ምክር ቢጤ ብአዴን ውስጥ ላላችሁ የአማራ ተቆርቋሪዎች | ከይገርማል

Ethiopia

እንደሚታወቀው ብአዴን ከኢሕአፓ ተነጥለው ለወያኔ ባደሩ ሰዎች በወያኔ እገዛና ክትትል ከተመሰረተው ኢሕዴን የወጣ ድርጅት ነው:: ኢህዴን ህብረብሄር የነበረ ድርጅት ስለነበር እንዲህ ያለ ድርጅት በወያኔ የፖለቲካ እምነት ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም:: በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ብቸኛ አማራጭ ነው ብሎ የሚያምነው ወያኔ የህብረብሄራዊ አደረጃጀትን የሚታገስበት አቅም አልነበረውም:: በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለውን ታጋይ አሰባስቦ ከወያኔ ጎን ተሰልፎ ደርግን እንዲወጋ ተልእኮ ተሰጥቶት የነበረው ኢሕዴን ቀዳሚ ተልእኮውን ስላጠናቀቀ ደርግ ከተወገደ በኋላ ንቅናቄው እንዲፈርስና የንቅናቄው ታጋዮች ወደየጎሳ ጉረኗቸው ተሰባስበው ለሁለተኛው ዙር ተልእኮ እንዲሰለፉ አደረገ:: ይህ ሁለተኛው ዙር የጎሳ ድርጅቶች ተልእኮ ዜጎች በየጎሳ ድርጅቶቻቸው ዙሪያ ታቅፈው ጎሳዊ አመለካከታቸውን በማዳበር ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ማደብዘዝና የወያኔን አላማ ማስፈጸም ነበር:: በዚህ መሰረት አማራ የሆኑት የቀድሞው ኢህዴን ታጋዮች ተሰባስበው ብአዴን የሚባል የአማራ ድርጅት እንዲመሰርቱና በዚያ ድርጅት ውስጥ እንዲካተቱ አደረገ::

ነፍጠኛ ተብሎ የተፈረጀው አማራ ከብሄሩ በላይ ኢትዮጵያን የሚወድ: ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ደሙን ለማፍሰስና አጥንቱን ለመከስከስ ወደኋላ የማይል እንደሆነ ስለሚታወቅ ብአዴንን ካለተቆጣጣሪ ብቻውን መልቀቅ ለወያኔ አላማ እንቅፋት እንደመፍጠር ተደርጎ ስለታመነ ይመስላል ድርጅቱን እንዲመሩ በቁልፍ አመራር ሰጭነት ቦታ ላይ የተቀመጡት በሙሉ ወይም በከፊል የሌላ ብሄር (ማለት የሌላ ክልል) አባል የሆኑ ሰዎች እንዲሆኑ ተደረገ:: እኒህ በድርጅቱ የአመራር ቦታ ላይ የተቀመጡት ሰዎች የህዝባቸውን ጉዳይ ትተው ወያኔ አድርጉ ያላቸውን ብቻ ተግተው በማስፈጸም አማሮች ካለአይዟችሁ ባይ ክልላቸውን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የግፍ ሰለባ እንዲሆኑ አደረጉ::

አማራን መግደል ዶሮን የማረድ ያህል ቀላል ሆነ:: እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ ካለታሪክ ማስረጃና ካለፍላጎቱ ወደሌላ ክልል ሲካለል: ተወልዶ ካደገበት ቀየ ያላግባብ ሲፈናቀል: ንብረቱ ሲወረስ: ሲንገላታና ሲገደል ሳት ብሎት “በአማራ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ይብቃ!” ብሎ ድምጹን ያላሰማ ድርጅት እንዴት የአማራው ወኪል ሊሆን ይችላል!

