የት ነው ያለሁት? እንዲሁ ይጨንቀኛል! – ነፃነት ዘለቀ

Woyane oo

ሰሞኑን ልክ አይደለሁም፡፡ መላ ሰውነቴ ልከ አይደለም፡፡ እጅግ ይጨንቀኛል፡፡ ያ ደደብ ደም ብዛት የሚሉት በሽታ ሊይዘየኝ ይሆን እያልኩም እጨነቃለሁ፡፡ የጭንቀት ጥበቴን መነሻ ግን አውቀዋለሁ፡፡ መፍትሔ የሌለው መሆኑ ስለሚሰማኝ ግና እየባሰብኝ እንጂ እየቀለለኝ ሲሄድ አይታይም፡፡ በተረቱ “የጨው ተራራ ሲናድ ብልህ ያለቅስ፣ ሞኝ ይስቅ” ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ የቁም ሞት የምንበሳጭና ተበሳጭተን የበኩላችንን አስተዋፅዖ የምናደርግ በጣም ጥቂቶች ነን – እኔን ሳይጨምር፤ ለኔ መጨነቄ ብቻ ይበቃል፡፡ ሀገር ቤት በተለይም አዲስ አበባ ላይ ያለን ዜጎች ከቁጥራችን በላይ የሆነ የሰላይና የሆድ አደር ግሪሣ ስለከበበን ጥላችንንም እንፈራለን – ስለዚህም ማድረግ ቀርቶ ለማድረግ ማሰባችን ራሱም የሚታወቅብን እየመሰለን ከማሰብም ተቆጥበናል – (የጆርጅ ኦርዌል ‹1984› መጽሐፍ ጨርሶታል)፡፡ ደርግ አመቻችቶት የሄደው የፈሪነት መንፈስ ሀገር ምድሩን አጥልቶበት የወንድነት ምልክታችን ሁሉ ወዳንጀታችን ገብቶ አንዳንዶቻችን ለመሽኛ እንኳን ፈልገን ልናገኘው አልቻልንም፡፡ “አንዳንዶቻችን” እያልኩ ባይሆን አባዘራፎችን ላግባባ እንጂ፡፡ ከየጎራው አኩራፊው በዝቶ ተቸገርን እኮ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገር አለችኝ አልልም፡፡ ዘረኝነቱ፣ አድልዖው፣ መታሰር መገረፉ … አይደለም የአሁኑ ችግር፡፡ እነዚህ የጠቃቀስኳቸው ችግሮች የዱሮ ናቸው፤ በጣም የተለመዱ፡፡ የአሁኑ የባሰ ነው፡፡

ደርግ ሥጋን ይገድል ነበር፡፡ ወያኔ ግን ሥጋን መግደል ብቻውን ስለማያረካው ከዚህ ደረጃ አልፏል፡፡ እናም ወያኔ የሚገድለው መንፈስን ነው – የሰይጣን ዋና ጠባይም ይሄው ነው፡፡ ወያኔ የሚገድለው ቅስምን ነው፡፡ ወያኔ የሚገድለው ኅሊናን ነው፡፡ ወያኔ ቢገድል ደስ የሚለው ነፍስንም ጭምር ነበር – ይህ ግን የማይቻል ሆኖበት ተቸግሯል፡፡ ስለዚህም መግደል የሚችለው የኛነተቻን ክፍል ተፈቅዶለት አለርህራሄ እየገደለን ነው፡፡

