ግንቦት 20 እንዲህ መቀለጃ ሆና ትቅር?

ከታዛቢ(አዲስ አበባ)

ሥራየ መምህርነት ነው፡፡ በአንድ የመንግሥት የ2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ውስጥ አስተምራለሁ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ የግንቦት 20 የኢትዮጵያ የነፃነት ቀን እንደመሆኑ የበዓሉን መቃረብ አስታክኬ በየምገባባቸው በርካታ ክፍሎች ትምህርቱን ከመጀመሬ በፊት “እንኳን አደረሳችሁ” እላለሁ፡፡ ይሀንን የምለው ኢሕአዲግ መራሹ ዴሞክራሲያዊው መንግሥታችን ጨቋኙን የደርግ መንግሥት ደምስሶ ሕዝባዊ መሠረት የተላበሰና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቆመ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመትከሉ ነው፡፡ በግንቦት 20 1983 ዓ.ም የተመሠረተው ይህ በሕዝቦች መፈቃቀድ የተገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኢትዮጵያን ከመፈራረስና እንደሶማሊያ ከመበታተን የታደገ በመሆኑ ዕለቱ ብቻ ሣይሆን ወሩ በሙሉ በድምቀት ቢከበርና ለዚህ የላቀ ማኅበረሰብኣዊ ደረጃ ያደረሱን እንደክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊና አባይ ፀሐዬን የመሰሉ ዕንቁ ታጋዮቻችንም ቢወደሱ አግባብ ነው ብለን የምናምን ኢትዮጵያውን እጅግ ብዙ ነን – በሀገር ውስጥም  – ወላ ከሀገር ውጪም፡፡

TTPLF

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አንዳንድ የዴሞክራሲ ምንነት ገና ያልገባቸው ተማሪዎችና መምህራን በዚህ ታላቅ በዓላችን ላይ ሲያላግጡና ሲያሾፉ ስመለከት በጣም እበሳጫለሁ፡፡ ሀገራችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲን ለማየትና በተግባር ለማጣጣም በመታደሏ መደሰትና ጮቤ መርገጥ ሲገባን ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ በማቆጥቆጥና ብሎም በማበብ እንዲሁም ሥር በመስደድ ላይ የሚገኘውን የኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲና የፌዴራል ሥርዓት ለማጠየም የሚደረገው የአንዳንድ የዋህና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች ተንኮል ይገርማል፤ ያሳዝናልም፡፡ የሚወራ ነገር ቢያጡ ዴምክራሲያዊው ሥርዓታችን “የጥቂት ዘረኞች ደባ የሚንጸባረቅበት ነው” በሚል አፍራሽና መሠረተ ቢስ ክስ ሕዝባዊውን ሥርዓት ለማጠልሸት በከንቱ የሚንፈራገጡ ወገኖች አሉ – ግን በጣም ጥቂት በመሆናቸው የትም አይደርሱም፡፡

እኔ በምሠራበት ትምህርት ቤት የአንድ ሕዋስ ተጠሪ ነኝ፡፡ መሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ ከመሰል ፓርቲዎች ጋር በእኩል ዕድልና በእኩል ሜዳ ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ በሥሩ ሕዝቡን አንድ ለአምስት ሲያደራጅ ከቀዳሚ ተሰላፊ መምህራን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ስለዚህም በትምህርት ቤቴ የበኩሌን ድርሻ እያበረከትኩ እገኛለሁ፡፡ በተቃዋሚ ሚዲያዎች ራሴን ለማስተዋወቅ ጥረት ባደርግም እስካሁን ዕድል አልተሰጠኝም፡፡ ዛሬ የሞከርኩት ከተሳካ ግን ደስ ይለኛል፡፡ በዚያውም ልዩነቶችን ለማትበብ ይረዳል፡፡ ሰሚ አጥቶ እንጂ በሕዝባዊ ማዕበል የምርጫ ሣጥን በትረ ሥልጣን የጨበጠው ኢሕአዲግ ሥልጣን መረከብ የሚችል ሌላ ብቁ ፓርቲ ወይ የፖለቲካ ኃይል ካገኘና ተወዳድሮ ካሸነፈው በሰላም ለማስረከብ ብዙ ጊዜ ቃል ገብቷል፤ በተግባርም አሳይቷል፡፡ ለምሣሌ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከደቡብ ሕዝቦች መመረጣቸው የሚያሳየን የፌዴራሉ ሥልጣን ከአነሳው የትግራይ ብሔር ወጥቶ ወደብዙኃኑ የደቡብ ብሔር ብሀየረሰቦች የመዛወሩን ብሥራት ነው፡፡ ይህንን የሥልጣን ሽግሽግና የኃይል ሚዛን ለውጥ አሌ የሚል ሰው ቢኖር ማር እያላሱት ጨው እንግሊዝ ነው የሚል ዳተኛ ሰው ነው፡፡ ይገርማል፡፡

