ሁላችንም የየድርሻችንን እናንሳ (ከይገርማል)

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደወያኔ ያለ የተበላሸ አስተዳደር እንዳልተፈጠረ የሚስማሙ ብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ብዙሀኑ ያልሁበት ምክንያት ቢያንስ የወያኔ ቁንጮወች እንደአሁኑ ያለ ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ልማት ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም እንደሚሉ ስለማውቅ ነው::

በኢትዮጵያ ታሪክ እንደወያኔ ያለ ብልሹ አስተዳደር ተከስቶ አያውቅም ሲሉ የሚከራከሩት ወገኖች ወያኔ መራሹን መንግሥት:

 • ሕዝብን በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ጎጠኝነት አብቦ የሚያስተሳስረን የአንድነት ክር እንዲረግብ ካደረገ በኋላ እያናጠለ እየተጫወተብን ነው:
 • ታላቋን ትግራይ ለመመስረት እንዲያመቸው ቀደም ባሉት በየትኛውም ጊዚያት የትግራይ ክልል አካል መሆናቸውን የሚያሳይ የሰነድም ሆነ የሰው ማስረጃ ሳይኖርና ህዝቡ ሳይፈቅድ ለም የሆኑ የአማራ አካባቢወችን በግድ ወደትግራይ ክልል እንዲካለሉ አድርጎ የተቃወሙትን እያፈነ ዳብዛቸውን እያጠፋ ነው:
 • የሀገራችንን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ሀገራችንን ወደብ አልባ እንድትሆን አድርጓል:
 • ታሪካውዊ ድንበራችንን በማፍረስ መሬት ቆርሶ ለሱዳን አሳልፎ ሰጠብን:
 • “መንግሥት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” የሚለውን መሰረታዊ መርህ በመጣስ ከቅዱስ መጽሀፍቱ ትእዛዛት ውጭ የሆኑ ስርአትና አስተምሮወችን በማስፋፋት: የተቃወሙትን ምእመናንና የሀይማኖት አባቶችን በተለያየ መንገድ በማስወገድ: አላማውን የሚያስፈጽሙትን የሀይማኖት ፖለቲከኞችን በጉልበት እየሾመ የሀይማኖት ተቋማትን የካድሬ መፈንጫ አድርጓል:
 • ለሕዝብ ፍቅርና ክብር የሌለው በተንኮልና በውሸት ተወዳዳሪ አልባ ወራሪ ሀይል ነው:
 • ንጹሀን ዜጎችን ያላግባብ በተለያየ መንገድ ይቀጣል (ከስራ ያባርራል: ከመኖሪያ ያፈናቅላል: ያስራል: ይደበድባል: ንብረት ይወርሳል/ያወድማል: ይገድላል):
 • በሰላምና በፍቅር አብሮ የኖረውን ኢትዮጵያዊ በደረጃ መድቦ በአንደኝነት ቦታ የተቀመጠውን ትግራይ በሁሉም ነገር ቀዳሚና የበለጠ ተጠቃሚ ሲያደርግ በመጨረሻ ቦታ የተቀመጠውን አማራ ደግሞ ታሪካዊ ጠላት በሚል ፈርጆ እጅግ ዘግናኝ ግፍ ፈጽሞበታል/ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችም ግፍ እንዲፈጽሙበት ቀስቅሷል/ አስተባብሯል:
 • የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ሙልጭ አድርጎ ዘርፎ ከሀገር አሽሽቷል:
 • ጥቂት የማይባሉ የአንደኛ ደረጃ ዜጎችና የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ ባለስልጣኖች ከዜሮ ተነስተው ሚሊዮነር ሲሆኑ ሌሎች ግን የነበራቸውን ተነጥቀው ለድህነት እንዲጋለጡ አድርጓል:
 • አንደኛ ደረጃ ዜጎችና አንጋቾች የተሻለ የስራ እድልና ጥሩ ደመወዝ እንዲያገኙ ሲደረግ ሌሎች ግን ስራ የማግኘት እድል ተነፍጓቸው ለሴተኛ አዳሪነት: ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለስደት ተዳርገዋል:

ወዘተ በማለት ይከሳሉ::

“ወያኔ ምንም ሀላፊነት የማይሰማው ፍጹም ግብረዲያብሎስን የተላበሰ የእኩዮች ስብስብ ነው” ሲሉ የሚጠሩትን ሰዎች ሀሳብ እኔም ራሴ የምጋራ ስሆን: ከእውነታው ጋር ለመታረቅ እና ችግሩን ወደአንድ ወገን ብቻ መግፋት መፍትሄ እንደማያስገኝ በማመን ከወያኔ ውጭ ባሉት ሌሎች አክተሮች ላይ የሚታዩ ጉልህ ችግሮችንም ለማንሳት ወድጃለሁ:: ይህን ስል ለመሆኑ አንተ እራስህ ምን አድርገህ ነው ሌሎችን ለመተቸት የምትነሳ የሚሉኝ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ አውቃለሁ:: መልሴ አንድም ከተወቃሾች ውስጥ ራሴም አለሁ ሌላም “ምክሬን እንጅ ተግባሬን አትዩ” የሚል ነው:: አንድ አጫሽ ሰው ሌሎችን እንዳያጨሱ ቢመክር “ራስህ ያላደረከውን ነገር ሌላው እንዲያደርግ መምከር የለብህም” ሊባል አይገባም:: እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር ያለው ተረት ማንሳት እፈልጋለሁ::