ሥጋን መግደል ቀላልና እርካታውም ጊዜያዊ መሆኑን ሰይጣናቱ ወያኔዎች በሚገባ ያውቃሉ፡፡ አንድን ሰው በጥይት ደብድበው በደቂቃዎች ውስጥ መግደል ቢችሉም ያን አዘውትረው አያደርጉትም፡፡ በርሀብ ወይም በበሽታ ወይም በሥነ ልቦናዊ ጭንቀት ቀስ ብሎ እንዲሞት በማድረግ መዝናናትን ነው የሚወዱት፡፡ ድመት በግዳይዋ ተዝናንታና ሰውነቷን አሟሙቃ ዐይጥን እንደምትበላት ወያኔም በጠላትነት የሚፈርጀውን አካል ወይም ግለሰብ አመንምኖና አክስቶ በማሰቃየት ይገድላል፡፡ ይህ ደግሞ የፈሪዎች ፈሊጥ ነው፡፡ ጀግና በምክንያ የጀብድ ተግባር እንጂ በዕብሪት አይኩራራም፡፡ ጀግና በርህራሄ እንጂ በጭካኔ አይገድልም፡፡ የርህራሄ ግድያን ለማወቅ ወያኔዊ አገዳደልን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከእሥር የተፈቱ ግን በቁማቸው የሞቱ እነ እንትናን በማየት ወያኔ በቁም በመግደል ዲያብሎሳዊ “ጥበብ” እንዴት እንደተራቀቀ ማጤን ይቻላል፡፡ ጉድ ነው! ወያኔ በዚህች ዓለም የእስካሁንም ይሁን የወደፊት ታሪክ ያልታየና ሊታይም የማይችል የመጀመሪያው ትንግርተኛ ፍጡር ነው፡፡ መጥኔ ለመጨረሻ ዕጣው! እንደዚህም ክፋትና ተንኮል አለ?

ወያኔን ማንም ያማክረው ማን፣ ማንም ያግዘው ወይ ጃዝ ይበለው ነገር ግን ኢትዮጵያ እንዳታንሠራራ ተደርጋ እየተገደለች ነው – ይህን መረዳት አቅቶናል፡፡ ባለመረዳታችንም የተጣባን ሀገራዊ አባዜ እንደእስከዛሬዎቹ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ  ወደታሪክ ጎተራ የሚከተት እየመሰለን ተዘናግተናል፡፡ የተናጠል ብልጽግናና ዕድገት ያለ ሀገር ፋይዳ ያለው ይመስል የየግላችንን ሕይወት ለማዳን መራወጣችንን ቀጥለናል፡፡ ይህ ደግሞ ለወያኔ ተመችቶታል፡፡ መቼ ሰው እንደምንሆን ሳስበው አለማሰቤ እንደሚሻለኝ ትውስ ይለኝና ማሰቤ ያስደምመኛል፡፡

ወያኔያዊ አገዳደልን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ትምህርትን ገድለውታል፡፡ እዚህና እዚያ ባሉ የግል ትምህርት ቤቶች የሚታዩ ጥቂት ግላዊ ጥረቶችን አትመልከቱ፡፡ የምለው አብዛኛውን ነው፡፡ እናም አብዛኛው የትምህርት ማኅበረሰብ ሞቷል፡፡ በደምብ ነው የሞተው፡፡ የሞተን ለማንሣት ከመሞከር ደግሞ እንደገና መፍጠር ይቀላል፡፡ የጠፋን ትውልድ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል አንድዬ ይወቅ፡፡ በሁሉም ረገድ ጠፍተናል፡፡

ለወትሮው “ስሙን የማይጽፍ ትውልድ” እንል የነበረው ለግነት ነበር፡፡ አሁን ግን በትክክል ስሙን (አስተካክሎ) የማይጽፍ የዲግሪ ተመራቂ በብዛት መታዘብ ተችሏል፡፡ በበኩሌ ይህን አውቃለሁ፡፡ በየኮሌጁና ዩኒቨርስቲው ብንሄድ ተማሪው ይቅርና በርካታው መምህር ራሱ የፊደል ዘር ለመለየት የሚቸገር ነው፡፡ ያጋነንኩ ይመስላል – ግን አይደለም፡፡ ይህ ነው የሚባል የትምህርት ፕሮግራም የሌላቸውና እንዳሻቸው በመፏለል ትውልድን እንዲያመክኑ የተፈደቀላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ እንዳሉ ይነገራል – በተለይ በአጥንትና በደም ለገዢው መደብ የቀረቡ ናቸው ከሚባሉት መካከል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ከአምስትና ስድስት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ የለየላት የማይማን ዋሻ ትሆናለች – ያለጥርጥር፡፡ ለነገሩ አሁንስ ምን ቀራት፡፡

