የወቅታዊ ተግባራዊ ትግል (ወተት) መልዕክት: ጦር ሠራዊት ለለውጥ !!! (በዶ/ር ታደሰ ብሩ)

የወቅታዊ ተግባራዊ ትግል (ወተት) መልዕክት:  ጦር ሠራዊት ለለውጥ !!! (በ ዶ /ር ታደሰ ብሩ የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር)

image

ህወሓት የጦር ሠራዊትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል የሚል ስሜት በብዙዎች ውስጥ አለ ብዬ እገምታለሁ። በዚህም ምክንያት ሠራዊቱም “ዝመት” ሲሉት የሚዘምት፤ “ግደል” ሲሉት የሚገል ግዑዝ አካል እንደሆነ አድርገን እንወስዳለን። በዚህ ድምዳሜ ውስጥ የተወሰነ እውነት ቢኖርም ሙሉ በሙሉ እውነት ላይሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ስላለኝ ይህንን የወተት መልዕክት ላቀርብ ወደድኩ።

እርግጥ ነው የሠራዊቱ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በህወሓት ሰዎች ተይዘዋል። አሁን ያለው የሠራዊት አደረጃጀት ልብ ብሎ ላስተዋለው አስደንጋጭ ነው  –  ከላይ ሙሉ በሙሉ ህወሓት፤ ከታች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኢ-ህወሓት ነው። [“ህወሓት” እና “ኢ-ህወሓት” ምን ማለት እንደሆነ ለመተንተን ጊዜ ማጥፋት ያለብኝ አይመስለኝም።]

ከአዛዦች መካከል ህወሓት ያልሆነ ማግኘት የሚከብደውን ያህል ከእግረኛ ተዋጊዎች መካከል የህወሓት ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ላስተዋለ ሰው ይህ ብዙ አንደምታ ያለው ሀቅ ነው። በተለምዶ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት” እየተባለ የሚጠራው ጦር አዛዥና ታዛዥ፤ አዋጊና ተዋጊ፤ አለቃና ምንዝር እንዲህ ተቃራኒዎች የሆኑበት ስብስብ ነው።

ትንሽ ስሌት እንጨምር። ህወሓት ስለሚመራው ሠራዊት ብዛት የተጋነነ ግምት ያለ ይመስለኛል። ተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን ያለው ሠራዊት የሰው ኃይል በአጠቃላይ (አየር ኃይል፣ አግዓዚንና  በ UN “ሰላም ማስከበር” ላይ ያሉትን ጨምሮ) ከ 140, 000 አይበልጥም፤ ከዚህ ውስጥ 15% ያህሉ በአስተዳደ ሥራ የተያዙ ናቸው። በዚህም ምክንያት በወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ያለው የሰው ብዛት 119,000 አካባቢ ነው። ከዚህ ውስጥ 12,000 ያህሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች የተቀመጡ አዛዦች ናቸው – እነዚህ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ የህወሓት ሰዎች ናቸው፤ ቀሪዎቹ 107,000 ኢ-ህወሓት ናቸው። ምጣኔያቸው 1: 9 ነው። [በዚህ ምክንያት ጭምር ነው “የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት” በሚለው መጠሪያ ውስጥ “ሠራዊት” ከሚለው ቃል ውጭ አሁን ያለው ሠራዊት ሊጠራበት አይገባም የሚል እምነት ያለኝ]

ስለ 12,000 ዎቹ በጥቂቱ

ከላይ እንዳልኩት 12,000 ዎቹ ሁሉም ህወሓቶች ናቸው፤ ከዚያም በተጨማሪ ሁሉም ጄኔራሎች አሊያም ባለከፍተኛ ማዕረጎች ናቸው። ምናልባት የ Busisness Administration  ወይም የ ባደግ (ILI) Institutional Leadership ዲግሪዎች ይኖራቸው ይሆናል እንጂ በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠኑ የሉባቸውም። የሚያውቁት ጦርነት ዱሮ በልጅነታቸው የተሳተፉበት የጎሬላ ጦርነት ነው፤ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ችከሻዎቻቸው በማዕረግ ምልክቶች ቢከብዱም ልቦቻቸው ያሳበጠው ገንዘብ ነው። ስለሠራዊቱ ሳይሆን እየገቡት ስላለው ፎቅና በአክስዮን ስለያዟቸው ቢስነሶች ሲጨነቁ ነው የሚውሉት።