በሰሞኑ የደረሰብኝ የተማሪና የማህምራን ለበጣና ፌዝ ግን መቼም ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በየክፍሉ ስገባ “እንኳን አደረሳችሁ” ስል “ለምኑ?” ይሉኛል፡፡ “እንዴ! ለታላቁ የግንቦት 20 በዓል ነዋ!” ስላቸው ይስቁብኛል፡፡ “ምን የሚያስቅ ነገር ተገኘ? ‹እንኳን አደረሳችሁ› ማለት ነውር ነው እንዴ?” ስላቸው አሁንም የበለጠ ይስቃሉ፡፡ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የሚስቁብኝ ደግሞ አንድም ሣይቀሩ ሁሉም ናቸው፡፡ ያደሙብኝም መሰለኝ፡፡ ወደ ፓርቲ ጽ/ቤት ሄጄም እንደዚሁ ብል ሣቁብኝ፡፡ የነሱን ሣቅ ግን ከዐይናቸው ውስጥ ነው ያነበብኩት፡፡ ምክንያቱም ዋናው ሰብሳቢያችን አቶ ጎይቶም ሐጎስ አብሮን ስለነበረ ደፍረው በጥርስ በሚገለጥ ሣቅ ስሜታቸውን ሊያሳዩኝ አልቻሉም፡፡ ብቻ ከሁኔታቸው እንደተረዳሁት ግን ለምንም ነገር እንዳልደረስን የሚያሳብቅ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ነገር የኢሕአዲግን ያጎረሰ እጅ እንደመንከስ ነው፡፡

ግን ለምን?

ተማሪዎቼን ስጠይቅ “ጋሼ፣ ይሄ በዓል እኮ ለእናንተና ለአለቆቻችሁ እንጂ ለኛ ለተራው ሕዝብ ከመከራና ስቃይ ውጪ ያመጣልን ነገር የለም፡፡ ስደት፣ እስራት፣ የኑሮ ውድነት፣ ግርፋት፣ ሞት፣ ሙስና፣ ዘረኝነት፣… ነው ያመጣብን፡፡ ስለዚህ ለኛ እርግማናችን እንጂ በዓላችን አይደለም፡፡ የናንተው በዓል ነው፡፡ እዚያው ጨፍሩ፤ ከተራበው ሕዝብ አፍ እየቀማችሁ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመጠጥና ለምግብ፣ ለሴትና ለዳንኪራ አውሉት፤ ነገ ግን እንደምትጠየቁበት ዕወቁ፤ እናንተ በአማራ ስም የምትነግዱ ብአዴኖች ደግሞ ያላወቅንባችሁ መስሏችኋል፡፡ በሣምንታት ዕድሜ ለደረቀ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሁለት ቢሊዮን ብር ማውጣታችሁን ሰምተናል – በስማችን ያን ሁሉ በጀት ቀረጠፋችሁት፡፡ ውኃው ለምስኪኑ ገበሬ ቢደርስ እንኳ ብትበሉትም ምንም አልነበረም፤ ግን አንዲት ቡትሌ ውኃ ሣትሰጡት  በጥቂት ሚሊዮኖች ሊያልቅ በሚችል ቁፋሮ ሰበብ ሁለት ቢሊዮን ብር መዝረፍ የግፍ ግፍ ነው፤ ልጅ አይውጣላችሁ ” አሉኝ በማን አለብኝነት ድፍረት፤ ደግነቱ ምን እንደተናገሩ በውነቱ አልሰማሁም፤ የኮሚቴ አባል እንደመሆኔ ስለበዓሉ ዝግጅት እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ በግማሽ ልብ እንደሰማሁት ግን እውነቱ  ይህ እንዳልሆነ ሁላቸውም ልቦናቸው ያውቃል፡፡ እንዲህ መናገራቸው ራሱ የዴሞክራሲያችን ውጤት መሆኑን ያወቁት ደግሞ አይመስሉም፡፡ ከኢሕአዴጋዊ ዴሞክራሲያችን ጋር ወደፊት!