“አንድ የቄስ መምህር ነበሩ:: መምህሩ ሲበዛ መጠጥ የሚወዱ ሰው ከመሆናቸው በስተቀር በሙያቸው ነቃፊ የሌለባቸው ሊቅ የተባሉ ነበሩ:: ፊደል አስቆጥረው: ዳዊትና ድጓ አስደግመው: ቅኔ አስዘርፈው ለታላላቅ ቦታ ያደረሷቸው ታዋቂ ሰዎች ምክርና ርዳታ የሚያገኙት እኒህ አባት ዘንድ ሄደው ነበር::

እኒህ በሙያቸው አንቱ የተባሉት አባት በእለት ከለት ኑሯቸው ግን ውስጥ ውስጡንም ቢሆን ይነቀፉ ነበር:: መምህሩ የሚነቀፉት የመጠጥ ሱስ ሰለባ በመሆናቸው ነበር:: ይህን ድክመታቸውን እሳቸውም ቢሆኑ አሳምረው ያውቁታል:: ሆኖም እንደጠላ ሰፈፍ በቀላሉ እፍ ተብሎ የሚከላ ወይም የሚገፈፍላቸው ስላልሆነ መጠጣቱን ቀጥለውበታል:: ሲያስተምሩ ይቆዩና “በሉ እናንተ ደግሞ ተጠያየቁ!” ብለው በአቅራቢያ ወደምትገኘው መሸታ ቤት ጎራ ይሉና አንድ ሁለት መለኪያ አረቂ ተጎንጭተው ይመለሳሉ::

የመጠጥ ምርኮኛ የሆኑት እኒህ አባት ተማሪወቻቸው የርሳቸውን ፈለግ ተከትለው የመጠጥ ተገዥ እንዳይሆኑ በማሰብ ዘወትር “ልጆቸ አደራ መጠጥ ወዳጅ እንዳትሆኑ! መጠጥ ጤና ይጎዳል: ሀብት ይጨርሳል: ትዳር ያፈርሳል: መልክ ያበላሻል: ማህበራዊ ክብር ያሳጣል:: አደራ ከመጠጥ ራቁ!” ሲሉ  ይመክራሉ::

አንድ ቀን መምህሬ የእለት የትምህርት ፕሮግራማቸውን አጠናቀው ሲጨርሱ እንደልማዳቸው ልጆቹን መምከር ይጀምራሉ:: ይኸኔ ከተማሪወቹ መሀል አንዱ አፈፍ ብሎ ተነስቶ “መምህር ርስዎ እየጠጡ እኛን አትጠጡ ይሉናል:: መጠጥ መጥፎ ከሆነ ለምን እርስዎ ይጠጣሉ?” ሲል ይጠይቃቸዋል::

መምህሩ እጅግ እዝን: ትክዝ ብለው ቆዩና እንዴት የመጠጥ ተገዥ ሊሆኑ እንደቻሉና መጠጥ በመውደዳቸው ምክንያት የደረሰባቸው ፈተና ምን እንደሆነ ተረኩላቸው::  በመጨረሻም ” አያችሁ ልጆች እኔ ከዚህ ሱስ ለመንጻት  ብዙ ታግያለሁ:: ግን ተብትቦ የያዘኝ አባዜ እንዲህ በቀላሉ ሊለቀኝ አልቻለም:: እናንተን መምከር ያለብኝ የእኔን ፈለግ ተከትላችሁ እኔ የማደርገውን እንድትደግሙ ሳይሆን ጠቃሚውን ከጎጅው ለይታችሁ መሆን የሌለበትን ነገር ትታችሁ መሆን ያለበትን ጠቃሚ ትምህርት እንድትጨብጡ ነው:: እስቲ እናንተን መልሸ ልጠይቃችሁ ‘ገጣባ አህያ በአቆማዳ ማር ተጭና ብትመጣ ማሩን ትበላላችሁ ወይስ አትበሉም?’” ሲሉ ተማሪወቻቸውን አማተሩ::  ከተማሪወች መሀል አንዱ ብድግ ብሎ “ማሩ ያለው ባቅማዳ ነው:: ከገጣባው ጋር ስላልተገናኘ አልተበከለም: ንጹህ ነው:: ስለዚህ እኔ በበኩሌ እበላዋለሁ::” ብሎ ሲቀመጥ ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ “ማሩንማ እንበላዋለን” ሲሉ ተቀባበሉ:: መምህሩ ፊታቸው በደስታ ፈታ ብሎ “ልክ ብላችኋል:: ማሩ አልተበከለም:: ስለመጠጥ መጥፎነት ያስተማርኋችሁ ትምህርትም ንጹህ ነው አልተበከለም:: ስለዚህ ያስተማርኋችሁን ትምህርት እንደማሩ እዩትና ተጠቀሙበት:: ገጣባዋ አህያ ማለት እኔ ነኝ::” አሏቸው ይባላል::

ከዚህ ቁምነገር አዘል ተረት የምንማረው ነገር አለ:: ማንም ይሁን ማን ሊመክር ወይም ሊያስተምር እንደሚችል:: መመዘን ያለበት በሚሰጠው ትምህርት እንጅ በሰውየው ግላዊ ባህሪ ወይም ተግባር መሆን የለበትም:: በርግጥ ራሳቸውን ከጣሉና በበጎ አርአያነት ከማይታዩ ሰዎች ትምህርት መውሰድ ይቸግር ይሆናል:: ያም ሆኖ ግን ሰው መምከር ያለበት ራሱ የሚያደርገውን ሌሎች እንዲደግሙት በማሰብ ሳይሆን ትክክለኛ ነው ብሎ የሚያምንበትን መሆን አለበት ብየ አምናለሁ:: ከዚህ ተነስቸ ነው እንግዲህ እኔም ትዝብቴንና ቅሬታየን ማሰማት እንዳቅሜም ምክር ጣል ማድረግ የፈለኩት::

