ዕርቅ፣ ብሔራዊ መግባባት ከማን ጋራ? (ይኄይስ እውነቱ)

ይኄይስ እውነቱ

ዕርቅ፣ ብሔራዊ መግባባት ከማን ጋራ? ይኄይስ እውነቱ ይህን ርእሰ ጉዳይ በግል አስተያየት መልክ ያነሳሁበት ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ያለውን ትርጉምና ተፈጻሚነት በሚመለከት በእግረ መንገድ ከማንሳት ባለፈ ምሁራን የበኩላቸውን በሳል ጽሑፍ እንዲያቀርቡበትና በራሱ ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ ስለታየኝ ነው፡፡

ዕርቅን ማውረድ፣ ይቅር ለእግዚአብሔር መባባል፣ ለታላቅና ዘላቂነት ላለው ዓላማ (ለአገር ኅልውና፣ አንድነት፣ ለሕዝብ ሰላምና ብልጽግና) ሲባል መግባባት የተቀደሱ አሳቦች ናቸው፡፡ የዕርቅም ሆነ የመግባባት ፍለጋ የተጣሉ፣ በአሳብ የተለያዩ ወገኖች መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ ዕርቅም ሆነ መግባባት ስለተፈለገ ወይም ስለተመኘነው ብቻ ተግባራዊ አይሆንም፡፡ ከሁሉም በላይ የተጣሉትን/የተለያዩትን ወገኖች ቅንነት፣ በጎ ፈቃድ/ስምምነት እና ዝግጁነት፣ በመጠኑም ቢሆን የዕርቅ ፈላጊዎቹን መንፈሳዊ ልዕልና/የሞራል ከፍታ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ዕርቅ ፈላጊዎቹ በተወሰነ ደረጃ የጋራችን የሚሉት ጉዳይ መኖር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በአንፃሩም በአስታራቂነት/በሸምጋይነት የሚሰየሙት ወገኖች ለዕርቅ ፈላጊዎቹ የዘረዘርናቸው ቅድመ ሁኔታዎች አስፈላጊነት እንደተጠበቁ ሆነው በተጨማሪ አርቆ አሳቢነት/አስተዋይነት፤ ከወገንተኝነት የነፃ ኅሊና፤ የዕርቅ ፈላጊዎቹን ማንነት፣ የልዩነት/አለመግባባት ምንጭ፣ የጋራ ጥቅም/ፍላጎት ጠንቅቆ ማወቅ እና እንደ አስፈላጊነቱ ለዚሁ ዓላማ አገር በቀል ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዕርቅ ፈላጊ ወገኖች ወይም አንዳቸው የተደበቀ አጀንዳ ይዘው ወይም ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ሳላላመቻቸው ጊዜ ለመበደር ብቻ ወይም ተገደው ወይም ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ፍጆታ ወይም ለለበጣ (ሊፕ ሰርቪስ) የሚያደርጉት ከሆነ ለዕርቅም ሆነ ለመግባባት ቦታ/ዕድል ያላቸው አይመስለኝም፡፡

የዕርቅ ወይም የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ወያኔ የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በኃይል ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከልብም ሆነ ከለበጣ ሲነሳ ሲሰበክ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ወያኔ በሕዝብ ላይ የፈጸመውን በደልና አገራዊ ጥፋት ተከትሎ የይስሙላ ዕርቆች በአስመሳይ ‹‹ሽማግሌዎች/የሃይማኖት አባቶች›› ተሞክረዋል፡፡ የወያኔ አለቃ ኑዛዜ አስፈጻሚ በሆነው አሻንጉሊት ጠ/ሚኒስትር በቅርብ ጊዜ የተደረገውን ጨምሮ ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ የ‹‹ብሔራዊ መግባባት›› ጉባኤዎችም ተደርገዋል፡፡ ሁሉም ለታይታ የተደረጉ በመሆናቸው ጭንጋፍ ሆነው ቀርተዋል፡፡

ስለ ዕርቅ ወይም ብሔራዊ መግባባት ስንነጋገር ሁለት ቢያንስ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡ 1ኛ/ ዕርቁ ወይም ብሔራዊ መግባባቱ ከማን ጋራ ነው? 2ኛ/ ዕርቁ ወይም ብሔራዊ መግባባቱ የወያኔ አገዛዝ ከተላላኪ አሽከሮቹ ጋር (በግልም ሆነ በቡድን) ለፈጸማቸውና እየፈጸመ ካለው የአገር ክዳት፣ የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊ ፍጥረት ላይ የተፈጸሙ፣ ልዩ ልዩ 2 የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ወ.ዘ.ተ. ተጠያቂነት/ኃላፊነት የሚያስቀር ነው ወይ?