ከወያኔ አላማወች ውስጥ አንዱ አሁን የአማራ ክልል ተብሎ ከሚታወቀው ክልል ውጪ ያሉትን ክልሎች አማራ አልባ ማድረግና በክልሉ የሚኖረውን አማራ ደግሞ ቅስሙ የተሰበረ ፍጹም ተገዥ ማድረግ ነው::

የብአዴን ባለስልጣናት ይህን የወያኔን አላማ በማሳካት በኩል ዋነኛውን ድርሻ ተወጥተዋል ማለት ይቻላል:: በአቶ በረከት ስምዖን: በአቶ ታምራት ላይኔ: በአቶ አዲሱ ለገሰ: በአቶ ተፈራ ዋልዋና በሌሎችም ሲተላለፉ የነበሩት መልእክቶች መላው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢው በሚኖረው አማራ ላይ እጁን እንዲያነሳ የሚቀሰቅሱ ነበሩ:: በሌላ በኩል በአማራው ህዝብ ላይ ተፈጸመ ተብሎ ለሚቀርበው ክስ እኒህ የብአዴን አመራሮች በሜዲያ በመቅረብ አማራ ተኮር የሆነ በደል እንዳልተፈጸመ ማስተባበያወች ሲሰጡና በአንዳንድ አካባቢወች የተፈናቀሉትም ቢሆኑ ”ዘራፊወችና ሌቦች ናቸው” በማለት ሽፋን ሲሰጡ ነበር:: በአማሮች ላይ የተፈጸመው ግፍ ምን ያህል ይሆን!

አሁን አሁን እንደምሰማው ከሆነ እኒያ በብአዴን አመራር ሰጭነት ተሰይመው በአማራው ላይ ሲደርስ የነበረውን ግፍ ሲያቀናብሩና ሲያስፈጽሙ የነበሩት ወንጀለኞች ከብአዴን ተገፍተው ወጥተው አመራሩ በእውነተኛ የአማራ ልጆች ተተክቷል የሚል ነገር አለ:: እየተባለ ያለው እውነት ከሆነ እንዴት ደስ ይላል!

እናንተ ብአዴን ውስጥ ያላችሁ እውነተኛ የአማራ ልጆች: ከ24 አመታ በላይ በአማራ ላይ የተፈጸመው ሰቆቃ ያበቃ ዘንድ ደም መክፈል ካለባችሁ ደም ክፈሉ:: ወያኔወች 7 ሆነው ወጥተው ለአላማቸው በጽናት መታገል በመቻላቸው ለዚህ በቅተዋል:: እናንተ እንደወያኔ የተበላሸ አላማና ግብ ይዛችሁ አይደለም የምትነሱት:: አማራን ከጥፋት መታደግና በኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት: ዴሞክራሲና ፍትህ እንዲሰፍን ብላችሁ የምታደርጉት ትግል ቅዱስ ትግል ነው::

በሀይል ወረራ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ህዝቧን ቅኝ ተገዥ ባሪያ ለማድረግ የመጣውን ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ጠራርጎ ለማስወጣት የተደረገው ጦርነት ቅዱስ ጦርነት እንደነበረው ሁሉ የአንድ ሀገር ልጆችን በዘርና በሀይማኖት ከፋፍሎ መከራ እያወረደ ካለው ወያኔ ጋር የሚደረገው ጦርነትም ቅዱስ ጦርነት ነው:: ወደዚህ ጦርነት ለመግባት ምንም ሊያስፈራችሁ አይገባም:: አማራው ዝም ብሎ በመቀመጡ የቀረለት መከራ ስለሌለ:: ዛሬም ቢሆን አማሮች አማራ በመሆናቸው ብቻ በመላው ኢትዮጵያ መከራ እያዩ ነው::

ወያኔ የወልቃይትን የአማራ መሬት በሀይል ወደትግራይ ካካለለ በኋላ ባለመሬቶችን እያፈናቀለ የራሴ የሚለውን ህዝብ እንዳሰፈረበት ማንም ያውቃል:: “ኧረ እኛ አማራ ነን! ከወገኖቻችን ተለይተን በመሬታችን ላይ ሌሎች እንዲሰፍሩ ተደርጎ እኛ ለባርነት እንድንዳረግ ለምን ይሆናል::” ብለው ወልቃይቴወች ከመጮሀቸው በፊት “ወልቃይት የአማራ መሬት ነው: ወልቃይቶችም አማሮች” ብሎ ሊከራከር ይገባ የነበረው ብአዴን ነበር::

