ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመምሪያ እና የኮሌጅ ሓላፊዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ

  • የማኅበሩ ሚዲያዎች ታግደው ክሥ እንዲመሠረትበት አቋም ለማስያዝ እየተቀሰቀሰ ነው
  • ልዩ ጸሐፊአቸው ንቡረ እድ ኤልያስ እና አባ ሰረቀ ብርሃን ግንባር ቀደም ቀስቃሾች ናቸው
  • ቋሚ ሲኖዶስ እና ብፁዓን አባቶች፣ ፓትርያርኩን ሲመክሩ እና ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል
  • ፓትርያርኩ፥“ምን ሲኖዶስ አለና” በሚል የጠሩት ስብሰባ፣ ሕጋዊም መዋቅራዊም አይደለም

ፓትርያርክ አባ ማትያስ፥ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችን ዋና እና ምክትል ሓላፊዎችን እንዲኹም የሦስቱን መንፈሳውያን ኮሌጆች የአስተዳደር ሓላፊዎችን፣ ዛሬ፣ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸው ተሰማ፡፡

በመንበረ ፓትርያርኩ አዳራሽ ከጠዋቱ 2፡30 ላይ የተጠራው አስቸኳይ ስብሰባው÷ ማኅበሩ በኮሌጆች ውስጥ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄስለሚገኝበት አሳሳቢ ኹኔታ በሚዲያዎቹ ማስነበቡን ተከትሎ፣ በክሥ እና በቅስቀሳ መልክ ያሳለፉትን መመሪያ የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ተገልጧል፡፡

መመሪያው፣ የተሐድሶዎችን ክሥ የሚያስተጋባና የእውነት ጠብታ እንደሌለው በመተቸት ማኅበሩ ባለፈው ሳምንት በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ክፉኛ ተበሳጭተዋል የተባሉት ፓትርያርኩ፣ በተለይም ከማኅበሩ አገልግሎት ጋር የሚገናኙ የሥራ ዘርፎችን በሚመሩ ሓላፊዎች በኩል ተጽዕኗቸውን ለማጠናክር የሚያስችል ‘የጋራ አቋም’ እንዲያዝማሰባቸው ተጠቅሷል፡፡

በክትትል እና በቁጥጥር ስም ለአገልግሎቱ አካሔድ ቢሮክራሲዊ ዕንቅፋቶችን ከመፍጠር በተጨማሪ የማኅበሩ መጽሔት እና ጋዜጣ/ሐመር እና ስምዐ ጽድቅ/ ታግደው ማኅበሩ በኮሌጆቹ የስም ማጥፋት ወንጀል ክሥ እንዲመሠረትበት ለማድረግ መታሰቡም ታውቋል፡፡

በዚኹ ዓላማ አቋም እንዲያዝ፣ ቅስቀሳውን በተሰብሳቢዎች ላይ በዋናነት ከሚያካሒዱት የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ዲን ተስፋዬ ሃደራ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

ከተሰብሳቢዎቹ የአብዛኞቹ ሓላፊዎች ተጠሪነት፣ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ አስፈጻሚውን አካል በበላይነት ለሚያስተዳድረው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ነው፤ የተወሰኑትም በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾኑ አካላትን የሚመሩ እንደ መኾናቸው፣ በፓትርያርኩ የተላለፈው የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ መዋቅራዊ አግባብነት የለውም፤ ውሳኔዎቹም ሕጋዊ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡

ይልቁንም ስብሰባው፣ ፓትርያርኩ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና አሠራር ከመፃረር አልፈው መሠረተ ህልውናውንም እስከ መጠየቅ ለደረሱበት ሰሞናዊ ዓምባገነናዊ አካሔዳቸው ተጨማሪ ግልጽ ማሳያ ነው የሚኾነው፡፡

ፓትርያርኩ ለኮሌጆቹ ያስተላለፉት መመሪያ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ አኳያ በተደጋጋሚ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ጋር እንደማይስማማ በመጥቀስ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲኹም ብፁዓን አባቶች በተናጠል እና በጋራ በመኾን አካሔዳቸውን እንዲያጤኑት ሲመክሯቸውና ሲያስጠነቅቋቸው መሰንበታቸው ታውቋል፡፡

ምክር እና ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው ከመታረም ይልቅ፣ “ይህን ማኅበር አንድ ነገር አናደርገውም ወይ?” በማለት የተወሰኑት ፓትርያርኩ፣አስፈላጊ ከኾነም ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራና ጉዳዩ በምልዓተ ጉባኤ እንዲታይ ሐሳብ ሲቀርብላቸው፣ “ምን ሲኖዶስ አለና!”እስከማለት ነው የደረሱት፡፡

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a comment