ነገሮች አዲስ የሚሆኑት፣ በእኛ ትናንትን መርሳት – ይገረም አለሙ

ሰሞኑን  በደቡብ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የተፈጸመን የባሪያ ፍንገላን ዘመን የሚያስታውስ  ኢሰብአዊ ድርጊት  የሚያሳይ ፎቶ  በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተሰራጭቶ አጀኢብ ጉድ ብለናል፡፡ ነገሩ ትናንትን እየረሳን ዛሬ ለሚያጋጥመን ነገር አዲስ እየሆንን ጉድ ጉድ ለምንለው  ለእኛ ነው እንጂ አዲስነቱ ለወያኔ ከበርሀ ጀምሮ አብሮት የኖረ ተግባሩ ነው፡፡

አይደለም ሥልጣኑን ሊነጥቁት በተቃውሞ የተሰለፉ፣  እኩይ ድርጊቱን እያጋለጡ ማንነቱን ጸሀይ የሚያሞቁ ፣ ሀሳብ እቅዱን እየተቃወሙ ጉዞውን የሚያደናቅፉ ቀርቶ የህውሀት አባል ሆነው ስህተት የጠቆሙ የዓላማቸውን መስመር መሳት የገለጹ የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የነቀፉ ወዘተ ምን እንደተፈጸመባቸው የአይን ምስክር የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ ሰምተናል ጽፈው አንብበናል፡፡ ባዶ ምንትስ ይባሉ በነበሩት እስር ቤቶች በውልደታቸው ትግሬ በድርጅታቸው ህውኃት የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ ምን አይነት ኢሰብአዊ ድርጊት አንደተፈጸመባቸው እነ ገብረ መድህን አርአያ ደጋግመው የነገሩን ነው፡፡ ዛሬም በተለያየ የሥልጣን ስም ተቀምጠው አረመኔያዊውን ድርጊት የሚፈጽሙ የሚያስፈጽሙት እነዛ የበርሀው ሲኦል እስር ቤቶች ሀላፊዎች የነበሩቱ ናቸው፡፡

ለሥልጣናቸው የሚያሰጋ፣ ያሰቡ ያቀዱትን ተፈጻሚ እንዳያደርጉ አንቅፋት የሚሆን፣ ማንም ሆነ ከየትም  ከማጥፋት የማይመለሱት ወያኔዎች (በተለይም አቶ መለስ) ዘር ሀይማኖት ሳይለዩ አስሮ ማሰቃየቱን አፍኖ መሰወሩን ገድሎ መጣሉን ብሎም ርስ በርስ ማገዳደሉን አብይ ተግባራቸው አድርገው የኖሩ ለመሆናቸው  ብዙ እጅግ ብዙ ማረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

የህውኃት ቀኝ እጅ የነበረው የደህንነቱ ሹም ክንፈየአግልግሎት ግዜው ሲያበቃ እንዴት እንዳስገደሉትና የግድያ ትዕዛዙን በፈጸመው የዋህ ታዛዥ ላይ ያደረጉትን የምናውቅ  በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ተግባር ለምን አዲስ አንደሚሆንብንና እንደሚገርመን  ራሱ የሚገርም ነው፡፡ ለህይወታቸው መድህን ለሥልጣናቸው ዘብ ሆነው የኖሩ ሰዎቻቸውን ለማጥፋት የማይመለሱ ሰዎች አንገዛም ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት ኢሰብአዊ ድርጊት ሁሌም አዲስ የሚሆንብን እኛ ትናንትን በመርሳት በሽታ በመለከፋችን  አለያም ሞኝ የሰማ/ያየ እለት እንደሚባለው እየሆነብን እንጂ ድርጊቱ ለወያኔ አዲሰ  አይደለም፡፡ እንደውም  ትናትን የመርሳት ችግራችን ከእባብ አንቁላል ርግብ አይጠበቅም የሚለውን አባባል  አስረስቶን የተቃውሞአችን እንዴትነትና  የጩኸታችን ምንነት  ከወያኔ የባህሪው ያልሆነ ነገር የምንጠብቅ ያስመስለናል፡፡