ማይምነትን ደግሞ አምባገነኖች በጣም ይወዱታል፡፡ ሰጥ ለምበጥ ብሎ ያገኘውን ነገር እንደከብት እያመነዠከ የሚገዛ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው ትምህርትን በመግደል መሆኑን ወያኔን መሰል ሰይጣናዊ አሰለጦች ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ዱላቸው የሚያርፈው ትምህርት ተቋማት ላይ መሆኑ አይገርምም፡፡

ትምህርት የሁሉም ዕድገቶች መሠረት ነው፡፡ በውራጅ የሥነ ሕንጻ ጥበብ መዥጎርጎራችንን አትዩ፤ በከተሞች አካባቢ በሚታዩ የአስፋልት መንገዶች አትታለሉ፡፡ እዚህና እዚያ ውር ውር በሚሉ ዘመናዊ መኪኖችም ዕድገትን እየለካችሁ አትሞኙ፡፡ ሕዝበቡን አደንቁረውናል፡፡ ዋናው ስዕል ይህ ነው፤ ያኛው ሽፋን ነው፡፡ በሽፋን ደግሞ መፍረድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሀገራችሁ እየወደመች እንጂ እያደገች እንዳልሆነ በተለይ ዲያስፖራዎች ተረዱ፡፡ ነገ ዞሮ መግቢያ እያጣችሁ ነው፡፡ የሰው ወርቅ ደግሞ አያደምቅም፡፡ በዚያ ላይ አክራሪነት ዓለምን እያጥለቀለቀ በመጣበት በአሁኑ ሁኔታ ነገና ከነገ ወዲያ አሁን አንጻራዊ ሰላም ያላቸው የሚመስሉት አሜሪካና አውሮፓ ሦርያና ኢራቅ የማይሆኑበት አጋጣሚ የለም፤ ደግሞም ይህ መጥፎ ዕጣ በነዚህ ሀገሮችም  ተጀምሯል – ጎረቤትህ ሰላም ካጣ አንተም ሰላም አይኖርህም – እንኳንስ የሰላም መታጣቱ ዋናው ምክንያት አንተው ራስህ ሆነህ ይቅርና ማለቴ ነው – ገና ምን ዓይተህ ይብላኝ ለሰላማዊ ዜጎች እንጂ እነእንቶኔማ የዘሯትን ያጭዳሉ፡፡ ስለዚህ “ወደ ባዳ አላምጠህ ወደዘመድ ዋጥ ነው”ና ነገሩ ወዳገራችሁ ለመምጣት ማሰባችሁና  መገደዳችሁም ስለማይቀር ሀገራሁን አትርሱ፤ እኛን ምሥኪን ወገኖቻችሁንም አትዘንጉ፡፡ ሀገር ከሌላችሁ ደግሞ የት ትገባላችሁ? ሁሉም ቦታ እሳት ሆነ! እዚህ እየጠፋን ነው – ያለ አንዳች ጦርነት! ሀገርን ለማጥፋት ለካንስ ሥውር ጦርነቶችም አሉ፡፡ የሚገርም ነው፡፡ ሰው ሳያውቅልህና ሳያዝንልህ እንዲህ በቀላሉ በቁም መጥፋት?

