በአትኩሮት ሊታሰብባቸው የሚገባ እውነታዎች። – ከተማ ዋቅጅራ

ሰውን በግድ እየገፋን ዘረኛ እንዲሆን ካደረግነው አደጋው የከፋ እንደሚሆን እሙን ነው። በዘረኝነት መስመር ስልጣኑን የያዘው መንግስት 25 አመት ሙሉ የሰው ህይወትን ከመቅጠፍ የኢትዮጵያ ህዝብንም ወደ ከፋ ችግር ከመክተት ውጪ ያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም። አለ ብሎ  የሚከራከር ካለ ልቦናው በጥቅም የታወረ እና እውነት በውስጡ የሌለ ብቻ ነው። በዘር የተመሰረተ ስርዓት ለውጥ የለውም ብለን የምንናገረው የኦሮሞ ህዝብ፣ የጎንደር ህዝብ፣ የኦጋዴን ህዝብ፣ የጋንቤላ ህዝብ፣ የኦሞ ህዝብን፣ በሚያደርስባቸው ግፍና በደልን በአደባባይ በመቃወማቸው በዘር የተመሰረተው ገዚው ህውአት ያመጣው ጣጣ ለብዙሃኑ ሞትና እንግልት እስራት እና ስደት መንስኤ ሆኗል። ይህ ሁሉ የሰበአዊ መብት ጥሰት የመጣው የራሴ ዘር ገዢ፣ የራሴ ዘር ባለሃብት፣ የራሴ ዘር ተፈሪ፣ የራሴ ዘር ፈራጅ አድርጎ ሌላውን ህብረተሰብ ለት ሰጥ አድርጌ እገዛለው በሚል በዘር ፖሊሲ  ህግ መሰረት በመመራታቸው የተከሰተ አደጋ ነው። ወደፊትም የከፋ ጥፋትና እልቂት የሚያስከትል አካሄድ ነው።

በዘር የተመሰረተ አገዛዝ ከጥፋት ውጪ ምንም ልማት የለውም። ከመተላለቅ ውጪ ምንም ስምምነት አይኖረውም። አደገኛነቱ ደግሞ  በዘር ፖሊሲ የሚያምኑት አካሎች ከፍተኛ አደጋ ሲያደርስ ብቻ የሚነቁ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የዘር ፖሊሲን የሚከተል ነው። ስለሆነም ለአማራው የራሱ የሆነ ካርታ እና ባንድራ፣አማራ የሆነ ተወካይ መሪዎች አድርጎ አስቀምጧል። ለኦሮሞ የራሱ የሆነ ካርታ እና ባንድራ፣ ኦሮሞ የሆነ ተወካይ መሪዎች አድርጎ አስቀምጧል። ለደቡቡ እንደዚሁ። ለኦጋዴን፣ ለጋንቤላ፣ ለአፋር፣ ለቤንሻጉል ጉምዝ እንደዚሁ የራሳቸው ካርታ እና ባንድራ ሰጥቶ አስቀምጧል። እውን ይሄ አካሄድ ለ25 አመት በቆየበት ሰዓት ሲፈተሽ ያመጠው ….ምን ያህል ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ተገድለዋል፣ ምንስ ያህል ሰዎች በዘራቸው ተለይተው ወደ እስር ቤት ታግዘዋል፣ ምንስ ያህል ሰዎች በዘራቸው ምክንያት መኖር አትችሉም ተብለው የሚወዷትን አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፣ እውነቱን ለመናገር ከፈጣሪ በቀር ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ አይቻልም። የንጹሃን ደም ግን እንደሚፋረዳቸው ግን ላስገነዝባቸው እወዳለው የዘገየ ቢመስልም በክፋት መንገድ እና በጥፋት ስራ የተሰማሩት ሁሉ የእጃቸውን ዋጋ የሚያገኙበት ግዜ አይርቅም። ያኔ ጥርስ ማፏጨት ብቻ ይሆናል። በዘር ምክንያት ተለይተህ ሲጎዱበት እንጂ ሲጠቅም አልታየም።

በኢትዮጵያ ዘግናኝ ክንውኖችን እያየን እና እየሰማን የተሻለ ግዜ ይመጣል በማለት አሁን ያለንበት ግዜ ደርሰናል። የዘረኝነት ፖሊሲ የዘራው ህውአት ምርትህን የምታይበት ግዜ ደርሷል እና ለመቀበል ተዘጋጁ። ዘረኝነቱ ሲፈነዳ አፈናቃይ ሳይሆን ተፈናቃይ፣ ገዳይ ሳይሆኑ ሟች፣ ዳኛ ሳይሆኑ ተዳኚ፣ ገዢ ሳይሆኑ ተገዢ፣ እንዳለ የምታውቁበት ግዜው ደርሶ  ነገሮች ተገልብጠው ስታዩት የዘረኝነት ፖሊሲ  ዘግናኝነቱን  እና ክፋቱን ትረዱታላችሁ። የሰው ልጅ ብልጡ ከታሪክ አልያም በትምህርት ይማራል። ሞኝ ግን በራሱ ይማራል። የሚል አባባል አለ።

