ማኅበረ ቅዱሳን: ዐውደ ርእዩ የታገደው በመንግሥት አካላት መመሪያ መኾኑን ገለጸ፤ ፓትርያርኩ እንዳሉበት “በኦፊሴል የምናውቀው ነገር የለም”ብሏል

  • ተለዋጭ ጊዜና ቦታው፥ የመመሪያውን መነሻና አግባብነት በማጣራት እንደሚወሰን ተገልጧል
  • ብዙ የተደከመበት እና አያሌ ለውጥ የሚያመጣ ዝግጅት ሲታገድ ስሜቱና ጉዳቱ ከፍተኛ ነው
  • ያለአሠራሩ ለመሰረዝ የተገደዱት የማዕከሉ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ትብብር፣ “ቀና ነበር” ብሏል
  • በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይካሔድ በመከልከሉ ታላቅና ተገቢ ዓላማው አይከሽፍም፤ በፍጹም!
  • አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ በኋላ ተወስኖ መታየት ይኖርበታል ብሎ የማኅበሩ አመራር ያምናል
  • ማኅበሩ፥ ዓላማውን ለምእመኑ ለማድረስ የሚያስበው በተገቢ፣ ትክክለኛና ሰላማዊ መንገድ ነው

ato-tesfaye-bihonegn

ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከመጋቢት ፲፭ እስከ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን: አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል በኤግዚቢሽን ማዕከል ለማካሔድ ዐቅዶ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀበት ዐውደ ርእይ ለጉብኝት ክፍት የሚኾንበት የመጨረሻ ሰዓት ሲዳረስ በእንግዳ አሠራር ተደናቅፏል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በሰፊው የሚያስተዋውቅና ከምእመኑ የሚጠበቀውን ድርሻ በአግባቡ የሚያሳይ ዐውደ ርእይ በሰፊው አዘጋጅተን በምናቀርብበት ሰዓት መከልከላችን ከፍተኛ ስሜት የሚፈጥር ነው፤” ብለዋል የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ – ትላንት ማምሻውን በማኅበሩ የዋናው ማዕከል ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በተካሔደ ጋዜጣዊ ጉባኤ፡፡

የማኅበሩ አመራር፣ ዐውደ ርእዩ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይታይ የተከለከለው ከመንግሥት አካላት በተሰጠ መመሪያ ነው፤ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ የትኛው የመንግሥት አካል በምን መነሻ እንደከለከለ ግን ለጊዜው አለመታወቁንና ይህም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በቀጣይ በመወያየት ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳለ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ይመለከተዋል የተባለው የአዲስ አበባ አስተዳደር ክፍል፣ ለዐውደ ርእይ ፈቃድ የሚሰጥበት አሠራር ይኹን ልምድ እንደሌለው ለማኅበሩ ይግለጽ እንጂ፣ ዝግጅቱ በማዕከሉ እንዳይካሔድ የተከለከለው ከበላይ አካል በተላለፈ መመሪያ መኾኑንና ጥያቄውንም በመቀበሉ ጭምር መወቀሱን የአስተዳደሩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑ አንጻር ሰሞኑን ከነበረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ፓትርያርኩ በእገዳው ይኖሩበት እንደኾን አቶ ተስፋዬ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ከቅዱስ አባታችን ጋር በተያያዘ እስከ አኹን ባለን መረጃ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤” ሲሉ የተደረሰበት ይፋዊ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ከተነሡት ጥያቄዎች፣ ዐውደ ርእዩ በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት እንደሚካሔድ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለተሠራጩ መረጃዎችና በቀጣይ ስለታሰበው አካሔድ የሚመለከት ይገኘበታል፡፡ የማኅበሩ አመራር፣ ዐውደ ርእዩ መታየት ይኖርበታል የሚል እምነት እንዳለው የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፣ “የት እና መቼ እንደሚካሔድ ግን እስከ አኹን አልወሰንም፤ በቀጣይ አስፈላጊውን ጥረት አድርገን ከወሰንን በኋላ የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፤” ብለዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳይካሔድ በመከልከሉ ዓላማው ፈጽሞ እንደማይከሽፍ ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፣ ማኅበሩ ዓላማውን ለሕዝብ በተገቢ፣ ትክክለኛና ሰላማዊ መንገዶች የሚያደርስበት ቀጣይ ጥረቶች እንደሚያደርግ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡ ከገንዘባዊ ወጪ በላይና ባሻገር ለዐውደ ርእዩ መሳካት ሌት ተቀን በብዙ የደከሙ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ወንድሞችንና እኅቶችን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚቻል እምነታቸውን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፥ ዐውደ ርእዩ እንዴት፣ የት እና መቼ እንደሚካሔድ  የሚወስኑትም እኒኽ ጥረቶችና ሙከራዎች እንደኾኑ አስታውቀዋል፡፡ የጋዜጣዊ ጉባኤው ሙሉ ይዘት በሚከተለው መንገድ ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የጋዜጣዊ ጉባኤው መግለጫ፤