ሰሞኑን ለምሳሌ በብዙ ቦታዎች ትምህርት የለም – በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፡፡ የጎረቤቶቼ ልጆች ወደቤታቸው መጥተዋል – ከናዝሬት፣ ከነቀምትና ከደብረ ብርሃን፡፡ እንደሰማሁት ደብረ ብርሃን ሁከት የለም፤ ነገር ግን መምህራኑንና የትምህርቱን አስተዳደር ምን እንደነካቸው አይታወቅም ትምህርት አልጀመሩም፡፡ በብዙ ቦታ ግዴለሽነትና ምንቸገረኝነት ነግሦ የ2ኛው ሴሚስተር ትምህርት ገና አልተጀመረም፡፡  ተማሪውም ግዴለውም፤ መምህሩም ግዴለውም፡፡ ቀጭን ሰበብ እየተፈለገ ትምህርትን መዝጋት በጣም የተለመደ ሆንዋል፡፡ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ ነው፡፡ አንድ ሃይማታዊ በዓል ካለ ከበስተፊት አንድ ሣምንት ከበስተኋላው አንድ ሳምንት ይጨረገድለታል – በቀን መቁጠሪያው ግን አንዲት ቀን ብቻ ናት የምትዘጋው፡፡ የተማረው ወገን ኮብልስቶን እየጠረበ ያልተማረው ወገን በዘረኝነትና በጠባብነት መሰላል ተንጠላጥሎ ባንድ አዳር እየበለጸገ ሲታይ በርግጥም የመማር መንፈስን ይገድላል፡፡ ብዙው ተማሪ ከመማር ይልቅ ዲግሪውን በገንዘብ ቢገዛ ይመርጣል፡፡ ዕውቀት ድባቅ ተመትታ፣ የማወቅ ፍላጎት ተሸመድምዶ እንደምንም ብሎ በሀብት የመክበር ፍላጎት ነው የገነነው – ለገንዘብ ደግሞ አይደለም ባዳን ዘመድንና የገዛ ወላጅንም ሳይቀር መሸጥና አደጋ ማድረስ እጅግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ወያኔ መንፈስንና ኅሊናን እያኮሰመነ የጥቂቶችን ሰውነት በግሳንግስ እያደለበ ይገኛል፡፡ ሰውነት ሲጠበድል ጭንቅላት ይጫጫል፡፡ አእምሮ ሲጫጫ ማመዛዘንና ማስተዋል ገደል ይገባሉ፡፡  ያኔ መተዛዘንና መተሳሰብ ይቀሩና ሰዎች ወደ አውሬነት ይለወጣሉ፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡ ሰውነት በአውሬነት ተለወጠ፡፡ ሃይማኖት ወደሆድ ወርዶ ተሸጎጠ፡፡ በቦሌም በባሌም መክበር ባህል ሆነ፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም ተሸመድምዶ ወደ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ነባራዊ ሁኔታ እያመራን ነን፡፡ ጭብጥ ቆሎ ገዝተህ ራትህን ለመቆርጠም አሥር ብር አይበቃህም፡፡ ብዙ ወዛደሮች አንዲት ብጥሌ ዳቦ በጋራ የሚገዟትን ግማሽ ኪሎ ሙዝ ለሁለት ወይ ለሦስት ተከፋፍለው የሚመገቡበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ይህ ዘግናኝ ነገር ነው፡፡…

ከፍተኛ የምግብ ዕጥረት አለ፡፡ ምግብ ከሌለ ሰውነት ይጎሳቆላል፡፡ ሰውነት ሲጎሳቆል በትክክል ማሰብ ያስቸግራል፡፡ የሀገራችንን ሕዝብ ስንታዘብ በግምት 98 በመቶው ርሀብተኛ ነው፡፡ ይህ ቁጥር የተጋነነ ይመስላል፡፡ እኔ ግን እላለሁ – ሀብታሞቹም ርሀብኞች ናቸው፡፡ ሁላችንም ተርበናል፤ ሁላችንም ኮስምነናል፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ! ርሀብ ዓይነቱ ብዙ ነው እያልኩ መፈላሰፍ አምሮኝ እንዳይመስላችሁ፡፤ ወደዚያ ደግሞ አልገባም፡፡ የእንጀራውን ርሀብ ማለቴ ነው፡፡ ሀብታሞቻችን ደናቁርት ናቸው – ብዙዎቹ፡፡ ሌላው ይቅርና የአመጋገብ ዕውቀት እንኳን የላቸውም፡፡ ሀብታም ስለተሆነ የተመጣጠነ ሣይንሣዊ አመጋገብን አንድ ሰው በአግባቡ ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አዳር ከብሮ የሚያድር ሰው በአንድ አዳር አውቆ አያድርምና በገንዘቡ እየጠጣ በሽታ ይገዛበት እንደሆነ እንጂ ስለአመጋገብ አንድም መጽሐፍም ሆነ ባለሙያ አያማክርም – አብዛኛው ሀብታም ከፊደል ዘር ጋር የተኮራረፈ መሆኑ ደግሞ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ሥጋና ዊስኪ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ይተካል እንደማትሉኝ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም እሱም እንደኛው ርሀብተኛ ነው – የኛን ባያህልም፡፡ ያለ ዕውቀት የሚገኝ ገንዘብ ከጠላት ተለይቶ አይታይም ወንድሞቼ፡፡ የገጠመን አሣር ለየት ይላል ምዕመናን፡፡