የመምህራን ማረፊያ ውስጥ ያገኘኋቸው መምህራን ደግሞ “ለምኑ ነው ‹እንኳን አደረሳችሁ› የምትለን?” በማለት በቁጣ ነው ያበሻቀጡኝ፡፡ የለውጡን ጠቃሚነት ላስረዳቸው ብሞክርም አንድም ሰው የሰማኝ የለም፡፡ እንዲያውም አንዱ በንዴት እየፎገላ፡-

“ሰማህ ወንድም ጓድ ካድሬ! እንዲያውም ከነፃነት በኋላ ግንቦት 20 የሚባል ቀን ከናካቴው እንደማይኖር ካሁኑ ላርዳህ፤ ቁርጥህን ዕወቅ፡፡ ግንቦት 19 ይባልና በቀጥታ ወደ ግንቦት 21 ይኬዳል፡፡  ስሟን ቄስ ይጥራውና ይቺ ግንቦት 20 የሚሏት ቀን ጳጉሜ ላይ ትደረብና ከነፃነት በኋላ የምትኖረው ጭንጋፏ የጳጉሜ ወር በያመቱ 6 ቀናት ይኖራታል፤ በአራት ዓመት አንዴ ደግሞ 7 ትሆናለች፡፡ ግም-ቦት ያኔ በድምሩ 29 ቀናት ብቻ ይኖሩታል ማለት ነው፡፡ ግንቦት 20 በአሜሪካና በአውሮፓ ኃያላን ሀገራት ቡራኬ የኢትዮጵያ ውድመት ለኢትየጵያውንና ለዓለም መርዶ የተነገረበት፣ የዚህች ታሪካዊ ሀገር መፈራረስ የታወጀበት ዕለት በመሆኑ ቀኒቷ የተረገመች ናት፡፡ አሁን ለይመስልና ለታይታ ያህል የሚያከብሯትም እንደርሷው የተረገሙ ያንተው አለቆች ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ‹እንኳን አብሮ አደረሰን› የሚል ሰው አገኛለሁ ብህ አትድከም፡፡…” አለና ወሽመጤን ቆረጠው፡፡ ኧረ የራሱ ወሽመጥ ይቆረጥ፤ የኔስ ገና ነው፡፡

ከትምህርት ቤት ውጪም የትም ሄጄ “እንኳን አደረሳችሁ” ስል የማገኘው መልስ ተመሳሳይ ነው፤ መሣቅ የሚችሉ ይስቃሉ፡፡ የፈሩ ደግሞ ገላምጠውኝ በሆዳቸው የስድብ መዓት ያወርዱብኛል፡፡ አንዱ በሆዱ ምን አለኝ “አንት አጋሰስ ሆዳም! ቆይ ታያለህ! አሁን ሆድህን ሞላህና አብረህ ታረጠርጣለህ አይደል? ይህ ክፉ ቀን የማያልፍ መስሎህ ነው አይደል?”፡፡ እኔም በሆዴ “ መስሎሃል! ሆዴስ አልሞላም፡፡ ግን እንደዚህ ያለ የደስታና የድሎት ዘመን ሀገርህ ኢትዮጵያ መቼም አታገኝም፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ፍትህንና ሰላምን ከነፃነትና እኩልነት ጋር አስማምቶ በሀገር ላይ የሚያነግሥ መንግሥት መቼም አይመጣም፡፡ የደርግና የቀደሙት መንግሥታት ሕዝባቸውን በውሸትና በማስመሰል ቀጥቅጠው ይገዙ ነበር፡፡ ኢሕአዲግ ግን በእውነትና በትክክለኛ ፍትሃዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት አንዱን ጎሣ ከሌላው፣ አንዱን ሃይማኖት ከአንደኛው ሳያበላልጥና እንደቀድሞዎቹ ክፉዎች መንግሥታት ለማጋጨት ሳይሞክር ያስተዳድራል፡፡ ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚቸግረው ነገር ሁሉ እየረዳ አቅፎና ደግፎ የያዘው” አልኩ፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባል፡፡ የርሱን ብሶት እንደሰማሁለት የኔን ምሥክርነት ሰምቶ ከሆነ እሰዬው ነው፡፡ ምነው ሁሉንም እንደኔ ልብ ሰጥቶት ኢሕአዲግን ለተጨማሪ 100 ዓመታት በመረጠው!

ግን ሰውን ምን ነካው? “እንኳን አደረሳችሁ” ሲባል ብሶቱን የሚያሰማው በርግጥ ምን ደርሶበት ይሆን? የኔ መነፅር ተበላሽቶ ይሆን ወይንስ ሕዝቡ እንዳለ ተሳስቶ ነው ልበል? የትኛውን እንደምል ጨነቀኝ፤ እስኪ ማለት ያለብኝን ንገሩኝ፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s