እንደሚታወቀው፣ ዛሬ የዐውደ ርእዩ መክፈቻ መርሐ ግብር ስለነበረ 10፡00 ላይ ጥሪ አድርገን ነበር፡፡ በታሰበው ጊዜ ልክ አልጀመረም፤ ይኼ ዐውደ ርእይ ፈቃድ የተጠየቀበት 2007 ዓ.ም. ጳጉሜን ላይ ነው፤ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከዓመት በፊት ነው ፕሮግራም የሚያዘው፤ 2007 ዓ.ም. የማስፈቀዱን ሒደት የጀመርንበት ነው እንጂ ፕሮግራሙን ቀድመን ነው ያስያዝነው፤ ለኹለት ሳምንት ለማካሔድ ዐቅደን ነበር ፕሮግራም ያስያዝነው፤ ነገር ግን በአንዳንድ የፕሮግራም መጨናነቅ ምክንያት የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ እንዳለው በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ስለተገለጸልን ሰባቱን ቀናት በአግባቡ ለመጠቀም ወስነን ከማዕከሉ አስተዳደር ጋር ተወያየን፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የፈቃድ ደብዳቤ እንድናመጣ ጠየቁን፤ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ ፊርማ ተፈርሞ ይዘን ሔደን በዚኽ መሠረት ከኤግዚቢሽን ማዕከል ጋር ውል ፈጸምን፤ የመጀመሪያ ክፍያም ከፈልን፡፡

በዚኽ መሠረት የዐውደ ርእዩ ዝግጅት ተጀመረ፤ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው የቆየነው፤ በየመሐሉ ከኤግዚቢሽን ማዕከል ጋር ብዙ ውይይት እያደረግን ቆይተናል፤ በየጊዜው ነው የምንሔደው፤ በነገራችን ላይ ቀና ትብብር ነው አላቸው፤ እስከ መጨረሻው ድረስ ቀና ትብብር ነው የነበራቸው፤ እኛም መርሐ ግብራችንን በሰፊው አዘጋጀን፡፡ ሰኞ፣ መጋቢት 12 ቀን የመጨረሻ ክፍያ ከፍለናል፤ ማክሰኞ የዲዛይን ሥራዎችን ለመሥራት፣ አንዳንድ ነገሮችንም ለማስገባት ብቅ ብለናል፤ ምንም ችግር አልነበረም፤ ችግሩ የተፈጠረው ትላንትና ጠዋት ነው፡፡ የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ለትዕይንቱ ዝግጅት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ይዞ ሔዶ የአዳራሾቹን ቁልፎች ሲጠይቅ፣ አይ፥ ችግር አለ፤ የሚል መልስ ነው የተሰጠው፡፡

የዐቢይ ኮሚቴው አባላት ወዲያው ለእኛ ደውለውልን ሔድን፡፡ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ከአቶ ታምራት ጋርና ከተወሰኑ ስታፎች ጋር ውይይት አደረግን፡፡ ለእኛ እንግዳ ነው፤ በርግጥ፣ ለእነርሱም እንግዳ ነገር እንደ ኾነ ነው የነገሩን፡፡ እነርሱ እንደሚሉት፣ ኹለት ዓይነት አሠራር አለው፡፡ አንደኛው፥ ንግድ ፈቃድ ያላቸው አካላት ዐውደ ርእይ ወይም ኤግዚቢሽን እንዲሳተፉ ከንግድ ቢሮ ደብዳቤ ሲያጽፉ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ኹለተኛው፥ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ዕውቅና ከሰጧቸው አካላት ደብዳቤ ያጽፋሉ፤ ቢበዛ የሚጠበቅባቸው ያ ደብዳቤ ነው፡፡ በዚኽኛው መሠረት ነው ማዕከሉ እኛን ለማስተናገድና ውል ለመፈጸም የፈቀደው፤ ሌሎቹንም የሚያስተናግደው በዚኹ አሠራር ነው፡፡

