ብዙዎች ዋጋ የከፈሉበትን የነጻነት ትግል መተው አይገባም – ግርማ ካሳ

Asrat

በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተወለዱት። ገና የሶስት አመት ሕጻን የነበሩ ጊዜ ቤተሰባቸዉ ወደ ድሬዳዋ ይዞራሉ። ፋሺስት ጣሊያን አገራችንን ሲወር፣ የስምንት አመት ልጅ ነበሩ። በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ከተወረወረ በኋላ፣ ጣሊያኖች በፈጸሙት የብዙ መቶ ሺህ ዜጎች ጭፍጨፋ፣ የእኝህ ሰው አባት ተገደሉ። እናታቸው ብዙ ሳይቆዩ አረፉ። ጣልያን ተሸንፎ. እነ በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በአዲስ አበባ ከሰቀሉ በኋላ ፣ ከድረደዋ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ።

አዲስ አበባ በሚገኘዉ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቅቃሉ። በእንግሊዝ አገር በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ሞያ እንደ አዉሮፓዉያን አቆጣጠር በ1956 ዓ.ም ይመረቃሉ። ኑሯቸዉን በዚያዉ በውጭ አገር ከማድረግ፣ ሕዝባቸዉንና አገራቸውን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ። በልእልት ፀሐይ (ጦር ኃይሎች) ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ። ጥቂት አመታት እንደቆዩም፣ አሁንም በእንግሊዝ አገር.፣ በቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝ ያደርጋሉ። በ1965 ዓ.ም ወደአገራቸው ተመልሰዉ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር፣ የመጀመሪያውን የሕክምና ኮሌጅ፣ በኢትዮጵያ ያቋቁማሉ።

የቀዶ ጥገና ቢላዎችና መቀሶችን እንጂ እጆቻቸው ጠመንጃና ቦምብ ጨብጠው አያውቁም። ሐኪሞች የሚለብሱት ነጭ ካፖርታ እንጂ፣ በየጫካዉና በየበረሃዉ የሚለበሱ አረንጓዴና ቡና አይነት መለዮዎች አለበሱም። ለሕክምና የሚመጡ ሰዎችን ጠረን እንጂ፣ የባሩድን ሽታ አላሸተቱም። ኪኒኖች እያዘዙ፣ ካንሰሮችንና ጠጠሮችን ከሰዉነት ዉስጥ ቆርጠዉ እያወጡ ኢትዮጵያውያንን አዳኑ እንጂ፣ ማንንም ዜጋ ተኩሰዉ አልገደሉም።

እኝህ ሰዉ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ፣ የምንወዳቸው፣ የምናከብራቸዉ እና መቼም የማንረሳቸዉ ታላቁ ፕሮፌሰር አሰራት ወልደየስ ነበሩ።

ፕሮፌሰር አስራት «አመጽን ቀስቅሰሃል» በሚል በ1992 ዓ.ም. ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይታሰራሉ። በዚያኑ አመት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የ«ሕሊና እሥረኛ» ብሎ ሲሰይማቸው፣ በዋስ የመፈታት እድል ያገኛሉ። ደጋግሞ ማሰራና ማሰቃየት ልማዱ የሆነዉ የኢሕአዴግ አገዛዝ፣ ከአንድ አመት በኋላ መልሶ ያስራቸዋል።

ከሁለት አመት የፍርድ ሂደት በኋላ በዲሴምበር 1995 ወንጀለኛ እንደሆኑ ዳኛ ተብዬ የአገዛዙ ካድሬዎች ይወስናሉ። በ1998 በእሥር ቤት ሳሉ በደረሰባቸው መከራ ክፉኛ ይታመማሉ። ሊሞቱ ትንሽ ሲቀር፣ ከፍተኛ የአለም አቀፍ ግፊት ስለበዛ፣ በዲሴምበር 1998 ፣ ይፈታሉ።

ወደ አሜሪካን አገር ሲመጡ ሃኪሞቹ «አስቀድሞ ሕክምና ማግኘት ነበረባቸዉ። ጊዜዉ አልፏል» ይላሉ። ብዙም አልቆየም ከዘጠና ቀናት በኋላ፣ በእሥር ቤት እያሉ ሕክምና ካለማግኘታቸዉ የተነሳ፣ ሕይወታቸው ያልፋል። አቶ መለስ ዜናዊ አገዛዝ በዚህ መልክ ፣ እኝህን አንጋፋ ኢትዮጵያዊ አሰቃይቶ ይገድላቸዋል።

የኢሕአዴግ አገዛዝ እንደ አቶ አሰፋ ማሩ፣ ሽብሬ ደሳለኝ፣ ቢያንሳ ዳባ፣ አረጋዊ ገብረ ዮሀንስ የመሳሰሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ቀጥፏል። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩትን በእሥር ቤት እያንገላታ ነዉ።

download (7)ለሃያ አራት አመታት ያየነዉ ነገር ቢኖር፣ አሁን ያሉት ገዢዎች የፈለጉትን ሲያሰሩ፣ የፈለጉትን ሲዘርፉ፣ የፈለጉትን ሲገድሉ፣ የፈለጉትን ሲያፈርሱ ነዉ። በአገራችንና በምድራችን ባርያ፣ እንግዳ፣ ባይተዋር እየተደረግን ነዉ። ማንም ጉልበተኛ ተነስቶ ቤታችንን ያፈርሳል። በአንዲት ቀጭን ትእዛዝ ከስራችን ያባርረናል። አንገታችንን ደፍተን፣ ሕሊናችንን ሽጠን፣ «እሺ ጌታዬ» እያልን እንደ ባርያ ካልኖርን በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ክብራችን ተጠብቆ፣ ስብዕናችን ተከብሮ የምንኖርበት ሁኔታ ፈጽሞ የለም።