የዘር ፖሊሲ አደገኛነቱ በሰላም ይኖር የነበረውን ሰው በጥላቻ ይቀሰቀስና ሌላውን ዘር እንዲጠላ ይደረጋል። ይሄንን ጥላቻ አዘል ሲነገረው ወደ ፍጹም ቂም አዘል ይለወጣል። እውነተኝነት በሌለው ነገሮች ይሞላና የሌላውን ዘር ወደ መጥላት እና ወደ ማጥፋት ይነሳሳል። ዘረኛ ያልነበረው በሰላም ሲኖር የነበረው ህዝብ በግድ ተገፍቶ ዘረኛ እንዲሆን ይደረጋል የዚህን ግዜ ሁሉም ብሔር  ውስጥ ዘረኝነት ይፈጠራሉ። የዚህን ግዜ አደጋው ሁላችንም ላይ ይመጣል ወደ አልተፈለገ ግጭቶችም ይገባል። ቀድሞ የጥላቻ መልእክት ስለተላለፈ ለመጎዳዳት ምንም ነገር አያግዳቸውም። ያሸነፈ ግዛቱን የማስፋት የተሸነፈ ደግሞ ግዛቱን የመልቀቅ ነገሮች ይፈጠራሉ። ይሄንን ግጭት እንደ ቀላል ማየት ግን ፈጽሞ ሞኝነት ነው።

1ኛ፡ ለዘራችን ቆመናል የምንል የራሳችን ወገን በብዛት ይረግፍብናል

2ኛ ለግዜው የተሸነፈው ቆይቶ በቀሉን ለመመለስ መነሳት መቻሉ ተረጋግቶ ለመኖር አያስችለንም

3ኛ፡ ፍጹም ዘላቂ በሚመስል መልኩ የትኛውም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የተረጋጋ ኑሮ  መኖር ወደ ማይችልበት የሁል ግዜ የአዘን ቤት እንድትሆን ያደርጋል

4ኛ፡ የሁሉም ዘሮች የራሴ ግዛት ወደሚሉት የመሬት ይዞታ ካርታ አውጥተው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ

ህውአት አሁን በኦሮሚያ፣ በጎንደር፣ በጋንቤላ፣ በኡጋዴን፣ በአኝዋክ፣ በኦሞ፣ እያደረገ ያለው የዚህ የዘረኝነት ውጤት ነው። የራሴ ወገኖች የሚላቸውን አስፍሮ የሌላ ወገን የሚለውን ገድሎ አልያም አባሮ  የራሴ ለሚላቸው በመስጠት ግዛቱን በማስፋፋት ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የዘረኝነት ውጤት ነው። ይሄም ደግሞ  ሊከፍሉት የማይቻላቸውን ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል አለመረዳታቸው ያሳዝናል።

አሁን ባለው የዘር ፖሊሲ ከቀጠልን በመጀመሪያ ከፍተኛ እልቂት የሚፈጸመው በደቡብ ነው። 52 ብሄር አለ 52 ጦርነት ይደረጋል ማለት ነው። ሌላው ኦሮሚያ ወሎን ጨምሮ እስከ ራያ ድረስ የኔ ግዛት ነው ይላል እዚህ ጋር የሚፈነዳ እልቂት አለ ማለት ነው። አማራ ወለጋን፣ ሸዋ ጨምሮ ሃረር ድረስ የኔ ግዛት ነው ይላል እዚህ ጋርም የሚፈነዳ እልቂት አለ ማለት ነው። ሱማሌ ቦረና፣ ባሌን ጨምሮ እስከ አዋሽ ድረስ የኔ ግዛት ነው ይላል እዚህ ጋርም ሌላ የሚፈነዳ እልቂት አለ። ትግራይ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ የኔ ግዛት ነው ይላል እዚህ ጋር የሚፈነዳ እልቂት አለ። ሲዳማ ቦረናን ጨምሮ አዋሳ ድረስ የኔ ግዛት ነው ይላሉ እዚህ ጋር ሌላ እልቂት አለ። በሁሉም አቅጣጫ የተጠመደ ፈንጂዎች አሉ ማለት ነው። ሁሉም ሊያተኩርበት የሚገባው ለዘሬ ቆሚያለው ዘሬን ብቻ ነጻ አወጣለው የሚል አካል ካለ ከላይ በጥቂቱ የገለጽኳቸውን አደጋ ለራሱ እንደመጋበዝ ነው። ምክንያቱም ወደ ይገባኛል ከተኬደ ወደ ፊት ልንጋፈጠው እና አይቀሬ አደጋዎች እና ጥያቄዎች እነዚህ ናቸውና።

ለኢትዮጵያ የዘላቂ መፍትሄ ህዝባችንን የሚጨቁነውን እና የሚገድለውን መንግስት ጥሎ ለህዝብ እኩልነት እና ነጻነት የቆመ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ሊያስተዳድር የሚችል ስርዓት መፍጠር ያስፈልገናል። ይሄንን  የሚያደርግ ማንም ኢትዮጵያዊ ለወገኑ የሚያስብ ሃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆነ ልጠቁም እወዳለው። አይ የለም በዘራችን የምንል ከሆነ ግን ዘረኛ በሆንን ቁጥር ሌላ ለኛ ጠላት ሊሆኑ  የሚችሉ አደገኛ ዘረኛን እንደምንፈጥር ልናውቅ ይገባናል።

ከተማ ዋቅጅራ

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s