የምጽፈው ትክክል ነው ብየ የማምነውን ነገር ለማካፈል እንጅ ማንም እንዲወደኝም ሆነ እንዲጠላኝ በማሰብ አይደለም:: ለነገሩ ይህ ሁሉንም ቆንጣጭ የሆነው አቀራረቤ ጠላት እንጅ አወዳሽ እንደማያስገኝልኝ መገመት እችላለሁ:: ምዝግዝጌ ሙጭ የሚጠርግ በመሆኑ እኔንም የሳተ አይደለም:: ቢሆንም ተነካሁ ያለ ሁሉ ጣቱን ወደሌላ መቀሰሩን ትቶ ራሱን ወደ ውስጥ አይቶና ገምግሞ ካሳለፈው ጥሩም ሆነ መጥፎ ተሞክሮ ትምህርት እንዲወስድና ለበጎ ነገር እንዲነሳሳ አሳስባለሁ:: ቅድሚያ በራሴ ላይ  ፈርጀ ድርሻየን ከወዲሁ አንስቻለሁ: :

ትዝብቴና ቅሬታየ የሚያርፈው በአካልና በመንፈስ ካልጎለበቱ ሕጻናት: ከአካልና ከዐዕምሮ ጉዳተኞች: በእድሜ ከገፉ ሰዎችና ከአቅመደካሞች በስተቀር በሌሎች በሁሉም ላይ ይሆናል:: በዚህም መሰረት በጣም ባጭር ባጭሩ ወያኔ: የክልል መንግስታት: ተቃዋሚ ፓርቲወች: የፖሊስና የጦር ሰራዊት: ምሁራን: ወጣቱ: ቀሪው ብዙሀን (ጭራሹን ዘመናዊ ትምህርት ያልነካው ወይም በትምህርቱ ብዙ ያልገፋው አነስተኛ ሲቭል ሰርቫንቱ: ነጋዴው: አርሶ አደሩ: ወዘተ): የሀይማኖት አባቶች: በሚል ከፍየ በያንዳንዱ ክፍል በተካተቱት የሕብረተሰብ አካሎች  የተፈጸሙ ወንጀሎችን/ ሕጸጾችን ወይም በተግባር ሊያውሏቸው ይገቡ የነበሩ ነገር ግን ያልተገበሯቸው በጎ ርምጃወችን ጠቅለል ባለ መልኩ በመዳሰስ ትዝብቴንና ነቀፌታየን አቀርባለሁ:: እያንዳንዱን ነገር ልዘርዝር ቢባል የማይቻል በመሆኑ የትዝብቴና የቅሬታየ መነሻ የሆኑትን ጥቂት ነጥቦች ብቻ ለማንሳት እገደዳለሁ::

 1. ወያኔ:- ውሸታም: አታላይ: ተንኮለኛ: ቂመኛ: ጸረ አንድነት: ታሪክና ቅርስ አውዳሚ: ከፋፋይ: ጨቋኝ: የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ: በሰው የሚነግድ (ሕጻናትን ሳይቀር ወደውጭ እየላከ: በማይመለከተው ጦርነት ወታደር እያሰማራ በምትኩ ገንዘብ የሚቀበል): አፋኝ: ገዳይ: – – – ባጠቃላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ለህዝቡና ለሀገሩ ደንታ የለሽ ዘራፊና አውዳሚ ቡድን በመሆኑ ከቅሬታ አልፎ ጥርስ ከነከሱበት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ:: ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ወያኔን ይጠሉታል ቢባል “ሀሰት!” የሚባል አይሆንም:: መላው ኢትዮጵያዊ ይህን ቡድን ከነሰንኮፉ ነቅሎ የሚጥልለት ሀይል ይፈልጋል:: በየቦታው የሚሰማው ድምጽ ወያኔ እንዲወገድ የሚያስተጋባ እንጅ ስለመጭው የሚጨነቅ ብዙም አይስተዋልም:: ምንም ቢሆን አሁን ካለው ስርአት የከፋ አይመጣም እየተባለ ነው:: ወያኔ ግን አንዱን ገድሎ ሌላውን ተጠያቂ ያደርጋል: የጥቅም ተጋሪወቹን አሰልፎ ስለዴሞክራሲያዊነቱና ስለልማታዊነቱ ይሰብካል:: የምንሰራው ህዝባዊ ልማት ለማረጋገጥ ነው ሲል ዘወትር የሚሰማ ሲሆን የትኛውን ህዝብ ማለቱ እንደሆነ ግን ለማንም ግልጽ አይደለም::  ስለህዝቡ ጉዳትና ጥቅም መናገር ያለበት ህዝቡ ነው ወይስ ወያኔ? ይህ ቡድን ከትዝብት: ከቅያሜና ከጥላቻ በላይ ሊታይ የሚገባ ለመጥፎነቱ ቃላት ሊገኝለት የሚያዳግት የሚገርም ቡድን ነው:: ተወደደም ተጠላም ዕውነቱ ይኸው ነው:: ሕዝብን በተለያየ መንገድ እያጠቃ ህዝባዊ ነኝ ማለት ስለማይቻል የወያኔ ቁንጮወች ወደህሊናችሁ ተመለሱና ለህዝብ የለውጥ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ስጡ:: ምንም ይሁን ምን ወያኔ አሁን ያለውን ጥንካሬ ይዞ ለልጅ ልጅ ሊተላለፍ አይችልም:: ከታሪክ ተማሩ:: ካለፈ በኋላ ከመቆጨት ሳይመሽ ንስሀ መግባትና ይቅርታ መጠየቅ ብልህነት ነው::
 2. የክልል መንግስታት:- ሰብአዊ ክብር የሌላቸው: ፍጹም ለሆዳቸው ያደሩ: እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ክብርና ወገንተኝነት የሌላቸው: ፈሪወች: የወያኔ አንጋችና ጉዳይ አስፈጻሚወች: – – – በመሆናቸው ከወያኔ በላይ ሊጠሉ የሚገባቸው ናቸው::