ለዚህም ነዉ «ነጻነታችንን እንፈልጋልን» የሚሉ ወገኖች በእሥር ቤት የሚገኙት። ለዚህም ነዉ ብዙዎች፣ «በአገሬ ታፍኜና ተዋርጄ ከምኖር በባእድ አገር ትንሽ የነጻነት አየር እየተነፍስኩ መኖር ይሻለኛል» ብለው ስደትን የመረጡት።

እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ «እንደ ሕዝብ እሰከመቼ ነዉ የመጨረሻዉ አድራሻን ዉጭ አገር ወይንም ቃሊቲ፣ ቂሊንጦና ማእከላዊ የሚሆነዉ ?» የሚል ነዉ።

ትላንት እነ ፕሮፈሰር አስራትና አሰፋ ማሩ ተገደሉ። ትላንት ብርቱካን ሚደቅሳ ዘግናኝ፣ በማንም ነፈሰ ገዳይ ላይ እንኳን ያልደረሰ፣ ግፍና ቶርቸር ወያኔዎች ፈጽመዉባት፣ አሰቃይተዋት ከቃሊቲ ወጣች። ዛሬ ደግሞ የነፕሮፌሰር አስራትንና ብርቱካን ሚደቅሳን ቦታ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዱዋለም አራጌ ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ናትናኤል መኮንን እና ሌሎች ተክተዉታል።

ሰርካለም ፋሲል ባሌቤቷ እስክንድር ሲታሰር የተናገረችዉ አንድ ትልቅ አባባል ነበር። የማልረሳው።፡«እስክድንር ላመነበት ነገር ነዉ የታሰረዉ። ዛሬ በእስክንድር የደረሰዉ ነገ የእያንዳድንዱን ቤት ያንኳኳል» ነበር ያለቸዉ። ይኸው ከስክንደር በኋላ ስንቱ ታሰረ። ሃብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ ዞን ዘጠኞች፣ ዮናታን ተስፋዬ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ በላይነህ ሲሳይ፣ አስቴር ስዩም …እረ የስንቱ ስም ይዘረዘራል። ነገም፣ ከነገወዲያም እስሩ ይቀጥላል። ሁሉም በየወረፋ ፍዳዉን ይበላል። ወይ ይሰደዳል፤ ወይ ወደ ወህኒ ….. አፉን ለግሞ፣ ባሪያ ሆኖ ፣ እንደ እንስሳ ካልኖረ።

ያ እንዳይሆን ከፈለግን፣ እንግዲህ ትግሉን መልክ ማስያዝ ያለብን ይመስለኛል። እሥረኞችን ለማስፈታት ከሚደረገዉ ትግል አልፈን በመሄድ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ በነአንዱዋለም ላይ የተፈጸመዉን አይነት ግፍ፣ ከአሁን በኋላ እንዳይፈጸም፣ ፍርድ ቤቶች፣ ጥቁር ካፓርት ለብሰዉ የሚቀመጡ ካዴሬዎች የሚፈነጥዙበት ሳይሆን፣ ነጻና ገለተኛ በሆነ መንገድ ፍትህን የሚያሰፍኑ፣ ለዜጎች ሁሉ የሕግ ዋስተና የሚሰጡ እንዲሆኑ እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የአገዛዙን ቀልደና ጨዋታ ለማቆም መታገል አለብን። ለዚያ ዝግጁ ነን ? ዝግጁ ከሆንን ሶስት ነጥቦችን ጠንቅቀን ማወቅ አለብን፡

1. ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ሌላ አደረገም አላደረገም የድርሻችንን ለማበርከት ፍቃደኞ መሆን አለብን። የድርሻችንን እናደርግ ዘንድ የምንለምን ከሆነ፣ የተለያዩ ሰበቦችና ምክንያቶች የማናቀርብ ከሆነ፣ ሌሎች እንዲያደረጉ የምንጠብቅ ከሆነ ዝግጁ አይደለንም።

2. ተስፋ መቁረጥ የለብንም። በቀላሉ እጅ የምንሰጥ ከሆነ፣ በቀላሉ የምንደናገጥ ከሆነ፣ ችግር ነው።

3. እንክርዳዱን ከስንዴው መለየት አለብን። በትግሉ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ መሪዎች እና ፖለቲከኞችን መታገስ የለብንም። ትግሉ የጥቂቶች ተክለ ሰዉነት መገንቢያ ማድረግ የለብንም። ማንም ሰው፣ ማንም ሃላፊነት ከትግሉ በላይ እንዳልሆነ መረዳት አለብን።

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s