ትላንት ከማዕከሉ ማኔጅመንት ጋር በነበረን ውይይት፥ ማዕከሉ፣ “የአዲስ አበባ አስተዳደር አልፈቀደም፤ ከእርሱ ደብዳቤ ይዛችኹ ኑ፤” የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ እኛም፣ እንዲኽ ያለ አሠራር እንዳልነበረ ተናግራችኋል፤ ስለዚኽ ከየት መጣ? ከጠየቃችኹንስ ዛሬ በዋዜማው ነው ወይ የምትጠይቁን? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አነሣን፡፡ ከእነርሱ ያገኘነው ምላሽ፥ “ጥፋቱ የኛ ነው፤ በማንኛውም በሚዲያም በምንም ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል ነው፡፡

የማኅበሩ አመራር፣ ይህ ኹኔታ እንዳጋጠመ ከሰማ በኋላ በጣም ሰፊ ጥረት አድርጓል፡፡ አንደኛው፣ ወደ አዲስ አበባ መስተዳደር መሔድ ነው፡፡ መስተዳድሩ፥ ለዐውደ ርእይ እንደማይጠየቅ፤ ተጠይቆም እንደማያውቅ፣ አሠራሩም እንግዳ እንደኾነበት አሳውቆናል፡፡ ስለዚኽ ዐውደ ርእዩ የተቋረጠው በመንግሥት ነው፤ ወደሚለው ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ ማንኛው የመንግሥት አካል ነው ለሚለው፣ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ አኹን የምናውቀው መንግሥት እንደከለከለ ነው፡፡ ይኸው ነው፡፡ ጥያቄዎች ካሏችኹ የተወሰኑትን ማስተናገድ እንችላለን፡፡

ከጋዜጠኞች የተሰነዘሩ ጥያቄዎች፤
  1. በቀጣይ ዐውደ ርእዩን እዚኽ በማኅበሩ ሕንጻ ላይ የማሳየት ኹኔታ አለ ይባላል፤
  2. በመንግሥት ነው የተከለከለው የሚል ድምዳሜ ተሰጥቷል፤ ምን ተጨባጭ ነገር ይዛችኹ ነው? በቀጣይስ ምን ርምጃ ለመውሰድ ታስቧል? በማኅበራዊ ሚዲያ በገንዘብ እንዳከሰራችኹ ያየኹት ነገር አለ፤ ከገንዘብ ባሻገር በዚኽ ኹኔታ ውስጥ ምን ዐጣን ትላላችኹ?
  3. አዲስ አበባ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑና በቅርቡ ከነበረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ቅዱስ ፓትርያርኩ ዐውደ ርእዩን እንዳገዱት ይወራል፤ ምእመናን በዚኽ እንዳይሰናከሉ ማኅበሩ ሊሰጥ ያሰበው መልስ አለ? ዐውደ ርእዩ በመታገዱ የማኅበሩን ርእይና ዓላማ ያደናቅፋል ብለው ያስባሉ?
የዋና ጸሐፊው ምላሽ፤

ዐውደ ርእዩ የት እና መቼ እንደሚካሔድ እስከ አኹን አልወሰንም፤ በቀጣይ የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፡፡ ምናልባት እዚኽ በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት እንደሚካሔድ የተሠራጩ ወሬዎች ይኖራሉ፡፡ የማኅበሩ ሥራ አመራር ግን የት፣ መቼ ዐውደ ርእዩ እንደሚታይ እስከ አኹን አልወሰነም፡፡ ወደፊት እናሳውቃለን፤ ምክንያቱም ቀጣይ ጥረቶች አሉ፡፡ በትክክል፣ ማንኛው የመንግሥት አካል ነው ያገደው? በምን መነሻ ነው ያገደው? የሚለውን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመወያየት ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ያ ሙከራ ከተካሔደ በኋላ እንዴት፣ የት እና መቼ እንደሚካሔድ ወደፊት የምናሳውቅ ነው የሚኾነው፡፡

መንግሥት ለመኾኑ ምን ተጨባጭ ምክንያት አለ? ለሚለው፤ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ አዲስ አበባ መስተዳድር ፈቃድ መስጠት ይኖርበታል የሚል እንግዳ አሠራር ጠይቋል፡፡ አዲስ አበባ መስተዳደርን ስንጠይቅ ደግሞ፣ እንዲኽ ያለ እንግዳ አሠራር አላውቅም፤ ለኤግዚቢሽን ማዕከል ፕሮግራም ፈቅደን አናውቅም፤ ብሎናል፡፡ ስለዚኽ በመንግሥት እንደታገደ ከዚኽ በላይ ምንም ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም፡፡ በመደበኛ አካሔድ ባይኾንም በተለያዩ መንገዶች ይህን አረጋግጠናል፡፡ ያ አካል ግን በትክክል ማን ነው? የሚለውን ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ቀጣይ ውይይት የሚታወቅ ነው የሚኾነው፡፡