አሁንም ቢሆን ያንን ማድረግ ይቻላል:: የአማሮች መብት የሚረገጥበትን ስርአት ማገልገል ብሎም ከጠላቶቹ ጋር ተባብሮ የራሱን ቤተሰብ ማሰቃየት ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን ህሊናንም የሚቧጥጥ የእብድ ተግባር ነው::

በአማራ ባህል ሰው የሚኖረው ለራሱ ብቻ አይደለም:: በተለይ ወንድ ልጅ ደም መላሽ: ለሀገርና ለወገን መከታ ነው ተብሎ ይታመን ስለነበር ወንድ ልጅ ሲወለድ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጎረቤትም ደስ ይለው ነበር:: ዛሬ ላይ ከጠላት ጋር አብሮ የራሱን ቤተሰብ እንዳይፈራገጥ እጅና እግሩን ጠፍሮ ይዞ የሚያሰቃየው ከዚያው ከህብረተሰቡ አብራክ የወጣው ልጅ መሆኑ “ምን አይነት ጊዜ ላይ ደርስን!” ያሰኛል:: የወገኑ ጥቃት ሳይቆጨው ይባስ ብሎ ደግሞ ደም ከጠማቸው ወፈፌወች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የራሱን ሰው የሚያሰቃይ ሰው ምን አይነት ሰው ሊባል ይቻላል! አማራ የሚታወቀው በዚህ መልኩ አልነበርም::

በብአዴን ውስጥ ጊዜ ቦታውን ያስጨበጣችሁ አማሮች ለወገናችሁ በመቆም ይህን አጋጣሚ ልትጠቀሙበት ይገባል:: ወያኔ ሰላም ካልወደደ ምንም ማድረግ አይቻልም:: የፈለገው ቢደረግ በአንድ ወገን ትእግስት ብቻ ሰላም ሊሰፍን አይችልም:: ስለዚህ ቁረጡና ከህዝባችሁ ጎን ቁሙ:: እመኑኝ መላው አማራ ከጎናችሁ ይሰለፋል:: ይህን ስታደርጉ ብቻ ነው ህዝባችሁን ከጥፋት ልትታደጉ ራሳችሁንም ከህሊና ጸጸት ነጻ ልታወጡ የምትችሉት:: ትግላችሁን ስኬታማ ለማድረግ