መቅረጸ ድምጽም ሆነ ምስል ያልደረሰባቸው የአይን ምስክርም ተገኝቶ ይፋ ያላደረጋቸው ብዙ አጅግ ብዙ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊቶች በወያኔ ለመፈጸማቸው በመረጃ ከተረጋገጡት ድርጊቶቹ ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡እነዚህ ሰዎች ለሥልጣን የበቁት የመረጃ ማስተላለፊያው ጥበብ እንዲህ ባለልተስፋፋበትና ባልተራቀቀበት ዘመን ቢሆን ምን ያደርጉ ነበር ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡የሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በር ዘግተው በምስጢር የሚነጋገሩት ድምጽ ከምስል እየሾለከ ለአለም ህዝብ አይንና ጆሮ ሲበቃ የማያስደነግጣቸው፣ የማያሳፍራቸውና የማያስፈራቸው (ለነገሩ ማን ሰው ብለው) ወያኔዎች በድብቅ የሚሰሩት ሁሉ ተደብቆ የሚቀር ቢሆን የአረመኔነታቸው መጠን የክፋታቸው ደረጃ  የአገዛዛቸው ግዞት እስከምን ይደርስ አንደነበር መገመት አይገድም፡፡

ጎምቱ ጋዜጠኞች ውሻ ሰው ነከሰ ዜና አይሆንም ሰው ውሻ ቢነክስ ግን ትልቅ ዜና ነው ይላሉ፡፡ የአባባሉ ምንነት ግልጽ ነው፡፡ ውሻ ሰው መንከሱ የተፈጥሮው፣ የባህሪው፣ የሚጠበቅበት ተግባሩም ስለሆነ  ነው ዜና የማይሆነው፡፡ ሰው ግን ውሻ ቢነክስ  ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቅና የማይገመት አዲስ አስገራሚ ክስተት  በመሆኑ ነው ትልቅ ዜና የሚሆነው፡፡

ወያኔም ማሰሩ፣ መግደሉ፣ ማሰቃየቱ፣ መዋሸቱ ፣ማታለሉ ሰው በሀሰት መወንጀሉ ወዘተ  ለሥልጣን የበቃበትና ሀያ አራት ዓመታትም ለመግዛት የቻለበት የተፈጥሮ ባህሪይው እና ተግባሩ  በመሆኑ በዚህ መልክ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ለጋዜጠኞች ዜና ሊሆኑ ቢችሉ አንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን  አዲስ ክስተት የሆኑ ያህል ሊያስገርሙን ሊያስደንቁንም ሆነ ሊያስደደነግጡን  አይገባም ነበር፡፡ ምነው ቢሉ እየረሳናቸው ካልሆነ በቀር አብረውን ያሉ ናቸውና፡፡

ይልቁንስ ከወያኔ አንጻር ለመገናኝ ብዙኃን ትልቅ ዜና ሊሆን ከኢትዮጵያውያን አልፎ የኢትዮጵያን ጉዳይ (ለራሳቸውም ዓላማም ሆነ ለህዝቡ ጥቅም ሲሉ) በቅርብ ለሚከታተሉ አለም አቀፍ ግለሰቦች ቡድኖችና መንግሥትታ አስገራሚ ክስተት ሊሆን የሚችለው፡፡