 

ከስልጣን ላይ ቁጭ ብለው ግን አድርጉ የሚባሉትን ብቻ የሚያደርጉ የየክልሉ ባለስልጣናት ሮቦቶች እንጅ ሰብአዊ ፍጡሮች ሊባሉ አይችሉም:: ለምሳሌ ያህል የአማራን ክልላዊ መንግስት እንውሰድ:: አማሮች   በየአካባቢው ግፎቹ ሁሉ በአይነት ሲፈጸሙባቸው የአማራ አስተዳዳሪ ነኝ የሚለው ብአዴን ለአመል ያህል እንኳ ሲያጉረመርም አልተሰማም:: እንዲያውም በአመራሮቹ አማካኝነት አንድም በአማሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በመቀስቀስ በሌላም በኩል በአማሮች ላይ የደረሰን ግፍ በማስተባበል በቁስል ላይ ሚጥሚጣ እየጨመረ ስቃይን የሚያበረታ ሆኖ የወያኔን አላማ ለማሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየሰራ ያለ ቡድን ነው::

 

ብአዴን የአማራው ወኪልና ተቆርቋሪ ቢሆን ኖሮ ”አማራ ሆኘ ባልተፈጠርሁ ኖሮ!” በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ ”የሚደርስብንን ማንኛውም ነገር ከዚያው ከህዝባችን ጋር ሆነን እንቀበላለን” በማለት በድፍረት “እኛ አማሮች ነን” ለሚሉት ወልቃይቴወች ከጎናቸው ቆሞ ለመብታቸውና ለነጻነታቸው ይታገል አልነበር!

 

አይደለም በሀገር ውስጥ በውጭ ሀገር የሚኖር ዜጋ እንኳ አላግባብ ለጉዳት ተዳርጓል በሚል የሀገሩ መንግስት ሊከራከርለት እንደሚችል እየታወቀ የሰው ልጅ በራሱ ሀገር በደል ሲፈጸምበት ደፍሮ ”አይዞህ አለሁ”  የሚል ወኪል ማግኘት አለመቻሉ እንዴት ያሳዝናል! ወንድሞቹና እህቶቹ ታግተው ሲገረፉ ጩኸታቸውን እየሰማ: የጣእር ድምጻቸውን እያዳመጠ አንጀቱ ችሎ አርፎ የሚቀመጥ ሰው የቱ ላይ ነው ጋሻነቱ: የቱ ላይ ነው መከታነቱ! አባቶቻችን ነጻነትና ሀገር ያወረሱን ደምና አጥንት ከፍለው እንጅ ተንበርካኪ ሆነው አልነበረም::

 

ሌሎች የክልል መንግስታትም ቢሆኑ ከወያኔ ጋር ተባብረው ሕዝባቸውን የሚያጎሳቁሉ በመሆናቸው የሚያሳፍሩ ናቸው::  የየክልሉ ባለስልጣናት ወያኔን ፈርተው/አክብረው ህዝባቸውን ደግሞ ንቀው ከሆነ ወይም ለስልጣንና በሙስና ለሚሰበስቡት ጥቅም በልዋጩ ህዝባቸውን ለወያኔ ጥቃት  ማጋለጥ ተገቢ ነው ብለው አምነው ከሆነ ምን ማለት ይቻላል! ግን አንድ ነገር ልብ በሉ! የምትበሉት የህዝብ ስጋ የምትጠጡት የህዝብ ደም ነው::

 

የራሳችሁን ወገን የምትመዘብሩና የምታስመዘብሩ: የምታሰቃዩና ለስቃይ አጋልጣችሁ የምትሰጡ እናንተ የወያኔ አሸርጋጆች ዐዕምሯችሁን አጽድታችሁ ጆሯችሁን ሰጥታችሁ የህዝብን እሮሮ ስሙ: አይናችሁን ከፍታችሁ ኑሮውንም እዩ:: የህዝብ ድጋፍ የሌለው አካል መውደቁ አይቀርም: ከውድቀት በኋላም መሸሸጊያ ሊቸግር ይችላል:: ሕዝብ መጠለያ ቤት: መደበቂያ ዋሻ: መከላከያ ሀይል መሆኑን አምናችሁ ከህዝባችሁ ጎን ቁሙ::

3.ተቃዋሚ ፓርቲወች:- እኒህ ቡድኖች ደግሞ የሚገርሙ ናቸው:: ስለህዝብና ስለሀገር ያለቅሳሉ በተግባር ግን ስለህዝብና ስለሀገር አይሰሩም:: የህዝብን ትግል እንደወያኔ ሁሉ ከፋፍለውታል: ለወያኔ ካላቸው ጥላቻ ይልቅ እርስ በርሳቸው ያላቸው ጥላቻ ያይላል: አንዳንዶቹ ሰፈርተኞች ናቸው: አብዛኞቹ አድመኞችና አግላዮች ናቸው: መጠላለፍን መለያቸው ያደረጉ ስለሆኑ ከፊት ለመታየት ሲሉ ብቻ ሁሌም ከላይ ያለውን ጠልፎ ለመጣል የሚያሴሩ ናቸው (ለዚህ አቢይ ምሳሌ የሚሆነው አንድ ድርጅት የነበረው ምንም የፕሮግራም ወይም የአላማና የግብ ወይም የታክቲክና የስትራቴጅ ልዩነት ሳይኖር ለሁለትና ለሦስት መከፈሉ ነው)::

