የ ህወሀት ኢህአዴግ ፖሊሲ ወጣቱን ወዴት እየወሰደው ነው ? – ኤድመን ተስፋዬ

Woyane

ከአፍሪካ አጠቃላይ ህዝብ ከ60 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ከ ሰላሳ አምስት አመት በታች በሆነ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ እንደ መሆኑ አንባገነናዊ ስርአትን ከአፍሪካ  ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረግ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ይህን የተናገሩት የዘር ሀረጋቸው ከጎረቤት ኬኒያ የሚመዘዘው የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንት ኦባማ  ከላይ የጠቀስኩትን ቁጭት አዘል የሆነ ንግግራቸውን ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስታቸው በነደፈው ፖሊሲ መነሻነት  እ.ኤ.አ በ2012 ከመላው አፍሪካ ለተውጣጡ ስልሳ ለሚሆኑ ወጣቶች ከአመራር ጋር የተገኛኘ ስልጠና  በአሜሪካ እንዲከታተሉ አድርገዋል፣እያደረጉም ነው፡፡ እንደ አሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ የመረጃ ቋት ከሀገራችን አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ 64.3 ፐርሰንት የሚሆነው ከዜሮ አመት እስከ ሀያ አራት አመት በሆነ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የእድሜ ክልሉን ከ 0 እስከ ሰላሳ አምስት ክልል ውስጥ ከፍ ስናደርገው ደግሞ አሃዙ ወደ 74 ፐርሰንት ይደርሳል፡፡ ይህም የሚያሳየን  ሀገራችን በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች በብዛት የሚኖሩባት ሀገር እንደሆነች ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ከአጠቃላይ የሀገራችን ህዝብ አብዛኛው በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ሀገራችንን በየአምስት አመቱ በሚታደስ የምርጫ ውል እያስተዳደረ ያለውን ኢህአዴግን ፖሊሲዎቹን መነሻ በማድረግ   የወጣቱን ተጠቃሚነት እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ የሀገሪቷ ሀብት ክፍፍል ላይ ተገቢውን ድርሻ ስለማግኘቱ ወጣቱ ትውልድ በኢኮኖሚ ስርአቱ ላይ ያለውን ተሳታፊነት መነሻ በማድረግ ማየት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ገዢው ፖርቲ ኢህአዴግ ወጣቶችን ማእከል ባደረገ መልኩ ያደረገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በዋኛነት የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋፋቱ እና የስራ እድል መፈጠሩ ላይ ትኩረት ባደረገ ምልኩ የሚገልፅ ሲሆን፣ በዋነኛነትም አስፋፋዉት የሚለው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እንዳለ ሆኖ የዩኒቨርስቲዎችን ማስፋፋቱን፣የሞያ እና ቴክኒክ ት/ም ቤቶችን ማስፋፋቱን እና በጥቃቅን እና አነስተኛ ወጣቶችን በማደረጀት ወጣቱን  የንብረት ባለቤት ማድረጉን ለማሳያነት ያቀርባል፡፡ እንደ እኔ እምነት ትልቁ ጥያቄ ገዢው ፖርቲ የሚለፍፈለትን  ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ያደረገውን ፖሊሲው  ነባራዊ የሆነ የሚታይ ለውጥ በብዙሀኑ ወጣት ላይ አምጥቷል ወይ የሚለው ሲሆን፣ ይህንንም  ለመፈተሸ ኢህአዴግ አስፋፋውት የሚለውን ዩኒቨርስቲዎችን፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ፖሊሲውን ወጤት እና ምንን መሰረት አድርጎ እንደተዋቀረ ግልፅ ያልሆነውን የፌደራሊዝም ስርአትን  ማእከል በማድረግ ማየት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ወጣቱን ተምሮ ስራ ፈት ያደረገው ኢህአዴግአዊ ፖሊሲ ለስራ ፈጣሪነትስ ምቹ ነው?    

ገዢው ፖርቲ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለብዙሀኑ ወጣቶች ተደራሽ እንዲሆን አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎችን በመክፈትም ሆነ ነባሮቹን በማስፋፋት  አስፋፋውት የሚለውን የዩኒቨርስቲ ትምህርት በነባራዊነት በትውልድ ተጋሪዬ ወጣት ላይ ያመጣውን ለውጥ ለማየት የስራ እድልን፣  የወጣትነት ባህሪን እና የማሰብ ነፃነትን ማእከል በማድረግ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ወጣትነት የእድሜ ክልል ራስን ከመቻል፣ቤተሰብን ከመርዳት ጋር ተገናኝ የሆኑ ፍላጎቶች የሚንሩበት እንደመሆኑ የከፍተኛ ተቋም ትምህርትን ለወጣቶች ተደራሽከማድረግ እኩል ታሳቢ መሆን ያለበት የስራ እድል የመሆኑን ሁነት እንደ ማርክ ዴን ያሉ የባህሪያዊ ኢኮኖሚደስቶች (Behavioural Economist) ይገልፃሉ፡፡ ሊዊንስተን በበኩሉ ከስራ እድል እና ራስን ከመቻል እና ቤተሰብን ከመርዳት ጋር የተገናኙ ፍላጎቶቹን ለማሳካት በገበያው ላይ ስራ ፈላጊ የሆነ ወጣት  ስራ ከማጣት ጋር በተያያዘ ለአይምሮ መታወክ እና ለድብርት ተጋላጭ የሚሆንበት እድል ከፍተኛ ስለመሆኑ ይተነትናል፡፡