በክልሉ በፌደራል ደህንነት ስም የሚንቀሳቀሱትን የወያኔ የደህንነትና የአፈና ቡድኖች መለየትና በስልት ማራቅ
በድርጅታችሁ ውስጥ ያሉትን ለወገን ደንታ የሌላቸውን አጋሰሶች: አስመሳዮች: አወናባጆች: ልፍስፍሶች: ነገር አመላላሽና እምነት የማይጣልባቸውን ሰዎች በስልት ማግለልና ድርጅታችሁን ማጽዳት
በሰራዊቱ: በደህንነት: በፌደራል ፖሊስና በሌሎች ወሳኝ የመንግስት መስሪያቤቶች ውስጥ ያሉትን አማሮች በተጠና መንገድ የትግሉ አጋር ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት
በየደረጃው ባሉት የሀላፊነት ቦታወች ላይ በሀላፊነት ሊቀመጡና አመራር ሊሰጡ የሚችሉትን ሰዎች በጥንቃቄ መምረጥ
በየገጠሩ ቀበሌ የሚኖሩት ወጣቶች የመሳሪያ አጠቃቀም የውትድርና ት/ ት እንዲያገኙ ማድረግ
በደርግ ጊዜ የነበሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች: ከወያኔ ጦር የተቀነሱትንና በተለያየ ምክንያት ከፖሊስና ከመከላከያ የተገለሉትን የሰራዊት አባላት አማራን በመታደግ አላማ ዙሪያ ማሰባሰብና ማስታጠቅ
ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖረው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ብአዴን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማገዝ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብትና እኩልነት የሚረጋገጥባት ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ደግፎ እንዲቆም ጥረት ማድረግ
የአማሮች እንቅስቃሴ ለሌሎች ክልሎች ስጋት እንዳይመስል የዲፕሎማሲ ስራ መስራት
ሕብረ ብሔር አደረጃጀት ያላቸው የተቃዋሚ ሀይሎች ወያኔንና ስርአቱን ለማስወገድ ለሚደረገው ግብግብ ጠንካራ አጋሮች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል:: ለእኒህ ሀይሎች በአማራ ላይ የደረሰውን በደልና የወያኔን እኩይ ስራ ለመተረክ ጊዜ መውሰድ አያስፈልግም: ከማንም በፊት የተገነዘቡና ጩኸታቸውን ያሰሙ እነሱ ስለሆኑ:: አካባቢን ወይም ጎሳን እንወክላለን የሚሉት ድርጅቶች ጋርም መነጋገርና መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው
የትግራይ ህዝብ በአማራ ላይ የደረሰውን በደል እንዲረዳ: የወያኔን እኩይ ተግባር ገልጦ እንዲያይ: የተዋደደብንን ልጓም በማውለቅ: የተጫነብንን ጭቆና በማስወገድ: የአንድ ሀገር ልጆችን ከፋፍሎ ሆድና ጀርባ ያደረገንን ጠላት ወደታሪክነት ለመቀየር ለሚደረገው ትግል የድርሻውን እንዲያበረክት የዲፕሎማሲ ስራ መስራት:: “እኛ ካልኖርን አማራ ያጠፋሀል” የሚለውን የወያኔ ቅስቀሳ የትግራይ ሕዝብ አምኖ እንዳይቀበል በተቻለውና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማስገንዘብ
ከኤርትራ ጋር ለ30 አመታት የተደረገው ጦርነት ከእንግዲህ በኋላ የሚደገም አይሆንም:: ኤርትራውያን የታገሉለትንና የሞቱለትን ሀገር ማንም በሀይል ሊያሳጣቸው አይገባም:: ለነጻነት ታግለዋል በትግላቸው ነጻነታቸውን ተጎናጽፈዋል:: ኤርትራ እንደሀገር ስትታወቅ በመሬት ላይ የሰፈረ የድንበር መስመር ስላልነበረ ለሁለቱ ሀገሮች የድንበር ግጭት መነሻ መሆኑ ይታወቃል:: ከወያኔ ውድቀት በኋላ እንዲህ ያለ ነገር ሊከሰት አይገባም:: የወደብም ይሁን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በውይይትና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ካልሆነም በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ወይም በግልግል ፍርድ ቤት የሚፈታ እንጅ ጦር የሚያማዝዝ እንደማይሆን ማስረዳትና ጥርጣሬን አስወግዶ መተማመንን መገንባት ያስፈልጋል::
መንግስታትና አለማቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣት እንዳለበት አምነው እንዲቀበሉና እንዲደግፉ የትግሉን አላማና ግብ ማስረዳት ያስፈልጋል::

የሰው ልጅ በሀገሩ ተከብሮና በፈለገው አካባቢ ተዘዋውሮ በሰላምና በፍቅር መኖር እንዲችል የሰላም: የፍቅር: የአንድነት: የእኩልነት: የፍትህና የዴሞክራሲ አረሞች መነቀል ይኖርባቸዋል:: ብአዴኖች ልብ በሉ! የምትኖሩት ለራሳችሁ ብቻ መሆን የለበትም:: ወገኖቻችሁ በየስርቻው የጣዕር ድምጽ እያሰሙ እናንተ ደስታና ሰላም ልታገኙ አትችሉም:: ምክሬን ብትቀበሉ አማራውንና ሁሉንም ሀገር ወዳድ ሀይል ከጎናችሁ አሰልፋችሁ በታሪክ የመጨረሻውን የግፍ ስርአት አብረን እንሻገራለን:: 7 ሆነው ወጥተው ሀገር ሀገር የሚለውን ወገን እየገደሉ ለድል የበቁት ወያኔወች በድፍረት ስለገቡበት: በጽናትም ስለያዙት እንጅ አላማቸው ሕዝባዊ ስለነበረ አልነበረም:: እናንተ ለምታደርጉት ትግል በአንድ ቀን ጀምበር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከጎናችሁ ልታሰልፉ ትችላላችሁ::

 

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s