እናንተ አፋዊ ተቃዋሚወች: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን አጥብቦ መተማመንና አንድነትን በመገንባት አሁን ያለውን አስከፊ ስርአት ለማስወገድና ለሁላችንም የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ትግል በማፋለስ ለወያኔ እድሜ መቀጠል ጉልህ ሚና እየተጫወታችሁ ስለሆነ ከስህተታችሁ ተማሩ::

 1. የፖሊስ ሰራዊት: የጦር ሰራዊት: የየአየርሀይል እና የባህርሀይሉ?:- ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደምንረዳው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሰራዊቱ አባላት ትግሉን ከመደገፍ አልፈው ትግሉን መምራት እንደቻሉ ነው:: በ1966 ዓ.ም የተከሰተው እውነታ ይኸው ነበር:: ራሱን ጊዚያዊ አስተዳደር ደርግ ብሎ የሰየመው መለዮ ለባሽ በጥቂት ራስ ወዳድ መኮንኖች ተጠልፎ አላማውን እንዲስት ተደረገ እንጅ መነሻው የህዝቡን ትግል ማገዝ የሚል ነበር::

ዛሬ ላይ የሚታየው የሰራዊቱ ሁኔታ ግን እጅግ የሚያሳፍር ነው:: መሳሪያን ያህል ነገር ታጥቆ የራስን ህዝብ ጨፍጭፍ ሲባል “ለምን?” ማለት አለመቻል ከታጠቁት መሳሪያ አለመሻልን ያሳያል:: ሀገሬንና ህዝቤን እከላከላለሁ ብሎ ቃለመሀላ ፈጽሞ ግንባሩን ለጥይት ደረቱን ለጦር ለመስጠት የተሰለፈ ሰራዊት ከህዝባዊነት ደረጃ ወርዶ የአንድ ጠባብና ባለጌ ቡድን መሳሪያ በመሆን ህዝቡን መጨፍጨፍ ከአላማ ጋር የሚጣረስ: ከሰውነት ደረጃም ዝቅ የሚያደርግ ተግባር ነው:: ይባስ ብሎ በዘርና በቋንቋ በተከፋፈለች ሀገር ውስጥ የሰራዊት አባል ሆኖ እያለ በራሱ ዘር ላይ በታቀደ ጥቃት ተሳታፊ የሚሆን የሰራዊት አባል ግብኑን ያለ: ማስተዋል የተሳነው: ሳይሞት የሞተ ነው:: ጠበንጃውን ከጠላቱ ላይ ሳይሆን ከወገኑ ላይ የሚወድር ወታደር እንዴት ሕዝባዊ ሊሆን ይቻለዋል!

በተለይ የቡድን አሽከር በመሆን በየሰፈሩ እያውደለደለ የህዝብን ድምጽ የማፈንና መብቱን የመርገጥ ተልእኮ አንግቦ ሰላማዊውን ዜጋ የሚገድለውና የሚያሰቃየው የሰራዊቱ አባል ሕዝባዊ ወታደር ነኝ ብሎ ካመነ ቆም ብሎ አስቦ ማን ላይ ማነጣጠርና ማለም እንዳለበት መወሰን ይኖርበታል::

 1. ምሁራን:- በኢትዮጵያ ከሚኖረው ህዝብ መሀል ከ80% በላይ የሚሆነው ህዝብ (በግምት) ከእጅ ወደአፍ በሆነ ኑሮ የሚኖረው አርሶአደርና አርብቶአደር ህዝብ ነው:: ከ80% በላይ የሚሆነው የከተማ ህዝብም (በግምት) ቢሆን ከእጅ ወደአፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ ያለ ህዝብ ነው::

ይህ ህዝብ ከሚያገኛት እየቆነጠረ አስተምሮ ለቁምነገር ያበቃቸው እጅግ በጣም አብዛኛው ምሁራን ድምጻቸውን አጥፍተው ወያኔን እያገለገሉ ነው:: አንዳንዶች ደግሞ የወያኔ ተቃዋሚ ሆነው ብቅ የሚሉት ከወያኔ ጋር የጥቅም ግጭት ውስጥ ሲገቡ ነው:: የወያኔን ስራ በገሀድ አውግዘው የቀረበላቸውን መደለያ ገፍተው ወያኔ እንዲወገድና የስርአት ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉ ምሁራን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል:: በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ የተሰለፉ አንዳንድ ምሁራንም ቢሆኑ በሚያለያይና በሚያዳክም ስራ ላይ በመሰማራታቸው የነርሱ ድርሻ ትግሉን ከመደገፍ ይልቅ የሚጎዳ አድርጎታል::

በመሰረቱ ለህዝብና ለሀገር ተቆርቋሪ ሆነው ለተሻለ ነገር በቀዳሚነት መሰለፍ የነበረባቸው ምሁራን ከዳር ሆነው ሲመለከቱ ማየት እንዴት ያሳዝናል! በነጻነት እጦትና በድህነት እየማቀቀ ያለውን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ማስተባበርና ማታገል ሲገባቸው “እኔን ካልነካኝ የራሱ ጉዳይ” በሚል መንፈስ ዝምታን መምረጣቸው በእጅጉ የሚያስተዛዝብ: የሚያስቀይምና የሚያስጠላ ተግባር ነው:: ለይቶላቸው የወያኔ አጋፋሪ ሆነው እዚህና እዚያ ጥልቅ እያሉ በህዝብ ላይ የሚቀልዱት ተማርን ባዮችን ምን ማለት እንደሚገባ አላውቅም:: መማር ለዚህ ከሆነ ትምህርትባፍንጫ ይውጣ!

