አንድነት ፓርቲ በአዲስ መንገድ ራሱን እያስተዋወቀ ነው

አንድነት ፓርቲ፣ በወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ካፌዎች የሻይ ቡና ውይይት በማካሄድ ፓርቲውን በአዲስ መንገድ ማስተዋወቅ መጀመሩን የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ አቶ እንግዳ ወልደፃዲቅ፣ ለፍኖተ-ነፃነት ገለፁ።

“ድምፅ አለኝ ምርጫ አለኝ” በሚል መሪ ቃል ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም የተጀመረው የሻይ ቡና ውይይት ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ ሲሆን የፕሮግራሙ አላማ “ህብረተሰቡ ስለምርጫው እንዲወያይ በማድረግ ህብረተሰቡ ለለውጥ እንዲነሳ” ማድረግ መሆኑን አቶ እንግዳ ገልፀዋል። ውይይቱ በአስር ክፍለ-ከተሞች እንደሚካሄድ የገለፁት ሃላፊው በፕሮግራሙ ወጣቶች፣ የፓርቲው ደጋፊዎች እና ከፍተኛ አመራር አባላት በየእለቱ በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ውይይት እንደሚያካሄዱ ገልፀዋል። ውይይቱ አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ካፌዎች እየተካሄደ እንዳለ የገለፁት ሀላፊው፣ ከህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ የሚባል ግብረ-መልስ እያገኙ እንዳለ አስታውቀዋል። በየካፌው የአንድነት አርማ ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ውይይቱን እያካሄዱ በመገኘት ላይ እንዳሉ የገለፁት አቶ እንግዳ ፣ እስካሁን ከህብረተሰቡ በማግኘት ላይ ያሉት ምላሽ አመርቂ ሊባል እንደሚችል አስታውቀዋል።

“የወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በቀጣይነት ምን ለማድረግ አስቧል?” የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አንግዳ ወልደፃዲቅ፣ “የወጣቶች ጉዳይ በቀጣይነት የተለያዩ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን እንደሚሰራ እና ከህዝብ ጋር የሚደረገው ውይይት ቀጣይነት እንደሚኖረው እና የማህበራዊ ድረገፅን ጨምሮ ህዝቡን ማግኘት በሚቻልባቸው መድረኮች ሁሉ ህዝቡ ስለምርጫው እንዲወያይ ማድረግ ነው ብለዋል። ይህ አይነቱ የውይይት መድረክ ቀጣነት እንዲሚኖረው ገልፀው አሁን በጀመሩት የሻይ ቡና ውይይት ብቻ እንደማይገደቡ” አስታውቀዋል።

ድምፅ አለኝ ምርጫ አለኝ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የሻይ ቡና ውይይት ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል።

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a comment