ስለሆነም የኛ የድሆቹ ርሀብ መሠረቱ ዕውቀትም ሀብትም ማጣት ሲሆን የሀብታሞቹ ርሀብ መሠረት ግን በዋናነት አላዋቂነት ነው፡፡ ተመልከት  – ሥጋ፣ ቅቤ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ወተት፣ ዕንቁላል፣ ዓሣ፣ ወዘተ. መቼና በስንት መጠን ሰውነታችን ማግኘት እንዳለበት በጥናት የተደረሰበት ነገር አለ፡፡ ገምቢ ምግቦች፣ ኃይልና ሙቀት ሰጭ ምግቦች፣ ከበሽታ ተከላካይ ምግቦች፣ ቪታሚኖቾ ወዘተ. የሚሏቸው አሉ፡፡ ድሃው አንዴውኑ ይበልጡን ከሀብትና ከዚሁ ባልተናነሰም ከዕውቀት ስለተፋታ ይህ የተመጣጠነ ምግብ ነገር ሲነሣ አያሳስበውም፡፡ ሀብታምም  ዕውቀቱ ከአፍ እስካፍንጫው እንኳን ስለማይደርስ ከኛው ጋር እኩል “ይራባል”፡፡ …

በርሀብ የሚገረፍ ድሃ ሕዝብ ሞቱን ተሸክሞ ይዞራል፡፡ ስለሀገርና ስለወደፊት የሚያስብበት አእምሯዊ ጫንቃም የለውም፡፡ ሕዝቡን እዩት – በተለይ በገጠር፡፡ ልብሱ እላዩ ላይ አልቆ እየተንጠራወዘ ሲሄድ ታያላችሁ፡፤ ያሳዝናል፡፡ እኔ ወደገጠር ወጣ ስልና ይህን አሰቃቂ ሀገራዊ ምስል ስታዘብ አንጀቴ ይንሰፈሰፋል፡፡ ወያኔ ለዚህ አበቃን፡፡ የተራበን ሕዝብ ከታዛዥ የቤት እንስሳ መለየት ያስቸግራል፡፡ አመጋገብህ አስተሳሰብህን ይወስናል፡፡ የአስተሳሰብ ችሎታህ በምግብህ ይመሠረታል፡፡ አሸር ባሸር በልተህ እንደጤናማ ሰው ላስብ ብትል አትችልም፡፡ የምትመገበው የማይረባ የመሆኑን ያህል የምታስበውም ውዳቂ ነው፤ በአካል ማደግ፣ በትምህርት ደረጃ መላቅ እዚህ ላይ ዋጋ የላቸውም፡፡ በሚገባ ያልተመገበ ዶክተር እንደሕጻን ሰኞ ማክሶኞ ሲጫወት ብታገኘው ብዙም አትደነቅ፤ አትዘንበትም፡፡ እናም ወያኔዎች ዱሮ ለከብቶቻችን እንኳን ስንሰጥ ከብቶቻችን የሚያሳዝኑንን የጓያ ሽሮ አሳጥተውን በርሀብና በእርዛት እየፈጁን ናቸው፡፡ ሀገርን መግደል ከዚህ በላይ የለም፡፡ ውኃም የለም፤ቢኖር እንኳንንጽሕናው ዜሮ ነው፡፡ ቧምቧህን ስትከፍት አያድርግብህ እንጂ ትንንሽ ዕንቁራሪቶች ሊመጡብህ ይችላሉ፤ የደፈረሰ ውኃማ “ዕድልህ ካማረ” በየሣምንቱ ሊመጣልህ ይችላል፡፡ መብራትም ይቆራረጣል ወይም ይደበዝዝና ዐይንህን ሊያጨናቁር ይችላል፡፡ ህክምና ዜሮ ነው፡፡ ሀኪምም የለም፡፡ ሀኪሙ በዕውቀት ዜሮ ነው፤ ይሻላ በሚባለው በግል የሕክምና ተቋማት ለመታከም ደግሞ አይሞከርም – እንኳን የህክምናውን የካርዱንም አትችለውም፡፡ በዚያ ላይ የሙያ ሥነ ምግባር ከሀገራችን ስለሸፈተ ለጣትህ ቁስል ሆድህን አልትራሳውንድ እንድትታይ ወይም ለእግርህ ወለምታ የጭንቅላት ራጅ ሊታዘዝልህ ይችላል – የገባንበት ማጥ ቀላል እንዳይመስልህ – ክፍያው ደግሞ ቤት ካለህ ያሸጥሃል – ሊያውም ብዙውን ጊዜ ለማይዳንበት ህክምና፡፡ አዋላጅ የለም፤ ምን አለፋችሁ ኑሯችን በውር ድምብር ነው፡፡ መንግሥት ይረን አይኑረን የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በኪነ ጥበቡ ነግቶ ይመሽልናል፡፡ የብላኔ ኑሮ፡፡