አንድ የማያታበለው ሀቅ ብዙወቻችን የወያኔን መወገድ ከመውደድ አልፈን እንደምንናፍቅ ነው:: የናፈቅነው ነገር ግን ካለወጪ በብላሽ የሚገኝ አይደለም:: ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በአንድ ወቅት ሲናገሩ “መሬት የሚሸጥ የሚለወጠው በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነው” ነበር ያሉት:: ይህ ማለት መሬታችንን እንኳ ለመሸጥ ኢህአዴግ መሞት አለበት ማለት ነው:: ኢሕአዴግ እያለ መሬት መሸጥ መለወጥ አይቻልም ማለት ደግሞ ስልጣናችንን አሳልፈን አንሰጥም ማለት ነው:: ኢሕአዴግ ስልጣን ካጣ መሬት እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ በምን ሁኔታ ማስቆም ይቻለዋል? ለዚያም ነው ሰውየው በውስጠ ወይራ አነጋገር “ስልጣን መቸም አሳልፈን አንሰጥም ሲያምራችሁ ይቅር” ያሉን:: እና ምን እናድርግ? እንደእኔ ከሆነ መልሱ “መታገል” የሚል ነው:: ሌላ የተሻለ አማራጭ አለ የሚል ሰው ካለ እሰየው ነው:: መልሱ “መታገል” ነው በሚለው ከተስማማን ግን ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ውስጥ እያንዳንዳችን ምን ያህል ተሳትፎ አድርገናል?  የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል:: መቸም በሌሎች ኪሳራ ለውጥ የምንመኝ ልንሆን አንችልም:: ሁላችንም ተረባርበን ይህን አስከፊ ስርአት እስካልለወጥን ድረስ ዘርፈ ብዙው ችግር መቆሚያ አይኖረውምና::

 1. ወጣቱ:- ወያኔንና ሻእቢያን ጨምሮ የያን ትውልድ የአላማ ጽናት ጠልቆ ለተመለከተው እጅግ የሚያስደምም ነው:: የወያኔ ጥቂት አጋንንት የብዙሀኑን የመስዋእትነት ውጤት ነጥቀው ለራሳቸው ፍላጎት መጠቀሚያ ቢያደርጉትም የታጋይ ወጣቶቹ ጽናትና ቁርጠኝነት ግን ጉድ የሚያሰኝ ነው::

የኢሕአፓ እንቡጦች የፈጸሙት ገድል እንደ ቀልብ ሰራቂ ድርሰት ደግመው ደጋግመው ቢሰሙት የማይሰለች: ሁሌም ልብን በኩራት የሚያሳብጥና ስሜትን የሚኮረኩር መሳጭ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑን የሚክድ ካለ እሱ ውሸታም ነው::

የዚያ ትውልድ ወጣቶች ለትግል ሲነሱ ለድርጅት የተመቻቸ ጊዜም ሆነ አደራጅ ሀይል አልነበረም:: ከፊሎቹ የሀገራቸው ኋላ መቅረትና የህዝብ ብሶት እረፍት ነስቷቸው:  እንደወያኔ ያሉትም በውስጣቸው የሰነቁትን ቂምና ጥላቻ ቋጥረው በገንቢም ይሁን በአፍራሽ ጎን ተሰልፈው ለአላማቸው በጽናት ተዋድቀዋል::

የዛሬ ወጣቶች ግን በባህሪም ይሁን በግብር ከእኒያኞቹ በእጅጉ ይለያሉ:: እምቅ ሀይል ያላቸው እኒህ የሀገርና የወገን ፈጥኖ ደራሾች ለነጻነት: ለዴሞክራሲ: ለፍትህና ለእኩልነት ሊታገሉ ሲገባ ለጥቃት ሲንበረከኩ: የአደንዛዥ እጽ: የወሲብና የመጤ ባህል ምርኮኞች ሆነው በአልባሌ ቦታ ሲውሉ ማየት የሚጠዘጥዝ ህመም ይፈጥራል:: አፍላ ጉልበት ያላቸው የማህበረሰቡ ክንዶች መስመራቸውን ስተው ወንዱ ሱሪውን ጭኑ ድረስ አውርዶ ሴቷ ራቁቷን የሆነች ያህል ተገላልጣ መታየትን የስልጣኔ መገለጫ አድርገው ከመኩራራትና ያለፈውን ትውልድ ከመውቀስ አልፈው ለተሻለ ነገር ሊሰለፉ ባለመቻላቸው የተጫነብንን ችግር መቅረፍ ተስኖናል:: ጊዚያቸውን ቁምነገር በሌለው ባልባሌ ቦታ ስለሚያሳልፉት ማህበራዊ እሴቶቻችንን: ባህልና ወጋችንን ከመበከል ያለፈ ስራ ሊሰሩልን አልቻሉም::