ስለ 107,000 ዎቹ በጥቂቱ

በሠራዊቱ በተዋጊነትና በዝቅተኛ የማዕረግ ደረጃ ላይ የሚገኙ 107,000 ዜጎች “ኢ-ህወሓታዊ” የሚል የጋራ ባህርይ ብቻ ነው ልሰጣቸው የቻልኩት። በኢትዮጵያዊ ሲቪል ዜጋ ላይ ያሉ ልዩነቶች (heterogeneity) እነሱ ላይ አሉ፤ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በፓለቲካ አስተሳሰብ … ወዘተ በመከፋፈላቸው በጋራ ለመቆም ተቸግረዋል። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በህወሓት አገዛዝ ይማረራሉ፤ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሥርዓቱ ቢለወጥ ደስተኛ ናቸው። ሆኖም ግን በዚህ ለውጥ ውስጥ የእነሱ ሚና ምን እንደሆነ ገና በትክክል የገባቸው አይመስልም። እንደ አብዛኛው ሲቪል አንጀታቸው እያረረ “እኔ ብቻዬን ምን ማድረግ እችላለሁ” እያሉ የታዘዙትን ይፈጽማሉ፤ ግደሉ ሲባሉ ይገድላሉ።

በዚህ ሁኔታ እስከመቼ ይቀጥላል? የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የለውጥ አካል የሚሆነው መቼ ነው? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች መሠረታዊ እና ከባድም ናቸው። ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ለመመለስ ልሞክር።

የተቋማት ትውስታ

ተቋማት ልክ እንደሰው ትውስታ (memory) አላቸው። የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑ በተቋሙ ትውስታ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ሠራዊቱ በመረረው ጊዜ ሁሉ ባለስልጣኑን ፈንቅሎ ራሱን ለመሾም ሲሞክር፤ በዚህም ምክንያት የአገራችንን ፓለቲካ በብርቱ ሲወዘውዝ ቆይቷል። ይህ አሁን አይታሰብም ሊባል አይችልም። 12,000 ዎቹ አለቆች ተመሳሳይ ስለሆኑ ሠራዊቱ የረባ የፓለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻለውም የሚሉ አሉ። እኔ በዚህ አልስማማም፤ የተቋሙ የለውጥ ትውስታም ይህንን አይደግፍም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል። በአዕምሮዬ የሚመጡልኝ ሶስት ዋና ዋና የከሸፉ ሙከራዎች የተመሩት በጄኔራሎች ነበር  –  የ1953ቱ በጄኔራል መንግስቱ ንዋይ፤ የ1981 በነጄኔራል ፋንታ በላይ፣ መርዕድ ንጉሴና ደምሴ ቡልቶ እና የ 2002 ቱ በነጄኔራል ተፈራ ማሞና አሳምነው ጽጌ።  በአንፃሩ፣ የተሳካው እና በኋላ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ደርግ ወደ ሥልጣን ያመጣው የነገሌ ቦረናውና የሀረሩ መፈንቅለ መንግሥት የተመራው በ 10 አለቆች እና በተራ ወታደሮች ነበር። ይህ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ብዬ አላምንም። ይህ እውነታ በተቋሙ ትውስታ (institutional memory) ውስጥ አለ።

የወተት መልዕክት

በሠራዊቱ ውስጥ ያላቸችሁ ወገኖቻችን ዓይኖቻችሁን ገልጣችሁ ዙርያችሁን ተመልከቱ፤ የተቋማችሁን ታሪክ አጥኑ። እናንተ ብዙሀን እና ጥቂቶቹ ህወሓት ሹማምንት 9 ለ 1 ናችሁ ! 9:1 !!!!   ለውጥ ለማምጣት ጄኔራል መሆን አያስፈልግም፤ እንዲያውም በጄኔራል ተመርቶ ስኬታማ የሆነ ለውጥ በተቋሙ ታሪክ የለም። ስኬታማ የሆነ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው በዝቅተኛ ባለማዕረጎችና ተራ ወታደሮች ነበር፤ እሱም ቢሆን መጨረሻው አላማረም።

አሁን ከእነዚህ ሁሉ የተሻለ ማድረግ ይቻላል። ጦር ሠራዊቱ የለውጡ አካል መሆን ይችላል። ጦሩ የተሳተፈበት በዲሞክራሲ ኃይሎች የተመራ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል። ያኔ  107,000 የዛሬ ጦር ሠራዊት አባላት ወገኖቻችን የህወሓቶች ጄኔራሎች የግል አሽከሮች ከመሆን ነፃ ወጥተው የምንኮራባቸው፣ የምንመካባቸው ፕሮፌሽናል የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ይሆናሉ። ይህ ማድረግ ይቻላል፤ ይሆናልም  !!!

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s