  • ሀያ አራት አመት የተጓዝንበት መንገድ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየወሰደን እንዳልሆነ ስለተገነዘብን  መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ቢባል፤
  • ለዘመናት አብረውን የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን እየቆፈሩ  አዳዲስ ልዩነቶችን መፍጠር የዛሬ መንገዳችንንም ሆነ  የነገ ግባችንን ከማሰናከሉም በላይ ኢትዮጵያን አንደ ሀገር ለማቆየት አስጋቸሪ የሚያደርጉ በመሆናቸው በእርቅ እልባት ሰጥቶ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል ቢባል፤
  • የገደለ ያስገደለ፣ የሰረቀ የተባበረ፣ በህዝብ ሀብት የከበረ፣ ከህግ በላይ ያደረ፣ወዘተ ለፍትህ ቀርቦ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ  ርምጃዎች መታየት ቢጀመሩ፣
  • የመገናኛ ብዙሀን ሰራተኞች አፋሽ አጎንባሽ መሆናቸው ቀርቶ እውነትን አነፍናፊ፣ የባለሥልጣናትን ፊት እያዩና ትንፋሽ እያዳመጡ የሚሰሩ ሳይሆን የሙያቸውን ነጻነት አክብረው ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው መስራት የሚችሉበትን አሰራር ተግባራዊ  የማድረግ ጅምር ቢታይ፤
  • ክልሎች በህገ መንግሥቱ የሰፈረው ሙሉ ነጻነታቸው ተጠብቆ ከህውኃት የሞግዚት አስተዳደር ተላቀው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ጅማሮ ቢታይ ፤
  • አባልም ሆነ አጋር የሚባሉት በህውኃት ተፈጥረው በህውኃት የሚዘወሩት ድርጅቶች የአገልጋይነት ዘመናቸውን ፈጽመዋል ተብሎ  በራሳቸው መቆም የሚያስችላቸው እንቅስቃሴ ቢጀመር፡፡
  • በድርጅት ታጥሮ በታማኝነት ተወስኖ ሀገር መምራት አንዳማይቻል የሀያ አራት አመት ልምዳችን አስተምሮናል፣ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሀገር መምራት በእውቀትና ሁሉን አሳታፊ በማድረግ  መሆን እንለበት ተገንዝበናል  ተብሎ ይህንኑ ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ ርምጃ  ቢታይ፡፡ ሌላም ሌላም ተመሳሳይ ነገር ከወያኔ ሰፈር ቢታይ ቢሰማ ትልቅ አስገራሚና ማራኪ ድንቅ ዜና ይሆናል፡፡ከዚህ ውጪ መልካም አስተዳደር የፍትህ መጓደል እያሉ ማላዘንም ሆነ  ይቅርታ እንጠይቃለን ማለት ሸብረክ ያሉ መስሎ ግዜ መግዣ የወያኔ የባህሪው  ተግባር ነውና ሊደንቀን አይገባም፡፡

ነገር ግን ወያኔ ያልፈጠረበትን በምክርም በመከራም ሊቀበለው ያልቻለውን ይህን ቅዱስ ተግባር በምን ተአምር ፈጽሞት ይህ  እውነት ሆኖ ለመስማት እንበቃለን! አይታሰብም፡፡ ወያኔዎች ይህን ለማድረግ አንደገና መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ እኛስ ትናንትን እየረሳን በየግዜው የሚገጥሙንን የወያኔን የባህርይ ድርጊቶች  እንደ አዲስ  ከማየት ለመላቀቅ እና ትግሉን በምሬትና በወኔ ለማጥበቅ  እንደገና መፈጠር ይጠይቀን ይሆን?

ትናትን እየረሱ የእለት የእለቱን አዲስ እያደረጉ መጮኹ በትግሉ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የበደል ሸክሙ የሚከብደን፣ የጥቃቱ ምሬት የሚመረን፣አንባገነናዊ አገዛዙ የሚያንገሸግሸን ከ እስከ አሁን ያለውን ስናስታውስ ነው፡፡ የዛሬው ሲያስለቅሰን ሲያስቆጣን ብቻ ሳይሆን የትናቱም ሲቆጠቆጠን ነው፡፡  የትናንቱን እየረሳን ለዛሬው አንድ ሳምንት እየጮኸን ከዛም ሌላ አዲስ ነገር እስኪመጣ ይህን እየረሳን  እኩል መብሰል ባለመቻላችን (ጥሬ  ብስልና የአረረ) ነው ሀያ አራት አመት ሙሉ ትግል እንጂ ለውጥ ማስመዝገብ ቀርቶ አዳዲስ ጥቃቶችን ማስቀረት፤ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይፈጸም ማስቆም ወያኔን ከደደቢት ህልሙ ስንዝር መግታት  ያልቻልነው፡፡  እውቁ የጽሁፍ ሰው አቶ ከበደ ሚካኤል ልጆች ሆነን ባነበብነው አንድ ጽሁፋቸው ፤

ያለፈው ሲረሳኝ መጪውን ሳላውቀው

እኔ መቼ ይሆን የምጠነቀቀው፤  ብለው የነበረው  ከላይ ለተገለጸው  ለእኛ እኛነት  በቂ ገላጭ አይሆንም ትላላችሁ?

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a comment