ወጣቱ በትምህርት ፖሊሲው ብልሹነት: በስራ እድል እጦት: በድህነትና በመሳሰሉት ቅስም ሰባሪ ጫናወች የተነሳ ለተስፋ መቁረጥ እንዲገፋፋ የወያኔ መንግሥት በተጠና መንገድ ሁኔታውን አመቻችቷል ማለት ይቻላል:: ይሁንና መሰናክሉን አክሽፈው ይህን ሀላፊነት የጎደለውን መንግስት በማስወገድ የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ሲገባቸው በተጠመደባቸው ወጥመድ ተይዘው በዚያው ደንዝዘው ተቀምጠዋል:: በዚህም ምክንያት አይደለም ሀገርና ህዝብን ራሳቸውንም ረስተው አፍላ ጊዜያቸውን ለከንቱ ነገር የሚያውሉ አላማ ቢሶች: ለሀገርና ለህዝብ የማያስቡ: ታግሎ የስርአት ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ሽሽትና ስደትን አማራጭ ያደረጉ ፈሪወች: አድርባዮች: ለጥቅም ተገዥወች: አንዳንዶች ታጋይ ነን የሚሉት ቢሆኑም ራሳቸውን ችለው መቆም የተሳናቸው ልፍስፍሶች: በጥቅሉ የግል ኩሩ ስብእና የሌላቸው በዋልፈሰሶች በመሆናቸው ለትዝብት የተጋለጡ ማፈሪያወች ሆነዋል::

ይህን ስል ራሳቸውን መስዋእት አድርገው ህዝባቸውን ለመታደግ በሰላማዊ መንገድም ይሁን በትጥቅ ትግል እየታገሉ ያሉ ጠንካራ ልጆች የሉም ለማለት አይደለም:: እነርሱማ ከማንም በላይ ስራቸው የሚናገርላቸው መኩሪያወቻችን ናቸው:: እኔ እያልሁት ያለሁት ብዙሀኑ ወጣት ምን እያደረገ ነው ነው?

በደርግ የመጀመሪያ አመታት የነበረው ነፍስ ያወቀ ሁሉ ማለት ይቻላል ወታደራዊ ሀይሉ ስልጣን እንዲያስረክብና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ሲል አንደበት ከሚገልጸው በላይ መስዋእትነት ከፍሏል:: ለዚያም ነው ደርግ ወጣት ሆኖ በተገኘው ላይ ሁሉ የቀይ ሽብርና የነጻ እርምጃ አዋጅ ያወጀው:: ይሁንና እኒያ ወጣቶች በህዝብና በሀገር ላይ የሚፈጸመውን በደል እያዩ በፍርሀት የተነሳ አንገታቸውን ሰብረው የሚኖሩ አልነበሩም::

የዛሬው ብዙሀኑ ወጣት ምን እየሰራ ነው? በኦሮሚያ የተነሳውን ተቃውሞ በድፍረት የተቀላቀሉት ስንቶች ናቸው? ቀሪውስ ምን አደረገ? በተለይ የአማራ ወጣቶች ምን እያደረጉ ንው? ቤተሰቦቻቸው: ወገኖቻቸው ሊነገር እንኳ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ሲገደሉ ምን አደረጉ? ሲፈናቀሉ: ሀብት ንብረታቸው ሲወረስ: ሲታሰሩ: ሲገረፉ ምን ምላሽ ሰጡ? እና እውነት አማራ ልጅ ወለድሁ ማለት ይቻለዋል? እኛስ ደፍረን አዎን ዘር ተክተሀል ብለን ለማለት ሞራሉ ይኖረናል?

 1. ብዙሀኑ ሕዝብ:- በዚህ ክፍል የተካተቱት ሰዎች በተለይ በትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው እነርሱን መውቀሱ ትክክል ላይመስል ይችላል:: ይሁንና በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያስተዋልናቸው አኩሪ ተግባሮች በሙሉ በምሁራን የተከወኑ አልነበሩም:: ግፍን መሸከም ያልፈቀደው ወገን መሸፈቱ ጥንትም የነበረ ነው:: በስማበለው ተሰባስበው: በየጎበዝ አለቃ ተደራጅተው ሀገርን ከጠላት ሲከላከሉ ጭቆናንም ሲቃወሙ የኖሩት ወገኖች ለትግል የተነሱት ተፈጥሮ ባደለቻቸው ዐዕምሮና በልምድና ተሞክሮ ባገኙት እውቀት ታግዘው እንጅ የአስኳላ ትምህርት ስለተማሩ አልነበረም:: ዛሬ ደግሞ ዘመኑ ሰልጥኗል:: መረጃውም በቀላሉ ይገኛል::

ዛሬ ላይ ሌላው ይቅርና “ጊዮርጊስ ይከተልህ: በል ሂድ!” ብሎ መርቆ ልጁን ወደትግል የሚሸኝ ወላጅም እየጠፋ ነው:: በዚህም ምክንያት ወላጅና ልጅ በፍርሀት ተጨብጠው ሞትን ሲጠብቁ ማየት የሚያሳዝንና መቸም ያልነበረ አዲስ ክስተት ነው:: ወያኔ እንደሆነ ገሎም ቀምቶም የማይረካ አውሬ ነው:: አዛውንቶች: ወጣቶችና ህጻናት የግፍ ሰለባ ሲሆኑ እየታየ ድምጽን ማጥፋትን ምን ይሉታል! የማይቀረውን ሞት በክብር ለመቀበል ካልተቆረጠ እንዴት ነው መከራን ማስቆም የሚቻለው? ማን  ያልተነካ የህብረተሰብ ክፍል አለ?