ሙስናው ጫፍ ደርሷል፡፡ ባዶ እጅህን ይዘህ የትም ቦታ ጉዳይ አይፈጸመልህም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ብትሄድ እውነቱ ይሄው ነው፡፡ ከአንድ ብዙም ጥቅም ከሌለው(ያው በሙስና ነው) ደብር ወደሌላ ለመዛወር ለአበው ካህናትና ለአኃው ዲያቆናት ባለሥልጣናት በብዙ ሺህ የሚገመት ጉቦ ከፍለህ ነው የሚሳካልህ፡፡ የዱሮውን ጋዜጠኛ የአሁኑን የቤተ ክርስቲያን ካድሬ እንደልቡ የማነ ዘመንፈስን የቅርብ ጊዜ የሙስና ታሪክ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ሞተናል በቁም፡፡ መስቀል ያሳለመህ ቄስ እጅ እጅህን ቢያይ አቅም ካለህ ወርወር ማድረግ እንጂ “ክርስቶስን በገንዘብ አልገዛም” ብትል በመናፍቅነት ያስፈርጅሃል፡፡ ገንዘብ እግዜርን ተክቷል፡፡ወያኔና ቤተ አምልኮዎቻችንም በገንዘብ ፍቅር ዐብደዋል፡፡ መጨረሻውን ያሣምርላቸው እንጂ አሁን ግን እንዲህ ሆነዋል፡፡

በየቦታው የመንግሥት ሥራ በቅጡ አይሠራም፡፡ ቢሮዎች ዝግ ናቸው – ስብሰባ፣ ስብሰባ፣ ስብሰባ፤ የማያልቅ ስብሰባ፡፡ አብዛኛው ስብሰባ ውሸት ነው፡፡ ሰውዬው ከቢሮ ወጥቶ የግል ቢዝነሱን ሲያቀላጥፍ ጸሐፊው “ስብሰባ ላይ ናቸው” የሚል ታፔላ አፏ ላይ ይለጠፍላትና እንደበቀቀን “የሥራ ሂደት ባለቤቱ ኃላፊ ስብሰባ ላይ ናቸው“ ስትል ትውላለች፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያለው መዋቅራዊ ቅርጽና የተለጠፈው የመፈክርና የመልካም ሥነ ምግባር መርሆ ዓይነት ብዙና እጅግ ማራኪ ይመስላል – ውስጡ ግን ባዶ ነው፡፡ ሁሉም የውሸትና የታይታ ነው፡፡ ያው መጠኑ እጅግ ቢያንስም ደሞዝ መብያ እንጂ ሥራን በአግባቡ የሚሠራ ሠራተኛና ቢሮ አለ ማለት አይቻልም፡፡