ዕርቅ ከማን ጋራ? ላለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራ ካለው የወያኔ አገዛዝ ጋራ? ሕዝብን በጎሣ አጥር ከልሎ በዘር በሃይማኖት እየፈጀና እያፋጀ ካለው፣ በደም ከተጨማለቀው የጥቂት ዘረኞች ሥርዓትና ተላላኪ አሽከሮቹ ጋራ? የኢትዮጵያን ሕዝብ መግቢያ መወጫ አሳጥተው ለመከራና እንግልት ከዳረገው ‹መንግሥታዊ አሸባሪ› ኃይል ወይም ለዚህ ኃይል ካደሩ አረመኔ ‹ቅጥረኞች› ጋራ? የአገሪቱን ሀብትና ንብረት ሙልጭ አድርጎ ዘርፎ ሕዝባችንን የድህነት ማጥ ውስጥ ከከተተው፣ ለማያቋርጥ ረሃብና ችጋር ባጠቃላይ ለባርነት ከዳረገው የግፈኞች ቡድን ጋራ?

ወይስ እነዚህ ወሮበሎች በረጩት አፍራሽ የጎሣ መርዝና ጥቂት ደናቁርት በሆኑ ‹‹የተቃዋሚ ቡድኖች›› መርዛማ ስብከት (አሳፋሪ የሐሰት ሐውልት ለማቆም እስካበቃው) ሰለባ በመሆን ደም በተቃቡ ኢትዮጵያውያን ወገኖች መካከል? ወይስ በጥርጣሬ/ባለመተማመን በጎሪጥ በሚተያዩ የተቃዋሚ ቡድኖች መካከል?

መቼም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ከሌለው ወያኔ ጋር አይመስለኝም? ይህ ከኵርንችት በለስ መጠበቅ ይሆናል፡፡ ወያኔ በአራት ማዕዘን ተወጥሮ መጣፊያ ሲያጥረው ጊዜ መግዣ ለመስጠትና ሰቆቃችንን ለማራዘም ካልሆነ በቀር፡፡ የወያኔ አለቃ ዕርቅ/ብሔራዊ መግባባት የሚባል ነገር ተቀባይነት እንደሌለው ደጋግሞ ሲደነፋ ምስክር ሆነናል፡፡ ኑዛዜ አስፈጻሚዎቹ ደግሞ ከዚህ የተለየ አሳብ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሲደናበሩና ሲበረግጉ ለቀጣይ ጥፋት ትንፋሽ ማግኛ የቆጥ የባጡን ሲዘላብዱ ሰምተናቸው ይሆናል፡፡ ወይም ልንሰማቸው እንችል ይሆናል፡፡ የሰሞኑ እየገደሉ ‹ይቅርታ› ለባዕዳን ‹አሳዳሪዎቻቸው› የሚበረከት እጅ መንሻ ከሚሆን በቀር፣ ውሸት/ቅጥፈት የወያኔ አገዛዝ ዓይነተኛ መገለጫ ከሆነ እነሆ 25 ዓመታት ተቆጥሮአል፡፡ ይህ ዓይነቱ ለቅፅበት ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ማደናገሪያ እንዳያዘናጋን ያስፈልጋል፤ ይልቁንም ባዕዳን ኃይሎች የሕዝባችንን ትግል፣ የደም መሥዋዕትነት ለገዛ አጀንዳቸው መጠቀሚያ ቀዳዳ እንዳያደርጉት ብርቱ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ዕድሜ ልካችንን ታሪካዊ ስህተት ስንፈጽም መኖር የለብንም፡፡

በሌላ በኩል መሠረት ከሌለውና ሆን ተብሎ ከተፈጠረው አንስቶ በትእቢት/በማን አለብኝነት ወይም ባለማወቅ ወይም ከአገዛዝ ሥርዓቶች በመጥፎ ውርስነት የተላለፉ የጎሣ ማንነትን፣ እምነትን፣ ባህልን ወ.ዘ.ተ. መሠረት ያደረጉ ቁርሾዎች፣ ቅሬታዎች፣ ቅያሜዎች፣ መናናቆች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ‹ቁስሎች› በአንድ ጀምበር ላይጠጉ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ዕርቅ በማውረድ ለወደፊቱ የመለያያ/የጥላቻ መሠረቶች እንዳይሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ለሚፈለገው ዕርቅ ከወዲሁም፣ ከወያኔ ውድቀት ማግስትም አጥብቀን ልንናስብበትና የሚመለከተን ሁሉ (የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ካላችሁ፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ሕዝብ እንወክላለን የምትሉ የፖለቲካ ማኅበራት) ውይይት/ምክክር ልናደርግበት ይገባል፡፡

ልዑል አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን እንድንታደግ ኃይሉን፣ ብርታቱንና ማስተዋሉን ያድለን፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s