“ከዚህ በላይ ምን ሊመጣብን ነው!” ብሎ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ የኩራት ሞት መሞት ሲገባ: በሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት እየተቀጡ: በተቀነባበረ መንገድ በጅምላ እየተረሸኑ : ሀብት ንብረታቸውን በግፍ እየተነጠቁ: እትብታቸው ከተቀበረበት ቀየ እየተባረሩ: ካላግባብ ከስራ እየተባረሩ እንዴት ዝም ማለት ይቻላል? በሚዋሻቸው: በሚያታልላቸው: በሚዘርፋቸው: በሚጠላቸው: በሚያዋርዳቸውና በሚያሰቃያቸው መንግሥት ስር አይደለም ችሎ ለመኖር አብሮ ለመዋልስ እንዴት ይቻላል? ልጅን ከጉያ የትዳር አጋርን ከእቅፍ የሚነጥቅ: ትንሽ ከትልቅ ሳይለይ የሚገድልና የሚያወድምን ጠላት እንዴት ነው መታገስ የሚቻለው?

ሲያፈናቅሉት ድምጽን አጥፍቶ የሚፈናቀል: ሀብት ንብረቱን ሲወርሱት ያለውን አራግፎ ሰጥቶ ለልመና አደባባይ የሚወጣ: ከስራ ሲያባርሩት የሚባረር: ሊያርዱት ቢላዋ ሲስሉ ቁጭ ብሎ እያየ ሲገሉት የሚሞት ሰው ከዘመነ ወያኔ በፊት አልታየም:: በመንግስት ስራ የተሰማራውና በንግዱ አለም ውስጥ ድርሻ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለመረጃ ቅርብ በመሆኑና መጠነኛም ዘመናዊ ትምህርት ስላለው በዚህ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያለኝ ስሜት ከቅሬታ ያለፈ ነው::

 1. የሀይማኖት አባቶች:- የተወለድሁበትና የአደኩበት ማህበረሰብ ዘንድ የሀይማኖት አባቶች በእጅጉ ይከበራሉ:: እንዲህ እንደዛሬው ቀኑ ሳይከፋ ቄስ የገዘተው ሰው ግዝቱን ሊያፈርስ አይደፍርም ነበር:: እስላሞችም ከሀይማኖት አባቶቻቸው ቃል አይወጡም ነበር:: እንዲያውም እስላም ማለት ሰላም ማለት ብቻ ሳይሆን ሀቀኝነትም ማለት ነበር:: አንድ ሙስሊም በማንኛውም ነገር ላይ “ወላሂ” ካለ የተናገረው ነገር ሀቂቃ ነው ተብሎ ይታመን ነበር::

ዛሬ ላይ እኒያን የድሮወችን የሀይማኖት አባቶች ለመተካት አልታደል ብለን ሕዝበ አዳም/ አደም ጠባቧን መንገድ ስቶ በሰፊው መንገድ እየነጎደ ነው:: የሀይማኖት አባቶች ሽጉጥ ከታጠቁ: በወታደር ከታጀቡ: ሕዝባቸውን ለጭቆና ካመቻቹ: ለችግር ለተጋለጠው ምዕመን ድምጻቸውን ካላሰሙ: ሀይማኖታችንን ከብረዛ ባህልና ታሪካችንን ከጥፋት ካልተከላከሉ: ስለአንድነትና ስለፍቅር ካላስተማሩ: ስለሰላምና ስለመተሳሰብ ካልሰበኩ ምኑን የሀይማኖት አባት ሆኑት:: ትውልዱ ፈጣሪን የማይፈራ ልቅና ግዴለሽ የሆነው አንድም በሀይማኖት አባቶች የተዛነፈ ተግባር ነው::

በደርግ ጊዜ የተገዘገዘው ሀይማኖት አሁን ላይ ጭራሹን ሊበጠስ ሰልስሏል:: ቤተክርስቲያንና መስጊድ በካድሬወች ሲመራ ሌሎች የሀይማኖት አባቶች ምንም ሳይኮሰኩሳቸው ቁጭ ብለው እየተመለከቱ ነው:: አንዳንዶችም ሀላፊነታቸውን ረስተው ለስጋቸው አድልተዋል:: ዜጎች ሲፈናቀሉና ሲገደሉ እያዩ ድምጻቸው ያልተሰማ አባቶች ይባስ ብለው የመንግስትን አቋም ደግፈው መግለጫ ሲሰጡ መስማት ስሜትን ብቻ ሳይሆን እምነትንም ይጎዳል:: ታዲያ በሀይማኖት አባቶች ላይ እየፈራሁም ቢሆን በትንሹ እንኳ ታዘብኋችሁ ብል በእግዜር ፊት ያስጠይቀኝ ይሆን!

በውስጤ የሚብላላውን ስሜት በትንሹም ቢሆን ተንፍሸ ሸክሜ ቀሎልኝ “ኧሁ!” ብያለሁ:: የጽሁፌ ጓል ወቀሳና ጥላቻ እንዳልሆነ ስገልጽ ካንጀቴ ነው:: በርግጥ በወያኔ ያስተዳደር ዘመን የደረሰው ጥፋት ከሚባለው በላይ መሆኑን ማንም አይስተውም:: ያም ሆኖ በአዲስ ኪዳን የተሻሻለን ህግ ጥሸ “አይን ያወጣ አይኑ ይውጣ” ማለት አልፈልግም:: እንከን ያልኋቸውን በጣም ጥቂት ነጥቦች ያነሳሁት እየደረሰ ያለውን ጥፋት እንድናስተውል ነው:: አነሰም በዛ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ የያንዳንዳችን እጅ እንዳለበትም አምነን ሁላችንም የየድርሻችንን አንስተን ስናበቃ ከስህተታችን ተምረን በቁጭት እንድንነሳሳና የተበላሸውን እንድናስተካክል: የደፈረሰውን እንድናጠራና የተጣመመውን እንድናቃና በማሰብም ነው:: ለኛ ያለነው እኛ ነንና ልብ እንግዛ::

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

Comment

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s