በንግዱ ዘርፍ የጦፈ ዘረፋ ይካሄዳል፡፡ የገንዘብ ዘረፋውን አሁንም ስለለመድነው ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን የነፍስ ዘረፋው ነው ያንቀጠቀጠን፡፡ በተለይ በምግብ ሸቀጦች በየጉራንጉሩ እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበው ምግብ – ዘይትና ቅቤን ጨምሮ – በሽታ በበሽታ እያደረግና አለዕድሜያችን እየቀጠፈን ነው፡፡ መርማሪና ተቆጣጣሪ የለም – “ሀገረይ ሕዝበይ” የሚል ገዢ አካል የለንም፤ ሁሉም ባለሥልጣን ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ እኛን ሕዝቡን ባገኘው መሣሪያ ይቀጠቅጠናል፡፡ ሁሉም በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ ማንም ማንንም መቆጣጠር አይችልም፤ የሞራል ብቃትም የለውም፡፡ ልናገር ቢል እንኳን የራሱ ቁስል ስለሚታወቅ ከመነሻው አይሞክረውም፡፡ ኢንቬስተር ተብዬዎቹ ደናቁርት ነጋዴዎች ከቻይና ደደቦች ጋር በመመሣጠር ሊፈጁን ነው፡፡ ልብሱ፣ ጫማው፣ የቤት ዕቃው ወዘተ. ሥሪቱ ከምን እንደሆነና ምን ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያስከትል ካለመታወቁም በተጨማሪ መናኛነቱና ለአጭር ጊዜ ብቻ እንዲያገለግል ተደርጎ መሠራቱ ከጠየናችንም ከገንዘባችንም ሳንሆን እንድንቀር እያደረገን ነው፡፡ ህግ ደግሞ የለም፡፡ ገድለህ እንዳልገደልክ፣ ሞተህ እንዳልሞትህ፣ ሳትገድል እንደገደልክ፣ ሰርቀህ እንዳልሰረቅህ፣ ሳትሰርቅ እንደሰረቅህ፣ … የምትሆንባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ሰው በመኪና ገጭተህ ብትገድል ወይም በቡጢና በመሣሪያ አንዱን ወደሰማይቤቱ ብትሸኘው ጥቂት ሺህ ብሮች ይኑርህ እንጂ ከ”ህግ አካላትና አባላት” ጋር ተደራድረህ ፋይልህ እንዲጠፋ ይደረግና ነፃ ትለቀቃለህ – እንኳንስ ተራ ወንጀል ሠርተህ በትልቁም አትነካም ማለቴ ነው፡፡ የሚታሰረው ድሃ፣ የሚቀጣው ድሃ፣ የሚፈናቀለው ድሃ፣ የሀብታሞቹን ሞት የሚሞተው ሳይቀር ድሃ ነው፡፡

