ጽ/ቤት
ለብ.አ.ዴ.ን ጽ/ቤት
ለሕ.ወ.ሃ.ት. ጽ/ቤት
ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ (VOA)

በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት-ሁመራ ተወላጆች አስተባባሪ ኮሚቴ

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s