እንደ ወጣት በዩኒቨርስቲ በሚኖረው ቀይታው በመጀመሪያ በነፃነት የሚማርበትን ስርአት መዘርጋት እና  ማመቻቸት የመንግስት ግዴታ ሲሆን ሲቀጥል ደግሞ በተማረው ሞያ ተቀጥሮ እንዲሰራ የስራ እድል ፈጣሪ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በግብርናው፣በኢንደስትሪው እና በአገልግሎት ዘርፉ ከግል ባለሀብቱ ጋር በመተባበር መከወን ሌላው ግዴታው ነው፡፡ በእኔ እምነት ዋናው ቁምነገር ዩኒቨርስቲዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ለሚወጣው የስራ እድል መፍጠር እና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ስርአት ማመቻቸት እንደመሆኑ ኢህአዴግ አስፋፋዋቸው እና አዲስ ከፈትኩአቸው ከሚለው ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው የሚወጡ የትውልድ ተጋሪዬ ወጣቶች በተማሩት ሞያ እንኳን የሀገራቸውን ችግር ሊፈቱ የራሳቸውን ችግር ሊፈቱ እንዳይችሉ ኢህአዴግአዊ ፖሊሲዎች ጋሬጣ ስለመሆናቸው መሞገት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

 

ከየትኛውም የእድሜ ክልል በተለየ ወጣትነት ነፃነትን የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጣት ትውልድ እምቅ ችሎታውን ተጠቅሞ የሀገሩንም ሆነ የራሱን የኑሮ ችግር ለመፍታት የሞያ ነፃነት ይፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ አመጣውት የሚለውን የኢኮኖሚ እድገት ነባራዊነቱን፣ የዲሞራሲያዊ ስርአት በሀገራችን ለመተግበር ኢህአዴግ እስኬት ድረስ ይሄዳል፣ መንግስታዊ ሌብነት እና ሀገራዊ መመዙ ወዘተ  የሚሉ ጉዳዮችን ወጣቱ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ሀገራዊ በሆነ ጥናት ከመፈተሸ ጋር በተያያዘ ለሚኖር ፍላጎቱ ኢህአዴግ እንደ መንግስት  ድጋፍ  ያደርጋል ወይ የሚለውን መነሻ አድርገን ስናይ አንድ ለ አምስት  የሚለው የፖርቲው የጥርነፋ ስርአት በዩኒቨርስቲዎች ስርመስደዱ እና ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ስራ ለማግኘት ከዲግሪ ይልቅ የፖርቲ አባልነት መታወቂያ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ በራሱ ከላይ የጠቀስኩትን ለመከወን መንግስታዊ እንቅፋት ስለመኖሩ አሳይ ከመሆኑም በላይ   የትውልድ ተጋሪዬ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በዩኒቨርስቲ ቆይታው በነፃነት  የሀገሩን ችግር ከሞያው አኩአያ ለማየት ኢህአዴግአዊ የፖለቲካ ተግዳሮቶች እንቅፋት ስለመሆኑ አሳይ ይመስለኛል፡፡

በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ የወጣ ወጣት ዲንጋይ ጠራቢ እና አስጠራቢ በሆነበት፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቃ የወጣች ወጣት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አልጋ አንጣፊ በሆነችበት ሁናቴ እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ  ብርን ማእከል በማድረግ ማህበረሰባዊ እና ሀገራዊ ዋጋ በማያውቅ ነፈዝ ብራም የወሲብ ማስተንፈሻነት ገላዋን እስከ መስጠት የሚደርስ ተስፋ አስቆራጭ ሁነት ውስጥ እንድትገባ መንስኤው ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከመውጣት በሁአላ በሰራተኛ ገበያው ያለው ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ መሆኑን በመጥቀስ ኢህአዴግ አስፋፋውት የሚለው ዩኒቨርስቲ   ለወጣቱ ያተረፈው ድብርትን እና ለአይምሮ መታወክ ተጋላጭነትን ስለመሆኑ  አሳይ ይመስለኛል፡፡

ገዢው ፖርቲ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን በተመለከተ በሚመስል መልኩ ብዙን ጊዜ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ የሚወጡ ወጣቶች ከመንግስት ስራ ከሚፈልጉ ስራ ፈጣሪ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ በእኔ እምነት ገዢው ፖርቲ ስለ ስራ ፈጠራ ሲያወራ የዘነጋው ነገር ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንዲሆን  ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነፃነት  መሆኑን ነው፡፡ ከዩኒቨርስቲ ተምሮ ባገኘው እውቀት ሀገሩን ለመርዳት በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ለመስራት በውስጠ ታዋቂነት ከትምህርቱ ይልቅ የኢህአዴግ አባልነት መታወቂያ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠለት ወጣት ስራ ፈጣሪ ሆኖ በኢኮኖሚ ስርአቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን  እዛም ቤት እሳት አለ እንዲሉ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን ማእከል ያደረገው ኢህአዴግ የሚመራው የሀገራችን የኢኮኖሚ ስርአት ላይ ወጣቱን ትውልድ ውድ የሆነውን ነፃነቱን ካልገበረ በቀር በመንግስታዊ ድጋፍ (ብድር፣የስራ ቦታ ማመቻቸት ወዘተ) መነሻነት ተሳታፊ የመሆኑን ነገር አስቸጋሪ ማድረጉ በእኔ እምነት የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ አመላካች ከመሆኑም በላይ ወጣቱ እንደ ትውልድ በተጋረጠበት መንግስታዊ ዳራ የተነሳ ዳራውን የጋረጠበት መንግስት ላይ እንዲዞር መንስኤ የሚሆን ይመስለኛል፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s