ምን ይብቃን? በትምህርት ዜሮ፣ በሃይማኖት ዜሮ፣ በሞራል ዜሮ፣ በሥራ ዜሮ፣ በምግባር ዜሮ፣ በህግ የበላይነት ዜሮ፣ በኅሊና ፍርድ ዜሮ፣ በሁሉም ዜሮ ….. ሆነናል፡፡ ማን ነው ይህችን ሀገር የሚታደጋት? የወጣቱን መንፈስ አሽመድምደውታል፤ አብዛኛው የማይበርደው የማይሞቀው ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ በልዩ ልዩ ተደራቢ ዐመልና በሱሶች ተጠምዶ እንኳንስ ሀገሩን ራሱንም የረሳው ዜጋ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ትልቁም ትንሹም ከሥራ ሲወጣ ሮጦ የሚገኘው መጠጥ ቤት ነው፤ ራሱን በብርጭቆ ውስጥ ወሸቆ የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር ቀላል እንዳይመስልህ፡፡ የዘራፊውም የተዘራፊውም የማታ መገናኛ ጣቢያ መጠጥ ቤቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ጭንቀታቸውን ለጊዜው የሚረሱት በዚያ ጊዜያዊ የነፃነት መድረክ ነው – በዛሬው ዘመን ለመዝናናት ከሚጠጣው ሰው ይልቅ ከጭንቀት ለመደበቅ የሚጠጣው ሰው ይበዛል፡፡ በየመሸታ ቤቱ ሲያውካካ የምታየው ሰው ሁሉ ተደስቶ እንዳይመስልህ፡፡ ይሄኔ ልጁ ባራባሶም አይኖረው ይሆናል፡፡ ይሄኔ የልጁ ሱሪ ተቀዶ ከመቀመጫው በኩል የመነጽር ቅርጽ አውጥቶ ይሆናል፡፡ ይሄኔ እቤቱ የሚላስና የሚቀመስ የሌለው ይሆናል፡፡ … ዘመናዊ ሕዝብን የማስተዳደር ጥበብ ማለት እንግዲህ እንዲህ እንደወያኔ ሀገርንና ሕዝብን በድህነት አረንቋ ከትቶ መሆን አለበት፡፡ ወያኔዎች ደስ ይበላችሁ! ኢትዮጵያን እንድታጠፉ ከጥልቁ የእሳት ባህር በእልልታና በሆታ የሸኛችሁ የአጋንንት ሠራዊት በጣም ተደስቷልና እባካችሁን ወያኔዎች በደስታ ዝለሉ፡፡ የባህርይ አባታችሁን ዲያብሎስንም አመስግኑ፡፡

ከየትኛው ሰማይ የሚላክ ዜጋ ይሆን ነፃነታችንን የሚያላብሰን? አንዳንችን ሌላኛችንን ነፃ እንድናወጣ ከተጠበቀስ መቼ ነው ነፃ የምንወጣው? የኔንስ ተውት የልጆቼና የልጅ ልጆቼ ዕጣ ምን ይሆን? ላብድ ነው፤ ጨነቀኝ – ባብድ ይሻል ይሆን? እስኪ የሞከራችሁት ካላችሁ ንገሩኝ – በተረቱም እኮ “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ (የልብ አይገኝም)” ነው የሚባል፡፡ ብቻ አንዳች አዋጭ መፍትሔ ያላችሁ ጠቁሙኝ፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት በእስካሁኑ ሁኔታ የበሬ ቆለጥ ሆና የቀረች ትመስላለች- ቀበሮዋ ትወድቅልኛለች ብላ ስትከተል ውላ ምራቋን የጨረሰችባት አጓጊ ቆለጥ፡፡ የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ሥልትም ሥራውን በሚገባ እየሠራ ነው – ጥቂት የማይባሉ የደቡብ አፍሪካውን ዓይነት የአፓርታይድ ቅኝት ዳንኪረኞች ፈጥሮልን ለተጨማሪ ዓመታት ወደ አረንቋ ሊከቱን እየተሟሟቁ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ያስጨንቃል – ካለፈውና ካለው ይልቅ የወደፊቱም በእጅጉ ይዘገንናል፡፡ ምን ይዋጠን? ራሳችሁን ጠይቁና እናንተም እንደኔው ጥቂት ተጨነቁ፡፡ ለመጨነቅ ደግሞ ለሀብትና ለዝና ወይም ለትምህርት ደረጃና ለዕድሜያችሁ ወይም ለዘራችሁና ለሃይማታችሁ ብዙም ሥፍራ  አትስጡ፡፡    እንደሰው እናስብ፤ ቢቻለን ደግሞ እንደአንዲት ሀገር አባላት እናስብ፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s