ዐውደ ርእዩ ባለመታየቱ ምን ጉዳት አምጥቷል? ለሚለው፣ በርግጥ ከገንዘብ አንጻር ኤግዚቢሽን ማዕከሉ፥ የከፈላችኹትን እመልሳለኹ፤ብሏል፡፡ ይህም ኾኖ ዐውደ ርእዩ ታላቅ መርሐ ግብር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሰፊው የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ ምእመኑን በአግባቡ የሚያስተምር ነው፡፡ ከምእመናን የሚጠበቀውን ድርሻ በአግባቡ የሚያሳይና ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ዐውደ ርእይ ነው፡፡ ብዙ ድካም ተደክሞበታል፡፡ ብዙ አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ብዙ ወንድሞች፣ ብዙ እኅቶች ብዙ ደክመዋል፤ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ እንዲኽ ያለ መርሐ ግብር በታሰበው ጊዜ ሳይጀምር ሲቀር ያለጥርጥር ብዙ ጉዳት አለው፡፡

ርግጥ፣ ወደፊት በሚደረጉ ጥረቶች ዐውደ ርእዩ ይታያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ መታየት አለበት፤ እንዲታይ አስፈላጊው ጥረት መደረግ አለበት፤ አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ በኋላ ተወስኖ መታየት ይኖርበታል ብሎ የማኅበሩ አመራር ያምናል፤ እኒኽ እንቅስቃሴዎች ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ይቀንሱታል እንጂ ይህን የመሰለ መርሐ ግብር በሰፊው አዘጋጅተን በምናሳይበት ሰዓት መከልከላችን ከፍተኛ ስሜት ነው ሊፈጥር የሚችለው፡፡

MK AWude ReEye Meg2008በኤግዚቢሽን ማዕከሉ የአብነት ት/ቤቶች መንደር በመገንባት የአብያተ ጉባኤያቱን ሥርዐተ ትምህርት እና ብሂላት በተግባር ማሳየት፣የ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ የክውን ጥበባት መሰናዶዎች አንዱ ነበር፤ ለዚኽም ከ80 ያላነሱ ከተለያዩ የአብነት ት/ቤቶች የመጡ መምህራንና ደቀ መዛሙርት ተዘጋጅተው ነበር፤ ትላንት ማምሻውን በዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ቅጽር ስለ መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ ክብር በተከናወነ የቅምሻ መርሐ ግብር፣ ዐውደ ርእዩን በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ብዙዎች መጽናናታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ሞራላዊ ጉዳታቸውን ይቀንስ ይኾን?


ኤግዚቢሽን ማዕከል በመከልከሉ ብቻ የዐውደ ርእዩ ዓላማ ሊከሽፍ ይችላል ወይ? በፍጹም! ማኅበረ ቅዱሳን በዚኽ መልኩ አይደለም ጉዳዮችን የሚይዘው፡፡ ዓላማው በሰላማዊ መንገድ፣ በትክክልና በአግባቡ ወደ ሕዝቡ፣ ወደ ምእመኑ የሚደርስበትን መንገድ ያስባል፡፡ በዚኽም ጉዳቱን በሒደት ልንቀንሰው እንችላለን እንጂ ሲታገድ የሚፈጠረው ነገር ቀላል አይደለም፡፡

ከቅዱስ አባታችን ጋር በተያያዘ እስከ አኹን ባለን መረጃ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ዐውደ ርእዩ የታገደው ከመንግሥት አካላት በተሰጠ መመሪያ እንደኾነ ነው የምናውቀው፡፡ በሒደት ግን በውስጡ ምን እንዳለና እንዴት እዚኽ ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ፤ እንዲኽ ዓይነት መመሪያ ሲሰጥ በምን አግባብ እንደተወሰነ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተወያየን ስንሔድ አንዳንድ ነገሮችን ልናውቅ እንችላለን፡፡ አኹን ባለው ኹኔታ፣ ኦፊሴሊያዊ የኾነ የምናውቀው ምንም ነገር የለም፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s